1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት ውል የተፈረመበት ቀን ታስቦ ዋለ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 2009

በጣሊያን መዲና ሮም የተሰባሰቡ የ27 የአውሮፓ ሃገራት መሪዎች የአውሮፓ ህብረት መመስረቻ ውል የተፈረመበትን 60ኛ ዓመት አስበው ዋሉ፡፡ ህብረቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል አውሮፓውያን ከእርስ በእርስ ሽኩቻቸው እንዲታቀቡ የህብረቱ መሪዎች አስጠንቅቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2ZxIA
Italien EU Gipfel
ምስል picture-alliance/AP Photo/A.Medichini

በጣሊያን መዲና ሮም የተሰባሰቡ የ27 የአውሮፓ ሃገራት መሪዎች የአውሮፓ ህብረት መመስረቻ ውል የተፈረመበትን 60ኛ ዓመት አስበው ዋሉ፡፡ ህብረቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል አውሮፓውያን ከእርስ በእርስ ሽኩቻቸው እንዲታቀቡ የህብረቱ መሪዎች አስጠንቅቀዋል፡፡ መሪዎቹ ዛሬ ለስብሰባ የተቀመጡት ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት የወሰነችው ብሪታንያ ይፋዊ የመልቀቂያ ደብዳቤዋን ከምታስገባበት አራት ቀናት አስቀድሞ ነው፡፡ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይም በስብሰባው ላይ አልተገኙም፡፡ የብሪታንያ መውጣት ለህብረቱ ትልቅ ጉዳት ነው ቢባልም በሮም የተሰባሰቡት መሪዎች ህብረቱ በ60 ዓመት ውስጥ ያስገኘውን ሰላም እና ብልጽግና አወድሰዋል፡፡

የአውሮፓ ሃገራት መሪዎች በቃጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ቀውሶች የሚታመሰውን ህብረትም ይበልጥ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል፡፡ ብዙዎቹ መሪዎች ኢኮኖሚያዊ እና የጸጥታ ጥቅሞች ከተፈጠሩ ለህብረቱ ያለው ህዝባዊ ድጋፍ ያንሰራራል ብለው ያምናሉ፡፡ “ዛሬ ለማይከፋፈል እና ለማይነጣጠል ህብረት የገባነውን ቃል የምናድስበትና ቁርጠኝነታችንን በድጋሚ የምንረጋግጥበት ነው”ብለዋል የአወሮፓ ህብረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዣን ክላውድ ጁንከር፡፡ የዛሬ ስድሳ ዓመት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አባታቸው ሉክዘምበርግ ውስጥ በጀርመን ጦር ሠራዊት ውስጥ ተገደው መግባታቸውንም አስታውሰዋል።

ውሉ ከተመሰረተ ከአንድ ወር በኋላ የተወለዱት የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ቱስክ በበኩላቸው በጦርነት ፍርስራሽ ውስጥ የልጅነት ዘመናቸውን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል። በህብረቱ አንዳንድ አባል ሃገራት ዘንድ የህብረቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ቢነገርም መሪዎቹ ግን «መተባበራችን ለበጎ ነው» ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ተፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ