1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀምቡርግ፤ የቡድን ሃያ ሃገራት ጉባኤ ተጀመረ

ዓርብ፣ ሰኔ 30 2009

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ቡድን የሃያ ሃገራት የሁለት ቀናት ጉባኤ ዛሬ በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ተጀመረ። የአስተናጋጇ ሀገር የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጉባኤዉ ተሳታፊ የመንግሥታት መሪዎችን ከተቀበሉ በኋላ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ይህ ስብሰባ በዓለም ላይ ለሚታየዉ ችግር መፍትሄ ያፈላልጋል ብሎ እንደሚጠባበቅ አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/2gAqu
Deutschland G20 Gipfel Retreat Sitzung
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

 እንዲያም ሆኖ ከዚህ ጉባኤ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለዉ መሪዎች በሚያደርጉት ዉይይት ሰጥቶ ለመቀበል ፈቃደኞች ከሆኑ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ጉባኤዉ ከሚነጋገርባቸዉ እና ሜርክል የጋራ መግባባትን ለማግኘት ከሚጥሩባቸዉ ነጥቦች አንዱ የአየር ንብረት ለዉጥን የተመለከተዉ ነዉ። በጉባኤዉ ላይ የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራት ፓሪስ ላይ የተስማሙበትን የአየር ንብረት ስምምነት ሀገራቸዉ እንደማትቀበል ማስታወቃቸዉ ይታወሳል። ከጉባኤዉ ቀደም ብለዉ ሜርክል ከቡድን ሃያ ሃገራት መሪዎች ጋር በስብሰባዉ አጀንዳዎች ላይ መነጋገራቸዉ ተገልጿል። የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጉባኤዉ በወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገር፤ ሀገራቸዉም ሚናዋን በሚገባ እንደምትወጣ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

«በቡድን ሃያዉ ጉባኤ ላይ ሚናችንን ሙሉ በሙሉ እንወጣለን፤ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይም እንነጋገራለን። መራሂተ መንግሥት ሜርክል የመወያያ አጀንዳዉን ፊት ለፊት በማስቀመጣቸዉ፤  መሪዎችም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዉ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ላይ በመነጋገራቸዉ በጣም አስደስቶኛል። ብንወያይበት የሚያስፈልገን ሽብርን በገንዘብ መደገፍን እንዴት መታገል እንዳለብን ነዉ።»

Deutschland Hamburg - G20 Proteste
ምስል Getty Images/AFP/O. Andersen

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጉባኤዉ በሚካሄድባት ከተማ ሀምቡርግ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዉ ተባብሷል። የቡድን ሃያ ጉባኤ ከመጀመሩ አስቀድሞ በርከት ያሉ መኪናዎች በእሳት ጋይተዋል። ለተቃዉሞ ከተደራጁት ቡድኖች ጋር በተደረገ ግጭትም ከ30 የሚበልጡ ፖሊሶች መጎዳታቸዉ ተነግሯል። ተቃዉሞ ለመቆጣጠር የሀምቡርግ ፖሊስ ከመላዉ የጀርመን ግዛት ተጨማሪ ኃይል ጠይቋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ