1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁከት በደቡብ ሱዳን መጠለያ ጣቢያ

ቅዳሜ፣ የካቲት 12 2008

በደቡብ ሱዳን የ«አፐር ናይል» ግዛት ዋና ከተማ ማላካል በሚገኘው የተመድ መጠለያ ጣቢያ ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ። የርዳታ ድርጅቶች እንዳስታወቁት፣ በዚሁ ባለፈው ረቡዕ፣ የካት ስምንት፣ 2008 ዓም ሁከት ሁለት ደቡብ ሱዳናውያን የድንበር የማይገድበው ድርጅት ሰራተኞችም ተገድለዋል። ከ30 የሚበልጡም ቆስለዋል።

https://p.dw.com/p/1HypT
Südsudan UN-Schutz Flüchtlinge in Malakal
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

[No title]

በዚሁ ጣቢያ በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን ሪየክ ማቸር ከስልጣን ባሰናበቱበት ጊዜ የተቀሰቀሰውን የርስበርስ ጦርነት የሸሹ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን አስጠልሎዋል። የሰሞኑ ግጭት በዚያው በመጠለያ ጣቢያ በሚኖሩ ተፈናቃዮች መካከል መነሳቱን እና የመንግሥት ጦርም ሆነ ያማፅያኑ ተዋጊዎች እንዳልተሳተፉበት በደቡብ ሱዳን የተመድ ተልዕኮ፣ በምህፃሩ «አንሚስ» ኃላፊ አሪያን ክዌንትየ ለዶይቸ ቤለ ገልጸዋል።
« ተኩሱ ከመጠለያ ጣቢያው ውጭ ሳይሆን በዚያው በመጠለያው ጣቢያ ውስጥ ነው የተጀመረው። በዚሁ ጣቢያ ውስጥ የተመድ ተልዖኮ ከለላ የሰጣቸው ወደ 47,000 የሚጠጉ የተለያዩ የጎሳ አባላት ይገኛሉ። ውጊያው ባለፈው ረቡዕ በሺሉክ እና በዲንካ ጎሳ ወጣቶች መካከል ነበር የተጀመረው። በቆንጨራ እና በሌሎች ቀላል የጦር መሳሪያ ወጣቶቹ የተገዳድሉበት ግጭት የተካሄደው በመጠለያው ጣቢያ ውስጥ ነው። »«አንሚስ» በደቡብ ሱዳን በከፈታቸው ስድስት ጣቢያዎች በጠቅላላ 198,440 ከለላ ሰጥቶዋል።

«አንሚስ» ወዲያው ጣልቃ የገባበት ርምጃ ሁከቱ እንዳይባባስ መርዳቱን የተልዕኮው ኃላፊ ገልጸዋል።
«በመጠለያ ጣቢያው ጸጥታ እና ስርዓት የሚያስጠብቀው የ«አንሚስ» ፖሊስ ተቀናቃኞቹን ወገኖች በሚያስለቅስ ጢስ ከመበተኑም በላይ የጣቢያውን እና ያካባቢውን ጥበቃ በጦር ኃይሉ አማካኝነት አጠናክሮዋል።»

Südsudan Rebellenführer Riek Machar
ያማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸርምስል Reuters/G. Tomasevic

ተልዕኮው ፍፁም አዲስ ያልሆነውን ይህን ዓይነቱን ግጭት ለማስወገድ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ክዌንትየ አስታውቀዋል።«አንሚስ» ግጭቱን ለማብረድ እና ውጥረቱን ለማርገብ ፣ እንዲሁም፣ በጣቢያው ሰላም እንደገና እንዲሰፍን ስለሚቻልበት ጉዳይ በወቅቱ ካካባቢው ባለስልጣናት ጋር ምክክር ጀምሮዋል። ይህ ዓይነቱ ግጭት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የታየ ቢሆንም፣ አሁን የተባባሰበትን ምክንያት ለመረዳት አልቻልንም፣ በመሆኑም፣ ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንገኛለን።»

የተልዕኮው በደቡብ ሱዳን የርስበርሱ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ የሀገሪቱ ዜጎች ትውልድ ቦታቸውን ለቀው ሸሽተዋል። ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ያማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ባለፈው ነሀሴ የርስበርሱን ጦርነት ለማቆም በአዲስ አበባ ስምምነት ከተፈራረሙ እና ባለፈው ጥርም በብሔራዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት ውስጥ ስልጣን ለመከፋፈል ከተስማሙበት መሰረት ሪየክ ማቸርን ከጥቂት ቀናት በፊት እንደገና ምክትል ብለው ሰይመዋል።

አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ