1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃያኛዉ ዓምት የጀርመን ዉሕደት-ገንዘብ እና የተስፋ ቃል

ዓርብ፣ መስከረም 21 2003

አንድ የአሜሪካ ታወቂ የንግድ ድርጅት ተጠሪ ከጥቂት አመታት በፊት የቀድሞዉን የገንዘብ ሚኒስትር ቴዎ ቫይግልን፣ «ምስራቅ ጀርመንን መግዛታችሁ» የተሳሳተ ንግድ ሳይሆን አልቀረም በማለት ጠይቀዋቸዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/PPhv
የምሥራቅ የሕብረት ሥራ ማሕበርምስል dpa ZB-Fotoreport

«የሚያብብ እና የሚበለጽግ ሐገር» ሲሉ ነበር የቀድሞዉ የጀርመን መራሄ መንግስት ሄልሙት ኮል ከጀርመን ዉህደት በኋላ ስለ ቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ቃል የገቡት። ምስራቅ ጀርመንን ለመገንባት እስከ ዛሬ ድረስ የፈሰሰዉ ወጪ 1.3 ትሪሊዮን ዩሮ ሲሆን ገና ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል።

የምዕራብ ጀርመን ቱሪስቶች በቀድሞዋ የምስራቅ ጀርመን አካባቢዎች ሲዘዋወሩ ስለሚታየዉ ጥሩ ስለታደሰዉ ህንጻ እና ቤት፣ ለጥ ስላለዉ አስፋልት እና የእግረኛ መንገዶች ጥራት፣ በአጠቃላይ ስለሚታየዉ ዘመናዊ መሠረተ-ልማት ይደነቃሉ። በርግጥም ምንም እንኳ የምስራቁን ክፍል ለመለወጥ የተጀመረዉ ግንባታ ብዙ ጊዜ ቢወስድም ከሃያ አመታት በኋላ ብዙ ነገሮች መለወጣቸዉ እና መሻሻላቸዉ ጥርጥር የለዉም። እ.ጎ.አ 1990 አ.ም ህዳር ወር ላይ፣ በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን በተደረገ የመጀመርያ የነጻ ምርጫ፣ አሸናፊ የሆኑት ፕሪዝደንት ሎታር ደ ሜዜር «ለዉጡ እና ግንባታዉ ብዙ ጊዜ አይወስድም ብለን አስበን ነበር፣ ቢሆንም አሁን የቀድሞ ምስራቅ ጀርመን እያደገ እና እያበበ መሆኑ ግልጽ ያልሆነለት ሰዉ፣ ማየት የማይችል እዉር አልያም ደደብ መሆን አለበት» ይላሉ። በመቀጠልም «በአሁኑ ጊዜ በዛክሶንያ ክፍለ-ግዛት በምትገኘዉ ጎርሊትዝ አድርጌ በቱሪኒጊያ ግዛት ወደ ምትገኛዋ ክዊድሊንቡርግ ከተማ እና ሌሎች ከተሞች ስዘዋወር፣ አካባቢዉ ምን ያህል እንደተለወጠ ማየቱ በጣም ያስደስታል» ብለዋል።

Bewerbung Görlitz für Kulturhauptstadt 2010
የጎርሊትስ መሐል ከተማምስል picture-alliance/ ZB

ዛሬ የጀርመን ዉህደት ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣ መገመት ብቻ ነዉ የሚቻለዉ። በሃለ ከተማ የሚገኘዉ፣ የኢኮነሚ ጥናት ተቋም ያቀረበዉ የጥናት ዘገባ እንደሚያሳየዉ፣ እ.ጎ.አ ከ1991 እስከ 2009 ድረስ 1.3 ትሪሊዮን ዩሮ በጀት ለዉህደቱ ወጭ ሆንዋል።ይህ በጀት በቀጥታ አዲስ ለተመሰረቱት የጀርመን ግዛት መንገዶች፣ ለአዉራጎዳናዎች፣ ለዉሃ ቧንቧ መስመሮች መዘርጊያ እና ለእድሳት ስራዎች ዉሏል።

Umweltverschmutzung in Bitterfeld
ዛክሰን-አንሐልት ክ-ግዛት ከቢተርፌልት ኬሚካል ኢንዱስትሪ አጠገብ የሚገኝ ቁሻሻ መጣያምስል AP

ሥራ አጥነትን ለማቃለል የተደረገ ወጪ

በቀድሞ ምስራቅ ጀርመን፣ የወደቀዉን የመሠረተ-ልማት ለማሻሻል የተደረገ ወጪ ብቻ ሳይሆን፤ በወቅቱ በመንኮታኮት ላይ የነበሩት ፋብሪካዎችና እና አምራች ድርጅቶች እንዲያሰራሩ ለመደገፍ የተደረገዉ ወጪም ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል በወቅቱ አምራች ድርጅቶች ተንኮታኩተዋል፤ በዚህም ምክንያት በምስራቁ ክፍል የስራ አጡ ቁጥር በሚያስደነግጥ መልኩ ጨምሮአል። በዚህም ወጭ ከተደረገዉ 1.3 ትሪሊዮን ዩሮ መካከል ሁለት ሶስተኛዉ ለማህበራዊ ኑሮ ድጎማ መዋል ነበረበት።አሁንም ቢሆን በምስራቁ ክልል ያለዉ የሥራአጥ ቁጥር ከምዕራቡ ከፍ ብሎ ይገኛል።
ምስራቅ እና ምዕራብ ጀርመን፣ እ.ጎ.አ 1990 ከሰኔ 1 ቀን ጀምሮ፣ የገንዘብ፥ የኢኮነሚ እና የማህበራዊ ኑሮ ዉሕደት መጀመሩ፣ የምዕራቡ ማርክ የምስራቁም የመገበያ ገንዘብ መሆኑ፣ በአጠቃላይ እንዲህ በፍጥነት የጋራ ነገር ይከሰታል ብሎ ያሰበ አልነበረም። ሁኔታዉን የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች በደስታ ነዉ የተቀበሉት፣ ያምሆኖ የምስራቅ ጀርመን የኢኮኖሚ ይዞታ አስጊ ሁኔታ ላይ ወደቋአል። የጡረታ ገንዘብ እንዲሁም አንድ የምስራቅ ጀርመን ነዋሪ በጁ ላይ የያዘዉን እስከ 6 ሺሕ የሚደርስ የምስራቅ ጀርመን ማርክ በምዕራቡ ማርክ አንድ ለአንድ መቀየር ተፈቀዶለታል። መምስራቅ ጀርመን የሚገኙ የተለያዩ አሰሪ ድርጅቶችና ቀጣሪዎችም ለሰራተኞቻቸዉ በምዕራቡ የጀርመን መገበያያ ማርክ ደምወዝ መክፈል ጀመሩ። በዚህም ምስራቅ ጀርመን ከምዕራብ ጀርመን የጀመረችዉን ዉድድር በምዕራቡ ኢኮነሚ ያለምንም ድጋፍ በአንድ ሌሊት ተጋልጦ ቁጭ በማለቱ ምርጫዉ መሸነፍ ብቻ ነበር። በሌላ በኩል የምስራቅ ጀርመን ነዋሪ እዚያዉ ምስራቁ የተመረተ ምግብም ሆነ ሌላም ቴክኒካዊ ቁሳቁስ ላለመግዛት ወሰነ።

Währungsunion DDR D Mark DM Umtausch Flash-Galerie
የገንዘብ ዉሕደቱ ዕለት-ባል ሚስትና ልጅምስል picture-alliance/ ZB

የመገበያያዉ ገንዘብ አንድ መሆን አማራጭ የሌለዉ ነበር

የኢኮነሚ ጠበብት የሁለቱ ጀርመኖች የመገበያያ ገንዘብ አንድ መሆን የምስራቅ ጀርመንን ኢኮነሚ እንደሚያንኮታኩተዉ ከመጀመርያዉ ታይቶአቸዉ ነበር። የቀድሞ የምዕራብ ጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ቴዎ ቫይግል በበኩላቸዉ፣ ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጹ «በዚያን ጊዜ እ.ጎ.አ በ1990 የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ዲ-ማርክ ወደ እኛ ካልመጣ እኛ ወደ እሱ እንሄዳለን ይሉ ነበር» ሌላ ምንም አይነት አማራጭ አልነበረም፣ «ሊከሰት የሚችለዉን ነገር ሁሉ ከባለ ሞያ ጋር ተወያይተንበታል» በማለት ያስታዉሳሉ በዚህም ይላሉ እ.ጎ. አ ከ1989 እስከ 1998 ድረስ የምዕራብ ጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር የነበሩት ቫይግል፥ «መልሰን የፈረሰዉን ግንብ ካልገነባን በስተቀር የትኛዉም የባለሞያ ዕቅድ እና ዘዴ መፍትሄ ሊሆነን አልቻለም» አንድ በሆነችዉ ጀርመን የኢኮኖሚ ይዞታም በተለያየ ቦታ ልዩነት አመጣ። ሁለቱ ጀርመኖች እንደተዋሃዱ የምዕራብ ጀርመን ድርጅቶች በአካባቢያቸዉ የሚያመርቱትን ምርት ምስራቅ ጀርመን እያመጡ ይሸጡ ነበር። ከዚያ ነዉ ቀስ በቀስ በምስራቅ ጀርመን በሚገኙ የማምረቻ ድርጅቶች ስራ በመጀመራቸዉ የስራ ቦታ መገኘት የጀመረዉ። አሁንም ቢሆን በምስራቃዊዉ ጀርመን የኢኮነሚዉ አቅም ከምዕራቡ ጋር ሲነጻጸር ሰባ አንድ በመቶ ነዉ የሚሆነዉ፣ ይህ ማለት የምዕራብ ጀርመን የኢኮነሚ ሁኔታ በሲሶ አይሎ ይገኛል። በምስራቁ ክፍል ያለዉ ምጣኔ ሃብት ለየአንዳንዱ ነዋሪ ቢካፈል የምዕራቡን ስድሳ ስድስት በመቶ ነዉ የሚደርሰዉ፣ ይህ ማለት ደግሞ ከምዕራቡ ክፍል በሰላሳ አራት በመቶ እጅ አንሶ ይገኛል።


ምስራቁን መገንባት «የተሳሳተ ንግድ»

West frisst Ost
ምዕራቡ ምስራቁን ዋጠዉምስል AP

አንድ የአሜሪካ ታወቂ የንግድ ድርጅት ተጠሪ ከጥቂት አመታት በፊት የቀድሞዉን የገንዘብ ሚኒስትር ቴዎ ቫይግልን፣ «ምስራቅ ጀርመንን መግዛታችሁ» የተሳሳተ ንግድ ሳይሆን አልቀረም በማለት ጠይቀዋቸዉ ነበር። ቫይግል ይህን አይነት ጥያቄ መጠየቃቸዉ እንዳበሸቃቸዉ ገልጸዉ «አዎ በጣም ብዙ ጊዜ እና፣ ከጠበቅነዉ በላይ ብዙ ወጭ አሶጥቶናል፣ ግን ዛሬ 18 ሚሊዮን ህዝብ በነጻ ዲሞክራሲ ህይወቱን ይመራል። እናንተ አስር አመት ሙሉ ይህን ያህል እርምጃ በኢራቅ አሳይታችሁ ከሆነ ይህንን አይነት ጥያቄ መልሰህ ልትጠይቀኝ ትችላለህ» ስል መለስኩለት ብለዉ ገጠመኛቸዉን ተርከዋል። ታድያ ይህን ጥያቄ አቅራቢዉ አሜሪካዊዉ ነጋዴ ከአስር አመት በኋላ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጹን አጉልቶ መናገሩን ያቆመ ይመስላል፥ ቫይግልም «ባገኘሁት ቁጥር ያንን ከዚህ ቀደም ያቀረብኩልህን ጥያቄ መልሼ አልጠይቅም» ሲል ይናገራል ብለዋል።

«ምስራቅ ጀርመን በህዝብ ትብብር እና ድጋፍ የተገነባ፣ በጀርመን መሬት ላይ የተከናወነ ክስተት ነዉ » ሲሉ ቫይግል ይገልጻሉ። ይህም ትብብር እና ስራ ገና ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል። አሁንም ቢሆን ምስራቅ ጀርመን በራሷ የኢኮነሚ አቅም ልትወጣዉ የማትችለዉ ነዉ። ምስራቅ ጀርመንን ከምዕራቡ ጋር የተመጣጠነ ለማድረግ የተጀመረዉ የትብብር ድጋፍ ስምምነት እ.ጎ.አ እስከ 2019 ድረስ ይቀጥላል፣ ያ ማለት ከምዕራብ ጀርመን ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ወደ ምስራቁ ይፈሳል፣ ወደ ፊት በአዲስ እቅድ ለግንባታዉ የሚታቀደዉ ነገር ደግሞ በጊዜዉ የሚታይ ይሆናል። ምናልባትም ይህ የትብብር ስምምነት ዉል ጊዜዉ ሲጠናቀቅ፣ ስምምነቱ ስሙን ቀይሮ፣ ምስራቅ ጀርመንን የተደራጀ እና የተስተካከለ ዋስትና ያለዉ ኢኮነሚ እንዲኖራት በሚል የትብብር ስምምነት ሊጸድቅ ይችላል። ይሕ ማለት ሃብታሞቹ የጀርመን ክፍለ-ግዛቶች በኢኮነሚ ዝቅተኛ ለሆኑት ክፍለ-ግዛቶች ድጋፍ መስጠት ነዉ። ይህ ደግሞ አሁንም በምዕራቡም የሚያታይ ነገር ነዉ።

Helmut Kohl winkt bei einer Wahlkampfveranstaltung
መራሔ መንግስት ሔልሙት ኩል በምርጫ ዘመቻ ላይ-ኤርፉርትምስል picture alliance/dpa

ዛቢነ ኪንካርትስ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ