1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግጭቱ ተሳትፏል የተባለ የሶማሊያ ወታደር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል

ማክሰኞ፣ መስከረም 2 2010

ምኤይሶ ከተማን ጨምሮ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎችን በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ተሳትፏል ሲል የኦሮሚያ ክልል ወነጀለ።

https://p.dw.com/p/2jphu
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በምትገኘው የምኤይሶ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ እና ምሊሻዎች ተሳትፈዋል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ አዲሱ በግጭቱ ተሳትፏል የተባለ የሶማሊያ ወታደር በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጨምረው ተናግረዋል። በምኤይሶ የተጀመረው የድንበር ግጭት ወደ ቦረና፤ባሌ ፤ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢዎች ተስፋፍቷል። በግጭቶቹ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ድረስ በግልፅ አይታወቅም። 

"የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት እንደተሳተፉበት ማረጋገጥ ችለናል። ከዚያም ባለፈ ደግሞ ሹኔ ኬሩ አብዲ የሚባል ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ከሞቅዲሹ የመጣ የሶማሊያ ወታደር የሆነ ሰውም እዛ ግጭት ውስጥ እንደተሳተፈ እና ተይዞ እንዳለ ማረጋገጥ ችለናል።ከዚያም ባለፈ የሶማሌ ሚሊሻዎች በዚህ አይነት ግጭት ውስጥ እየተሳተፉ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ከአሁን በኋላም ዜጎች ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የማድረግ ሁኔታ በሥርዓት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ እና ኦሮሚያ ክልል ላይ እየሔደ ያለው ሁኔታ ነገ ተባብሶ ወደ ሌላ አቅጣጫ የማይሔድበት፤ሌሎች ዜጎች ላይ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ላይ የማይደርስበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም።"

ሁለቱ ክልሎች ከሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የቦረና ዞን ጫሙኪ የተባለ ቀበሌ እንዲሁም በባሌ ዞን ራይቱ ገልቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን የአይን እማኞች እና አቶ አዲሱ አረጋ ባለፈው ሳምንት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር።  የሁለቱን ክልሎች ወሰን የተሻገሩ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም የተደረሰ ሥምምነትን በመጣስ የሶማሌ ክልልን ሰንደቅ ዓላማ በአካባቢው አውለብልበዋል ሲል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወቅሷል።

በዛሬው ዕለት ደደር እና መርካራፉ በተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በአወዳይ ከተማ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። የፌድራል መንግሥት የድንበር ግጭቱን ሊያስቆም ይገባል የሚል መልዕክት የተደመጠባቸው ሰላማዊ ሰልፎች መካሔዳቸውን ያረጋገጡት አቶ አዲሱ ሁሉም ሰላማዊ ነበሩ ብለዋል።

"ሕዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት አለበት፤እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች የሚያደርሱት ጥቃት መቆም አለበት፤ የክልሉ መንግስት እና የፌድራል መንግስት ይኸንን ሁኔታ ሊያስቆምልን ይገባል የሚል አይነት መፈክሮች እንደነበሩ ነው የሰማሁት።"

የኦሮሚያ ክልል ከጋምቤላ፣ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰንባቸውን አብዛኞቹን አካባቢዎች አካሏል። ከሶማሌ ክልል ጋር ያለው የድንበር ወሰን በ1997 ዓ.ም. በተካሔደ በሕዝበ-ውሳኔ ቢወሰንም እስካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ድረስ ገቢራዊ አልሆነም። አቶ አዲሱ "ሰሞኑን እየተከሰተ ያለው ግጭት ከአስተዳደር ወሰን ጋር የተያያዘ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ አዲሱ የድንበር ግጭቶቹ ቢበርዱም ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ግን ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ በማድረግ ላይ ናቸው ያሉት አቶ አዲሱ ጥቃቱን ያደረሱ አካላት ማንነት እና ተልዕኮ ከክልሉ መንግሥት በተውጣጡ ባለሥልጣናት እየተጣራ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ