1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለትንበያ አዳጋቹ የአየር ክስተት

ረቡዕ፣ የካቲት 8 2009

በምንኖርባት ምድር የአየር ጠባይ ከመደበኛው መጠን ይጨምራል ብሎም ይቀንሳል፤ ይኽ ተፈጥሯዊ ሒደት ነው። ሰው ሰራሽ ክስተቶች ግን  ከተፈጥሯዊ ሒደቱ ጋር ተደማምረው ጥፋቱን እንደሚያባብሱ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በተፈጥሮ ሒደቱ ብርቱ ድርቅ እንዲከሰት ያደረገው ኤል ኒኞ ሲያልፍ፦ የተተካችው ላ ኒኛ የተሰኘች የአየር ጠባይ ሌላ አደጋ ደቅናለች።

https://p.dw.com/p/2XYqz
Äthiopien Afar Kühe Rinder in trockener Landschaft
ምስል DW/G. Tedla

ለትንበያ አዳጋቹ የአየር ክስተት

ላ ኒኛን የቀደመው ኤል ኒኞ ባስከተለው ድርቅ  የተነሳ ለአብነት ያኽል በኢትዮጵያ  በአሁኑ ወቅት 5,6 ሚሊዮን ነዋሪዎች የረሐብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተዘግቧል።  የሙቀት መጠኑ እጅግ ሲቀንስ ወይንም ቅዝቃዜው አይሎ ላ ኒኛ የተሰኘችው የአየር ጠባይ ስትከተል በዓለማችን ምን ይከሰታል? ላ ኒኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሄዷ የአየር ትንበያን አስቸጋሪ የሚያደርገውስ ለምን ይኾን?

ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡባዊ እና ምሥራቃዊ አፍሪቃ የሚገኙ 25 ሃገራት ለዐሥርተ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ መመታታቸው ተዘግቧል። የድርቁ ዋነኛ መዘዝ ደግሞ የኤል ኒኞ አየር ጠባይ ነው ተብሏል። በተለይ ላለፉት 18 ወራት በብርቱው ኤል ኒኞ የተነሳ የተከሰተው አደገኛ ድርቅ ላለፉት 35 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ እንደኾነ ተነግሮለታል።

Äthiopien Fentale Skelett von Vieh an Straße
ምስል DW/S. Cousins

በዓለማችን የትኛውም አቅጣጫ ውቅያኖስ ከተለመደው የአየር ጠባይ እጅግ ሲቀዘቅዝ አለያም ሲሞቅ በሌላኛው የዓለም ክፍል ብርቱ ክንዱን ያሳርፋል። መደበኛ በሚባለው የአየር ጠባይ በደቡባዊም ኾነ በሰሜናዊ  ንፍቀ-ክበብ በምድር ወገብ አቅጣጫ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚነፍሰው ንፋስ (trade winds) ሞቃት የውቅያኖስ አካልን ወደ እስያ ይገፋል። ይኽ የንፋስ ጉዞ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይዳከማል። እናም ሞቅ ያለው የውቅያኖስ ውኃ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ይመለሳል። በደቡብ አሜሪካ አህጉር የባሕር ወሽመጦች ላይ የሚገኘውን ቀዝቃዛ ውኃም ይቀንሰዋል። ሒደቱን የከባቢ አየር ሳይንቲስቶች ኤልኒኞ ይሉታል በስጳኝ ቋንቋ አጠራሩ፤ «ትንሹ ልጅ» እንደማለት ነው ትርጓሜው። 

ኤል ኒኞ በሌላ ጊዜ ጠንከር ብሎ ወደ ምዕራብ ሲቀዝፍ የዓለማችን ምሥራቃዊ ክፍል የውቅያኖስ ውኃ ከተለመደው በላቀ እንዲቀዘቅዝ ያደርገዋል። ሒደቱን ተመራማሪዎች «ትንሿ ልጅ» ላ ኒኛ ይሉታል። ካናዳ በሚገኘው የካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ አከባቢ ተጽዕኖ ቅነሳ ፋኩልቲ ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር የኾኑት ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ይበልጥ ያብራሩታል። 
 
«በመደበኛ የውቅያኖስ ዑደት ላይ እነ ኢንዶኔዢያ፣ አውስትራሊያ ያሉበት የምዕራቡ ክፍል ሙቅ ውኃው የሚሰበሰብበት ነው። ቀዝቃዛው ውኃ ደግሞ ወደ በደቡብ አሜሪካ።ይኼ መደበኛ ዑደት ነው። »

ብርቱው ኤል ኒኞ እንዳለፈ ዘንድሮ የተከሰተችው ላ ኒኛ በጥር ወር ሞዛምቢክ ውስጥ የጎርፍ መጥለቅለቅ በማስከተል 300,000 ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሳለች። ብርቱ ዝናም በማስከተልም በደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙ ሃገራት ነዋሪዎች ላይ መፈናቀል አስከትላለች። የመሠረተ-ልማት አውታሮችን በመጉዳት፤ በሽታዎች እንዲከሰቱም አድርጋለች።  

BdT Überflutung, Trinidad Nordbolivien
ምስል AP

ኤል ኒኞም ኾነ ላ ኒኛ በተለምዶ ከ9 እስከ 12 ወራት ይቆያሉ። ዘንድሮ ብርቱውን ኤል ኒኞ የተከተለችው ላ ኒኛ አቅመ-ደካማ ቆይታዋ አጭር ነበር። ለአራት ወራት ግድም ነበር የቆየችው። ይኽ ወደፊት በወቅታዊ እና የረዥም ጊዜ የአየር ትንበያ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይጠቀሳል። በእርግጥ ምን አይነት ተጽዕኖ ነው የሚያስከትለው?

በይኾናል በመቶኛ የሚሰላው የአየር ትንበያ ኤል ኒኞ እና ላ ኒኛ ጌዜያቸውን ሳያዛቡ የሚሄዱ ከሆነ የትንበያው እርግጠኝነት ጥሩ ይኾናል እንደ ዶክተር ጌታቸው ማብራሪያ። ኾኖም ደካማ ኾና የተከሰተችው ላ ኒኛ በአጭር መቀጨት የሚቀጥሉት ሁለት ወቅቶች አልፈው እነሱን በሚከተሉት ሁለት ወቅቶች ላይ የኤል ኒኞ ክስተት እና መደበኛ ኾኖ የመቀጠሉን እርግጠንነትን ወደ 40 በመቶ ዝቅ አድርጎታል ብለዋል ተመራማሪው። 

የኤል ኒኞ እና የላ ኒኛ መደበኛ ዑደት ሲያጥር ሁለት እና ሦስት ዓመት ሲረዝም ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ይቆያል። ኢትዮጵያ ላ ኒኛን ከስድስት ዓመት ግድም በኋላ ያስከተለው ኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ክስተት ብርቱ ጥፋት ከደረሰባቸው ሃገራት አንዷ ናት። ላ ኒኛ ምን ይዛ እንደምትመጣ አይታወቅም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ