1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለዉ ግድያና ማፈናቀል።

ረቡዕ፣ ሰኔ 6 2010

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዘርን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ጥቃትና መፈናቀልን ለማስቆም መንግስት ርምጃ እየወሰደ አይደለም ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ።ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣዉ መግለጫ በሳምንቱ መጨረሻ በሶማሌ ክልል ጭናክሰን ወረዳ 14 ሰዎች መገደላቸዉንና ከ20 በላይ መቁሰላቸዉን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/2zUz7
Logo von Amnesty International

Ethiopian not doing enough to stop Ethnic violence ,Amnesty - MP3-Stereo

መንግስት በአሁኑ ወቅት እያደረገ ካለዉ  የማሻሻያ ርምጃ ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት አድርገዉ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን  ማዉገዝና ማስቆም አለበት ሲልም የድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣዉ መግለጫ ባለፈዉ ሰኔ 8 ቀን ብቻ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ  በጭናክሰን ወረዳ  ቆቦ ቢካ ፣ኡልኑላ እና ዋልኑስ በተባሉ ቦታዎች 3 ሰዎችን ሲገደል፤ ሌሎች 3 ሰዎች መቁሰላቸዉን ገልጿል። 
ይህ ጥቃት በማግስቱ  ቀጥሎ ደርቢጋ እና ጎለልቻ በተባሉ ቦታዎችም 7 ሰዎች ሲገደሉ 17 መቁሰላቸዉን  በዘገባዉ አመልክቷል።ያም ሆኖ ግን የፌደራሉ ይሁን የክልሉ መንግስት  ይህ ሀይል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፅመዉን ግድያ የሚያስቆም ርምጃ አለመወሰዱን ድርጅቱ ተችቷል። 
የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት መንግስት የድርጊቱን ፈፃሚዎች በህግ ተጠያቂ ባለማድረጉ በሳምንቱ መጨረሻም በአካባቢዉ ሌላ ጥቃት ተፈፅሟል።

«14 ሰዎች ተገድለዋል።እዛዉ ጭናክሰን ዉስጥ ባሉ አጎራባች ቀበሌዎች በጣም ብዙ ሰዎች ናቸዉየቆሰሉት።በ 20 ዎቹ ዉስጥ ያሉ ሰዎች ቆስለዋል።ድርጊቱን የፈፀሙት የሶማሌ ክልል የልዩ  ፖሊስ ነዉ።ልዩ ፖሊስ በክልሉም ይሁን ከክልሉ ዉጭ በመሄድ የሰብዓዊ መብት በመፈፀም የታወቀ ነዉ ።እና እስካሁን ድረስ ምንም ተጠያቂ ተደርጎ አያዉቅም።ለፍርድ ሲቀርቡ አይታይም።ስለዚህ በድርጊታቸዉ እንዲቀጥሉ የልብ ልብ የሰጣቸዉ ይመስለኛል » በማለት ነዉ የገለፁት።
የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ከህግ በላይ እንዲሆን መፈቀድ የለበትም ያለዉ መግለጫዉ እየተፈፀሙ ያለዉ ግድያና ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆምና ምርመራ እንዲካሄድ ድርጅቱ ጥሪ አቅቧል።ጉዳዩን በተመለከተ የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮምኒኬሽን ፅ/ቤት ሀላፊን አቶ ኢድሪስ ሀሰንን በስልክ ያነጋገርናቸዉ ቢሆንም  «ጥቂት ቤቶች ተቃጥለዋል» ከሚል አጭር ምላሽ ዉጭ ዝርዝር መረጃ ሊሰጡን አልፈቀዱም።
ድርጅቱ ባለፈዉ ዓርብ ባወጣዉ ሌላ ዘገባም ከኦሮሚያና ከቤንሻንጉል  ክልል  ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ የአማራ ተዎላጆች ጉዳይ፤ እንዲሁም በምዕራብ ጉጅና  ጌዲዩ  ዞኖች በተቀሰቀሰ ግጭት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ ዕልባት አለማግኘቱን ገልጿል። በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፣ኢሉ አባቦራና ቡኖ በደኖ አካባቢ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ጉዳይም አሳሳቢ መሆኑን አቶ ፍስሃ አብራርተዋል። 
ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች  ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና መፈናቀል ቢቀጥልም መንግስት በተገቢ ሁኔታ ድርጊቱን ባለማዉገዙ  ባለፈዉ መስከረም ከሶማሌ ክልል ብቻ ወደ 1 ሚሊዩን የሚጠጉ ሰዎች ከመፈናቀላቸዉ በተጨማሪ  በተለያዩ አካባቢዎች ማንነት ተኮር ጥቃት አሁንም ድረስ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለዉን የማሻሻያ ርምጃ የተሟላ ለማድረግ በማንነት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ላይም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አቶ ፍስሃ አሳስበዋል።
«መንግስት እንግዲህ በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት።እነዚህ ሰዎች በሀገራቸዉ ተዟዙረዉ መስራት አልቻሉም።የፈለጉበት ቦታ ላይ መኖር እስካልቻሉ ድረስ «ሪፎርም»ወይም የማሻሻያርምጃ የተሟላ አይሆንም።ስለዚህ ድርጊቱን ማንም ይፈፅመዉ ድርጊቱን በግልፅ ማዉገዝ ያስፈልጋል።መንግስት ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን ከማዉገዝ ባለፈም ለህግ ማቅረብ አለበት። »ነዉ ያሉት።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሚንኬሽን ፅ/ቤት ሀላፊን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም መልስ ልናገኝ አልቻልን።

Karte Sodo Ethiopia ENG

ፀሀይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ