1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 2009

ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ሲሰማ ተጨባጭ ለውጥ ስለመምጣቱ ጠይቀዋል። የመንግሥት የጸረ-ሙስና ዘመቻ መልሶ እያስተቸው ነው። መንግሥት አርቅቆታል የተባለው አዲስ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ሌላው መነጋገሪያ ነበር።

https://p.dw.com/p/2i2Lr
Ethiopia State of Emergency Merkel (picture alliance / AP Photo)
ምስል picture-alliance/AP Photo

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአስር ወራት በላይ የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ቢወስንም በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ የነበረው ምላሽ ግን ቀዝቃዛ ሆኗል። ፌስ ቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛዎች ኃሳባቸውን ያሰፈሩ ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ውሳኔ በተጨባጭ የሚለውጠው ነገር ስለመኖሩ እርግጠኞች አይደሉም። 

የፌስ ቡክ ተጠቃሚው ኤርሚያስ አበራ "ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፣ ወዳልታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተመልሰናል ተብሏል።" የሚል ኃሳብ አስፍረዋል። ዮና ብር "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ የቀድሞው የቀርፋፋ ጊዜ አዋጁ ተመልሷል። ለውጥ የለውም" ሲል አስተያየቱን በፌስ ቡክ ገጹ ፅፏል። ሰማኸኝ ጋሹ አበበ በበኩሉ "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ የሚያመጣው ለውጥ ቢኖር ቀደም ሲል የሰላማዊ ሰልፍ  ፍቃድ ኮማንድ ፖስቱ ከልክሏል በሚል ይመካኝ የነበረው አሁን ሰላማዊ ሰልፉን ለማስተናገድ በቂ የፖሊስ ሀይል የለንም በሚል የሚተካ መሆኑ ነው።" ሲል አስፍሯል። 

አባ ዳራር የተባሉ ሌላ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው የአዋጁ መነሳት "ለኦሮሞ ህዝብ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ " የሚል ኃተታ አስነብበዋል። አባ ዳራር በይፋ አይታወጅ እንጂ ባለፉት 27 አመታት የኦሮሞ ሕዝብ በየአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ቆይቷል የሚል ሙግት ያነሳሉ። በእርሳቸው አባባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍጹም አልተነሳም። ለዚህም "ወታደሮች ህዝብን ማሰቃየትና ማስፈራራትና ማሰር አሁንም ቀጥሏል፤ የታሰሩት ወገኖቻችን አሁንም እስር ቤት እየማቀቁ ናቸው፤ አቶ በቀለ ገርባና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች በሙሉ ያለ ምንም ጥፋትና ወንጀል ፍትህን ተነፍገው ቂሊንጦና ማዕከላዊ እስር ቤቶች ተዘግተው አሉ፡፡" የሚሉት አባ ዳራር በፅሁፋቸው ማጠቃለያ "ታዲያ አዋጁ ተነሳ የተባለው በምን ስሌት ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጣለው በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች በኋላ ባለፈው መስከረም መገባደጃ ላይ እንደነበር አይዘነጋም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት "መልካም" የሚሉት ሌላው የፌስ ቡክ ተጠቃሚ አባቡ ረሺድ "የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነትን ለጊዜው ማረጋገጥ" ችሏል ብለዋል። የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚው አባቡ ኢትዮጵያን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ መገዛት ያንደረደራት ችግር "ምን መፍትሄ ተገኝቶለታል? በቀጣይ አለመረጋጋቱ ላለመመለሱ ምን ዋስትና አለ?" ሲሉ ይጠይቃሉ። አባቡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመጣው " መረጋጋት እና የህዝብ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ጉዳይ ምን ያህል ዘላቂ ነው?" የሚል ሁለተኛ ጥያቄም አላቸው። 

በኢትዮጵያ መንግስት ተቺዎች እና ተቃዋሚዎች ዘንድ በእርግጥም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በአገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ አንዳች ለውጥ ለማምጣቱ ጥርጣሬ ይታያል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁም በፊት ሆነ በኋላ "የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይፈፅማል፤ካለ ፍርድ ተቃዋሚዎቹን ያስራል" የሚሉት ተቺዎች ዘንድ ይኸው ድርጊት ይቀጥላል የሚል ሥጋት ይንጸባረቃል። 

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ልክ የዛሬ ሳምንት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት "21,109 ተጠርጣሪዎች የተኃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ" መቀላቀላቸውን ተናግረዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም በበላይነት ይመራ የነበረው የኮማንድ ፖስት ዋና ተጠሪ የነበሩት አቶ ሲራጅ በምክር ቤቱ የተናገሩት ተጨማሪ ነገር ግን ለማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ሌላ የመወያያ ርዕሰ-ጉዳይ ነበር። አቶ ሲራጅ እንዳሉት "ብጥብጥ እና ሽብር በመፍጠር" የተጠረጠሩ 7737 ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ችሎት ላይ ናቸው። 

አቶ ውብሸት ሙላት የተባሉ የሕግ ባለሙያ በፌስ ቡክ ገፃቸው  "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ፣ በአዋጁ መሠረት የተከሰሱት ሰዎችስ?" የሚል ጥያቄ አንስተዋል። በሕግ ባለሙያው ትንታኔ መሰረት "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል ማለት አዋጁም መመሪያም ተሽረዋል ማለት ነው፡፡ በተለይም ከእነዚህ 7737 ተከሳሾች ውስጥ የተከሰሱበት ወንጀል ሙሉ በሙሉ አዋጁ ወይንም መመሪያው ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ የተከሳሾቹም ይሁን ጥፋተኛ የተባሉት ሰዎች ዕጣ ፋንታ ምን መሆን አለበት?" ሲሉ ጠይቀዋል። 

Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

አነጋጋሪው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ረቂቅ

ወደ ትዊተር ጎራ ስንል የኢትዮጵያ መንግሥት አዘጋጅቶታል የተባለው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ረቂቅ ሌላው መነጋገሪያ ነበር። ጦማሪው እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ኃይሉ በግል የትዊተር ገፁ የኢትዮጵያ መንግሥት አርቅቆታል የተባለው አዲስ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ተጠርጣሪዎችን ማሰቃየትን እንደ አንድ የምርመራ ዘዴ ፖሊሶች እንዲጠቀሙ ፈቃድ እንደሚሰጥ ፅፏል። ከፅሁፉ ጋር በፍቃዱ ያጋራው የረቂቁ ነው የተባለ አንድ ገፅ ፎቶግራፍ ላይ "አንቀፅ 109 በልዩ የምርመራ ዘዴ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ከፍርድ ቤት ወይም ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተፈቀደለት ሰው በተፈጸመ ወንጀል ማስረጃ ለማሰባሰብ የወንጀል ድርጊት መፈጸም ወይም መሳተፍ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ኃይል ለመጠቀም ይችላል።" የሚል ፅሁፍ ይገኝበታል።  በፍቃዱ እንደሚለው "በረቂቅ ሥነ ስርዓት ሕጉ መሠረት "ልዩ የምርመራ ዘዴ" (ቶርቸር) የተፈቀደላቸው ፖሊሶች ማድረግ የማይችሉት ነፍስ ማጥፋትና አስገድዶ መድፈር ብቻ ናቸው።" ጠበቃ ሻሹ ገብረሕይወት ታዲያ በረቂቅ የስነ-ሥርዓት ሕጉ ትርጓሜ ላይ ከበፍቃዱ ጋር ፈፅሞ አይስማሙም።  ሻሹ "ማስረጃ እሚገኝበት ሌላ መንገድ የሌለ እንደሆነ ፖሊሶች ወንጀለኛ መስለው ተጠርጣሪዎች ጋር ወንጀል ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ነው ይህ አንቀፅ እሚያሳየው።" ሲሉ ይሞግታሉ። በሻሹ ትንታኔ "...ሃይል ለመጠቀም ይችላል" የሚለው የረቂቅ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ክፍል ምርመራውን የሚያካሒዱት ወገኖች "የሚጠቀሙት ሃይል የወንጀሉ ተሳታፊ ናቸው የተባሉት ሰዎች ላይ ሳይሆን እየተፈፀመ ያለው የወንጀል ድርጊት ላይ ስለሚጠቀሙት ሃይል ነው።" አብርሐም ኤቢ የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ "አንድ ህግ ሲወጣ እንዴት አሻሚ በሆኑ ቃሎች ተለባብሶ ይቀርባል ?ሲሉ ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠርጣሪዎችን ሐብት አገደ 

Symbolbild Korruption Handschellen auf US Dollar
ምስል Fotolia/ia_64

ጋዜጠኛ አንሙት አብርሐም እና የበለጸገች ኢትዮጵያ የተ​​​​​​​ባለ የፌስቡክ ገፅ መንግሥት በሙስና የተጠረጠሩ የግል ኩባንያዎች ፤ ባለሥልጣናት እና ባለሐብቶችን ንብረቶች ማገዱን በፌስቡክ ፅፈዋል። ጋዜጠኛው አንሙት በግል ገፁ ባሰፈረው መልዕክት እንደሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ያገደው የ"8 ኩባንያዎችና 200 የሙስና ተጠርጣሪዎች ባለስልጣናትና ባለሀብቶች (ቤተዘመድ ጭምር) ንብረት እና ሐብት" ነው። 

ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ በስኳር ኮርፖሬሽን የመስኖና ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ ይገኙበታል።

በራሱ ሹማምንት ላይ የዘመተው የኢትዮጵያ መንግሥት የጸረ-ሙስናው ዘመቻ መልሶ ራሱን ያስወቅሰው ይዟል። "እንደኔ እንደኔ " ይላል "የስልጣን-ሙስና ከገንዘብ-ሙስና እጅጉን ይልቃል!" በሚል ርዕስ ትችቱን በፌስ ቡክ ያሰፈረው አናንያ ሶሪ። አናንያ "በህዝብ ስልጣን ላይ ጉዳት ያደረሱ ቱባ ባለሥልጣናት ከስልጣን ይውረዱ፤ እስከዛሬ ለመዘበሩት ደግሞ ህግ እንደሚገባው ይቅጣቸው።" ሲል መረር ያለ ትችቱን አስፍሯል። ጆማኔክስ ካሳዬ በበኩሉ "ለእኛ ከሾው ውጪ የሚተርፈን ነገር የለም ፣ የተቀሩት (የተረፉት) ታማኝነታቸውን ያድሳሉ ።" ብሎ ነበር። ዘላለም ክብረት ታዲያ "ከፀረ ሙስና ትግሉ ለኩሩውና ምስኪኑ የኢትዬጵያ ህዝብ የሚተርፍለት ነገር ቢኖር ዜና ብቻ ነው" የሚል ፅሁፍ ለመፃፍ እያሰብኩ ነው" ሲል ለጆማኔክስ መልሶለት ነበር። ፖለቲከኛው አብርሐ ደስታ ደግሞ "ፖለቲካ 101፡ የኢህአዴግ ባለስልጣንን ማሳሰር ስትፈልግ 'ሙስና' አለልህ፤ የተቃዋሚ አመራር አባልን ማሳሰር ስትፈልግ ደግሞ 'ሽብር' አለልህ። ባለስልጣንን በሙስና ለመክሰስ ማስረጃ አታጣም፤ ተቃዋሚን በሽብር ለመክሰስ ማስረጃ አትጠየቅም።" ሲል ተችቷል። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ