1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀዘንና ምሬት፤ የመገናኛ ብዙኃን ትችት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 7 2008

ከፓሪሱ ጥቃት በኋላ የዓለም ህዝብ የተሰማውን ሀዘን እና ለፈረንሳይ ያለውን ትብብር አሳይቷል። ይሁንና እንደ ቦኮ ሀራም እና አሸባብ ያሉ ቡድናት በተደጋጋሚ አፍሪቃ ውስጥ ጥቃት ሲጥሉ ለምን የዓለም የመገናኛ ብዙኃን እንደ ፓሪሱ ጥቃት በስፋት አልዘገቡም?

https://p.dw.com/p/1H7Mv
Deutschland Urteil im Wulff-Prozess wird erwartet Übertragungswagen in Hannover
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

«2000 ሰዎች ናይጄሪያ ውስጥ ሲሞቱ ምንም አልተባለም። በስደት ላይ ያሉ ወላጆች እና ልጆቻቸው ሲሞቱ ምንም አልተባለም» ይላሉ በምዕራባዊያን የመገናኛ ብዙኃን መብሸቃቸውን የገለፁት አንጎላዊ ሲሞና ሞራይስ ፤የፖርቹጋሊኛው ክፍል የፌስ-ቡክ ገፅ ላይ « አሁን 129 ሰዎች ሲሞቱ ዓለም ያለቅሳል፤ ሀዘን እና ትብብር ላይ ያለው ልዩነት ምን ያህል ብዙ ነው» ሲሉ አስተያየታቸውን ፅፈዋል። ይህ አስተያየት የበርካታ አፍሪቃውያንን ስሜት ያንፀባርቃል። የአማርኛው የፌስ-ቡክ ገፅ ላይ ያህያ ዜኮ የተባሉ የዶይቸ ቬለ ተከታታይ « ሶርያ ውስጥ በየዕለቱ ከ 300 በላይ ሰዎች ይሞታሉ፤ የእነሱም ደም ቀይ ነው» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ብዙዎች በጋዛ፣ ሶርያ ፣ኢራቅ እና ሶማሊያ የደረሱ የሽብር ጥቃቶች ትኩረት ሲያገኙ አለማየታቸው አስቆጥቷቸዋል። ቡሩንዲያዊው « የግሎባል ፎረም» ዳሪክተር ዳቪድ ጋኩንዚ አፍሪቃውያን በማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን የሚፅፉትን የምሬት ስሜት በደንብ እረዳለሁ ይላሉ።« ለምሳሌ በኬንያ የጋሪሳ ዮንቨርስቲ ጥቃት የተጣለ ጊዜ ከ 200 በላይ ተማሪዎች ተገድለዋል። የዓለም አቀፉን እንቅስቃሴ የተመለከትን እንደሁ በጥር ወርም ይሁን አሁን ፓሪስ ላይ እንደሚታየው ከፍተኛ አልነበረም። አሁን ድረስ በእጆቹ ስር የሚገኙትን ልጃገረዶች ቦኮ ሀራም ያገተ ጊዜም ቢሆን የዓለም አቀፉ አስተያየት እንደ ፓሪሱ የተጧጧፈ አልነበረም። »

Kenia Studenten trauern um Garissa-Kommilitonen 07.04.2015
ምስል picture-alliance/AP/Ben Curtis

ይላሉ ሳይንቲስቱ በእርግጠኝነት። እንደ እሳቸው ከሆነ ዓለም በመልከአ ምድር እና በፖለቲካ የተከፋፈለች ናት። በዚህም መሠረት የዓለም ማዕከል የሆኑ እና ድንበር ላይ የሚገኙ አሉ። ስለዚህ የዓለም ማዕከል ካልሆኑ ደግሞ ሌሎች የእነሱን ያህል የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አያገኙም በማለት ሁኔታውን ይገልፃሉ።«ይህ የዓለማችን እውነታ ነው» የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን የአለማችንን መልከአ ምድራዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነትን ነው የሚያንፀባርቁት። ስለዚህ እውነታውን በማቅረብ ላይ የሚፈጸም ልዩነት ሳይሆን የመልከአ ምድሩ ፖለቲካችንን የሚያንጸባርቅ ነው።»

ዳቪድ ጋኩንዚ በርዋንዳ የተካሄደው የዘር ጭፍጨፋ ምዕራባዊያን ዘንድ እስኪደርስ ምን ያህል እንደቆየ አስታውሳለሁ ይላሉ። አሁን አሁን በርካታ ወጣት አፍሪቃውያን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር በቀላሉ ተገናኝተዋል። ናይጄሪያ እና ኬንያ ብቻ 20 ሚሊዮን የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ይገኛሉ። ከሌላው የዓለማችን ክፍል ጋር የሚገናኙበት ቴክኖሎጂ አለ ይሁንና ግንኙነቱ ግን ልክ እንደ ባቡር ሀዲድ ነው ይላሉ ጋኩንዚ፤«የዚህች ዓለም ተካፋይ የሆኑ ወጣቶች አፍሪቃ ውስጥ አሉ። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። የዓለም ባህል አንድ አካል ናቸው። የዓለም አቀፉ ባህል አካልም ናቸው። አንድ አንዴ እንደውም የዚህች የተሳሰረች ዓለም ዜጋ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ጋኩንዚ የአፍሪቃ ሀገራቱ ራሳቸው ሊለውጡት የሚችሉት አለ ይላሉ። ይህም ሀገራቱ ጠንካራ እና የተረጋጋ ዲሞክራሲ በሀገራቸው ካሰፈኑ የመገናኛ ብዙኃንን ጎልተው ሊያወጡ እና አህጉሯ በዓለም አቀፍ ዘንድ ያላቸውን ገፅታ ሊገነቡ ይችላሉ የሚል።

Themenbild Breaking News
ምስል DW

በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የተሰጡት አስተያየቶች ከጥር ወሩ ጥቃት ጋር ሲነፃጸሩ ይበልጥ ሀዘን የተንፀባረቀበት ነበር። በወቅቱ በቻርሊ ኤብዶ ምፀታዊ ጋዜጠኞች እና በአንድ የአይሁዳውያን የገበያ አዳራሽ ላይ ፈረንሳይ ውስጥ የደረሰው ጥቃት ሀዘን ብቻ ሳይሆን ሐይማኖታዊ ጥያቄዎች እና ትችቶችን አስነስቶም ነበር። በአንድ ነጥብ ላይ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ። ፓሪስ ወይም አፍሪቃ ላይ የደረሱት ጥቃቶች ከእስልምና ሀይማኖት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም በሚለው።

ቢርጊት ሞርገንራት/ ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ