1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሸነፉ፤ ሜርክል ድጋሚ ተሳካላቸው!

እሑድ፣ መስከረም 14 2010

የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ለመራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትምህርት ሰጥቶ ነው ያለፈው። 32 ከመቶ ድምጽ በማግኘት ፓርቲያቸው (CDU) ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት (እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ከነበረው ውጤት ዐሥር በመቶ የመራጭ ድምጽ አጥቷል።

https://p.dw.com/p/2kcfp
Angela Merkel
ምስል picture alliance/dpa/AP Photo/M. Schreiber

የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ለመራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትምህርት ሰጥቶ ነው ያለፈው። 32 ከመቶ ድምጽ በማግኘት ፓርቲያቸው (CDU) ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት (እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ከነበረው ውጤት ዐሥር በመቶ የመራጭ ድምጽ አጥቷል። እናም ፓርቲያቸው አዲስ በሚመሰረተው ምክር ቤት ውስጥ አምስት ሳይሆን ስድስት ፓርቲዎች ይጠብቋቸዋል። እናም የፖለቲካ ፉክክሩ ጠንከር ሳይልባቸው አይቀርም። መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን (AfD) ፓርቲም በምክር ቤቱ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጠንካራ ተፎካካሪ በመኾን ራስ ምታት መፍጠሩ አይቀርም። ይኽ ሁሉ ተደማምሮ ለመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከፍ,ተኛ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም። ከምንም በላይ ግን ከዛሬው ምሽት የምርጫ ውጤት በኋላ አንድ ነገር ጎልቶ መውጣቱ አይቀርም። መራኂተ መንግሥቷ ግልጽ በሆነ መልኩ በርካታ ድምፆችን ሊያጡ ይችላሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ዘና ብለው መቀጠሉ የተመቻቸው ይመስላል። ከባየርኑ ክርስቲያን ሶሻሊስት ጋር ተጣማሪ የሆነው ፓርቲያቸው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1949 አንስቶ ከፍተኛ ሽንፈት ቢገጥመውም ማለት ነው።  

Binz Wahlkampf CDU - Merkel
ምስል Reuters/A. Schmidt

«ጃማይካ ጥምረት» 

በጀርመን ምርጫ ውጤት መሰረት አዲስ መንግሥት የሚመሰረተው የተለያዩ አሸናፊ ፓርቲዎች ተደራድረው ከተጣመሩ በኋላ ነው። አንድ ብቸኛ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭ ኾኖ እንዲገዛ አይፈቀድለትም። ዘንድሮ ጀርመን፦ «የጃማይካ ጥምረት» ሊገጥማት ይችላል ተብሎ ተገምቷል። «ጃማያክ ጥምረት» ጀርመን እንደ ኢትዮጵያ ከጃማይካዎች ጋር የተለየ ትስስር ኖሯት አይደለም። እንደ ሻሸመኔ ለጃማያካዎች የተሰጠ ሥፍራ በጀርመን ኖሮም አይደለም። ታዲያ «ጃማይካ ጥምረት» ቃሉ ከወዴት መጣ? በጀርመን እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱ መለያ ቀለም አለው። የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረትና የባየርኑ ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት ጥምረት መለያው ጥቁር ነው። የነጻ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ መለያ ቀለም ቢጫ እንዲሁም የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መለያ አረንጓዴ ቀለም በአንድነት ጥቁር፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለም ቅልቅል ይፈጥራል። ልክ እንደ ጃማይካ ባንዲራ ማለት ነው። «ጃማይካ ጥምረት»ቃሉ የመጣውም ከዚህ ነው።

ፎልከር ቫግነር/ማንተጋፍቶት ስለሺ