1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሕፃናት ከለላ የጠየቀዉ የUNICEF ዓመታዊ ዘገባ

ሐሙስ፣ ሰኔ 25 2007

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በምህፃሩ UNICEF የዘንድሮ ዘገባ እንደሚጠቁመው ፤ በዓለም ዙሪያ አንድ አስረኛ የሚሆኑት ሕፃናት በጦርነት ውስጥ ነው የሚያድጉት። ድርጅቱ ሕፃናት፣ እየተገደሉ፣ እየተደፈሩ እና ለስደት እየተዳረጉ ፤ ስለሆነ ከፍተኛ ከለላ እንደሚሹም አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/1FrIB
UNICEF Jahresbericht zur Lage von Kindern in Konfliktgebieten
ምስል picture alliance/abaca

[No title]

እንደድርጅቱ ዘገባ በተለይ ጦርነት በሚካሄድባቸው የዓለማችን ክፍሎች፤ የመማር እና የህፃናት እንክብካቤ መብቶች ህልም ብቻ ሆነው ቀርቷል።በአሁኑ ወቅት ጦርነት በሚካሄድባቸው የዓለማችን አምስት ሀገሮች፤ ሶርያ፣ኢራቅ፣ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ ሪፖብሊክ እና የመን ብቻ 21 ሚሊዮን ሕፃናት የጦርነት እና የአመፅ ሰለባ ሆነዋል ይላል የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት። ራሱን እስላማዊ መንግሥት በሚለው ቡድን እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት የሰብዓዊ መብቶች በከፍተኛ መጠን እየተጣሱ መሆኑን ድርጅቱ ያለፈው ዓመት ተሞክሮው ላይ ተመርኩዞ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

«ሕፃናት አልጋቸው ላይ እና ትምህርት ቤት ሆነው በቦምብ ተፈጅተዋል። ታግተዋል፣ ተገድለዋል፣ የወሲብ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል ወይም የልጅ ወታደር ሆነው ተመልምለዋል።»ይላሉ የ UNICEF ተጠሪ ቴድ ቻባን። በዚህም የተነሳ በዓለም ዙሪያ አንድ አስረኛው ሕፃን ወይም 230 ሚሊዮን ሕፃናት ጦርነት ውስጥ ለማደግ ተገደዋል። በጀርመን መዲና በርሊን ላይ ድርጅቱ የዘንድሮውን ዘገባ አሀዝ እየጠቀሰ ሲገልፅ፤ ችግሩ ምን ያህል የጎላ እንደሆነ 270 ገፆች ባሉት ጥናቱ ዘርዝሮ ለማሳየት ሞክሯል። እንደ ድርጅቱ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ቁጥራቸው እንደ አሁኑ ከፍ ያለ ሕፃናት ለስደት ተዳርገው አያውቅም። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ እንዳሁኑ መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ ለርዳታ አውጥቶ እንደማያውቅ ገልጿል። ጎርጎሮሳዊዉ አዲስ ዓመት ከገባ ከጥር ወር አንስቶ ብቻ ሶስት ቢሊዮን ዩኤስ ዶላር ለዚህ ወጪ ሆኗል። ለዚህም አስፈላጊ የነበረው 2/3ኛ የርዳታ ገንዘብ ከለጋሽ መንግሥታት ሲሰበሰብ ፤ 1/3ኛው ደግሞ ከግለሰቦች ነበር። ይህን ማሰባሰቡ አድካሚ እንደነበር የUNICEF የጀርመን ዋና ሊቀመንበር ዮርገን ሄሮየስ ገልፀዋል።

UNICEF Jahresbericht zur Lage von Kindern in Konfliktgebieten
ምስል picture alliance/abaca

«በሶርያ ከተጠቀሱት የጦርነት ችግሮች ይልቅ ለተፈጥሮ አደጋ ገንዘብ ማሰባሰብ ቀላል ሆኖ ሲገኝ አስተውለናል፤ ሰዎች የተፈጥሮ አደጋ እኛም ጋር ሊደርስ ይችላል በሚል ይረዳሉ። ሌላው ግን የጦርነት ግጭት ነው፤ ከኛ ጋር ብዙም የሚያገናኘው ነገር የለም በሚል።»

Irak Anbar Unicef Flüchtlinge Hilfe Kinder
ምስል RIRP

ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በጦርነት የስደተኞች መጠለያዎች 70,000 ሕፃናት መወለዳቸውን የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር በማስታወስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበለጠ መለገስ እንደሚገባው አሳስበዋል።«የዓለም የምግብ ድርጅትም ይሁን UNICEF ለምግብ የሚያቀርቡትን ገንዘብ ቀንሰዋል። ስለሆነም ሁሉንም ሕፃናት፣ወጣቶች እና ርዳታ የሚሹ ሰዎች ሊረዱ አይችሉም። ይህ የሆነው ባለባቸው የገንዘብ እጥረት የተነሳ ነው።»

ያም ሆኖ የጀርመን የልማት ድርጅት ባለፈው ዓመት 150 ሚሊዮን ዩሮ ለ UNICEF በመለገስ በጦርነት አካባቢ ለሚውሉ መርሀ ግብሮች አበርክቷል። ከዚህም ገንዘብ አብዛኛው ለሶርያ እና ኢራቅ የጦርነት ተሰዳጆች እንደዋለ ሚኒስትሩ ይናገራሉ። ሊባኖስ ውስጥ ደግሞ 100 000 ሕፃናት ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የልማት ድርጅቱ በደገፉን ሙለር ይናገራሉ። መጠኑን ባይናገሩም ዘንድሮም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ጀርመን ለሶርያ የሕፃናት ስደተኞች ለተነደፈው መርሀ ግብር በዋና ለጋሽ ሀገርነት ትጠቀሳለች። ቢሆንም ጥላቻ እና ችግር ከተሞላ ማህበረሰብ ይልቅ ጤናማ እና ተስፋ የተሞላ ሕፃን ለመፍጠር UNICEF አሁንም ከዓለም አቀፉ ማብሀረሰብ ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል።

ዛቢነ ኪንክራትስ

ልደት አበበ