1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚዳንት ያሕያ ጃሜህ ሽንፈታቸውን ተቀበሉ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 24 2009

ጋምቢያን ለ22 ዓመታት የመሩት ያሕያ ጃሜሕ የምርጫ ሽንፈታቸውን ተቀበሉ። ትናንት ምሽት በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ያሕያ ጃሜሕ ለአሸናፊው አዳማ ባሮው የእንኳን ደስ አለዎ መልክት አስተላልፈው ሥልጣናቸውን በሰላም እንደሚያስረክቡም ቃል ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/2ThDK
Yahya Jammeh
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ጋምቢያን ለ22 ዓመታት የመሩት ያሕያ ጃሜሕ  ሽንፈታቸውን ተቀበሉ። በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት ለተፎካካሪያቸው አዳማ ባሮው በተንቀሳቃሽ የእጅ ሥልካቸው የደወሉት ጃሜሕ ምርጫውን አሞግሰው በውጤቱ ላይም እንደማይከራከሩ ቃል ገብተዋል። «አላህ ጊዜዬ ማብቃቱን እየነገረኝ ነው» ያሉት ጃሜሕ፤ ሥልጣናቸውን ለ22 ዓመታት እንደ ብረት ቀጥቅጠው ላስተዳደሩት የጋምቢያ ሕዝብ በክብር እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል።

የጋምቢያ የምርጫ ኮሚሽን አዳማ ባሮው 45 በመቶ ፕሬዚዳንቱ ያሕያ ጃሜሕ ደግሞ 36 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን አስታውቋል። ውጤቱ በይፋ ከተገለጠ በኋላ በአደባባዮች የተለጠፉ የጃሜሕ የምረጡኝ ዘመቻ ማስታወቂያዎች ወታደሮች ፊት የተቀደዱ ሲሆን፤ «ነፃነት ነፃነት ነፃነት» የሚሉ መፈክሮችም ተደምጠዋል። ተመራጩ አዳማ ባሮው ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ለብሔራዊ አንድነት እና ኤኮኖሚያዊ እድገት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል። አዳማ ባሮው ገለልተኛ ፍርድ ቤት እንደሚያቋቁሙ፤ የመገናኝ ብዙኃን ነፃነት እንደሚያበረታቱ እና የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን በሁለት ዙር እንደሚገድቡም ተናግረዋል።

ያሕያ ጃሜህ የምዕራብ አፍሪቃዋ ጋምቢያን «ለቢሊዮን ዓመታት እመራታለሁ» ሲሉ  የዛሬ አምስት ዓመት ተናግረው ነበር።  

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ