1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአስተማማኝ ፣ዘላቂ ዕድገት፣ የሥነ-ቴክኒክ የፈጠራ ውጤት፣

ረቡዕ፣ ኅዳር 27 2004

ጀርመን ፤ Zukunftspreis የምትለውን በሥነ-ቴክኒክ ምርምር ፣ላቅ ያለ ውጤት ለሚያዝመዘግብ፤ለምታስመዘግብ፣ ለሚያስመዘግቡ ፣ በያመቱ የምትሰጠውን ትልቅ ሽልማት፣ ዘንድሮም ለ 15ኛ ጊዜ ታቀርባለች።

https://p.dw.com/p/S0cc
የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት የሚስበው አዲሱና እጅግ ንዑሱ የክብሪት መያዣ ያህል መጠን ያለው ስስ ጡብ መሰሉ መሣሪያ፣ምስል DZP/Ansgar Pudenz

ስለእጩ ተሸላሚዎቹ ከማውሳታችን በፊት፤ የ «አሪፍ የእጅ ስልኮች»ን (Smartphones)የኃይል ምንጭ ፣ በአጅጉ መቀነስ ስለተቻለበት ሁኔታ ፣ ከፊንላንድ በተገኘ ማብራሪያ እንጀምራለን።

ፊንላንድ ውስጥ ፣ ከመዲናይቱ ሄልሲንኪ ወጣ ብሎ የሚገኘው ፣ «አልቶ» የተባለው ዩኒቨርስቲ ተማራማሪዎች፣ የተለያየ ሰፋ ያለ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ የእጅ ስልኮች(«እስማርትፎንስ»)የሚጠቀሙበትን የኃይል ምንጭ፣ ከ 70 ከመቶ በላይ መቀነስ መቻላቸውን አስታውቁ ። ይህ፤ በእስማርትፎን ለሚገለገሉ ብዙዎች ሰዎች ፣ በተለይ ደግሞ፤ የቀን ፤ የወር ሆነ የዓመት ገቢአቸው ዝቅተኛ ለሆነው ለታዳጊ አገሮች ህዝብ፤ ሰፊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚያጠራጥር አይደለም ። የተለያየ አገልግሎት ሰጪ ዘመናዊ የእጅ ስልኮች፤ በዓለም ዙሪያ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ መሆናቸው የታወቀ ነው። ካለፈው ሐምሌ ወር ገደማ አንስቶ እስከመስከረም መጨረሻ በ 3 ወር ዕድሜ ብቻ በዓለም ዙሪያ 115 ሚሊዮን እስማርትፎንስ መሸጣቸው ነው የተነገረው። ለኀይል ምንጭ ቁጠባው መሠረቱ፣ በእጅ ስልክና ፈንጠር ብሎም ሆነ ከሩቅ በሚገኝ ኮምፒዩተር ያለ ግንኙነት ነው። በአልቶ ዩኒቨርስቲ ፤ በዚህ ረገድ በተደረገ ምርምር ፤ የመሪነቱን ቦታ መያዛቸው የሚነገርላቸው ሳይንቲስት ፤ Jukka Manner ና ቡድናቸው፣ ከስልክ ጋር ግንኙነት ያለው አዲስ «ሶፍትዌር» ና ከሩቅ ያለ የኮምፒዩተር «ሐርድዌር»፣ በስልኩ ራዲዮ አማካኝነት የኃይል መጠን በእጅጉ እንዲቀነስ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል። የተጠቀሰው የተማራማሪዎች ቡድን ፤ የመጀመሪያውን የምርምር ውጤቱን ፤ በቅርቡ ታንዛንያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪቃውያን የመገናኛ ጉዳይ ጉባዔ ላይ ማቅረቡ ተወስቷል። ማነር፤ የምርምሩ ውጤት መፈተሹንና ስለምርምሩም ሰፋ ያለ ማብራሪያ በአዲሱ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መባቻ ላይ መቅረቡ እንደማይቀር አስረድተዋል።

ተመራማሪዎቹ፤ በታንዛንያ፤ ዩጋንዳና ኬንያ፤ የኤልክትሪክ አገልግሎት በሌለባቸው ብዙ አካባቢዎች ያለውን የመረጃ ማግኛና ማስተላለፊያ ችግር፣ በተጠቀሰው መልኩ መቅረፍ እንደሚቻል የጠቆሙት ማነር ፤ ፊንላንድ ውስጥ፣ የእጅ ስልክን የኤልክትሪክ ኃይል መሙላት ካልተቻለ፣ ሰዎች ይናደዳሉ። በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች ግን ፤በዚህ ረገድ የሚያስቆጣ ጉዳይ አይኖርም። በመጀመሪያ ስልኩ፤ ባትሪውም ሆነ ኤልክትሪኩ የት ይገኝና! በማለት በአንክሮ ይገልጻሉ።

ከአፍሪቃ አንድ ቢሊዮን ፤ 37 ሚሊዮን አምስት መቶ ኻያ ዐራት ሺ ኀምሳ ስምንት ህዝብ መካከል 11 ከመቶው ብቻ ናቸው በኢንተርኔት መገልገል የሚችሉት። ያም ሆኖ ከግማሽ በላይ ፤ ማለትም ከ 500 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የአጅ ስልክ አለው። የፊንላንዳውያኑ ተማራማሪ ቡድን እንደሚለው፤ 90 ከመቶው አፍሪቃውያን የሚኖሩት የሞባይል አገልግሎት ማግኘት በሚቻልበት አካባቢ ነው። ማነር፤ ቡድናቸው አፍሪቃ ላይ ቢያተኩርም፤ ሥነ-ቴክኒኩ፣ ከሆነ የኢንተርኔት መረብ ወይም አገር ብቻ የተሣሠረ አይደለምና በመሠረቱ፣ የትም ቦታ ተግባራዊ የሚሆን ነው። እዚህ ላይ «ፕሮክሲ» የተባለው ከእጅ ስልክ የሚጠየቀውን መረጃ ሁሉ ሰብስቦ፣ ወደ ኢንተርኔት መረብ የሚያስተላልፍ ነው። ይኸው መሣሪያ፤ ከእጅ ስልክ መረጃ መቀበል ብቻ ሳይሆን ፣ እርሱም ራሱ ፤ ከኢንተርኔት የሚያገኘውን ፣ መልሶ፣ ለእጅ ስልክ ያስተላልፋል።

የአልቶ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ፣ «እስማርትፎን» የእጅ ስልክ የሚጠቀምበትን የኃይል መጠን 74 ከመቶ ገደማ በአስተማማኝ ሁኔታ መቀነስ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ጀርመንና በወደፊት መጻዔ ዕድሏ ላይ ያተኮረ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት፤

በመጪው ሳምንት ፤ረቡዕ፤ታኅሳስ 4, ቀን 2004 ዓ ም፤ በርሊን ላይ ፤ የጀርመን ፕሬዚዳንት ክርስቲያን ቩልፍ፣ ጀርመናውያን ፣ የመጻዔ ዕድል ሽልማት የሚሉትን፤ የሥነ-ቴክኒክም ሆነ የፈጠራ ሥራ፤ ወይም ለኤኮኖሚ ጠቀሜታ ላለው የምርምር ውጤት ሽልማት (Zukunftspreis)አሸናፊም ሆነ አሸናፊዎች በልዩ ሥነ ሥርዓት ይሸልማሉ። ለ 15 ኛ ጊዜ የሚሰጠው ፤ እ ጎ አ የ 2011 ሽልማት ይገባቸዋል ተብለው የታጩት 3 የምርምር ቡድኖች ሲሆኑ ፣ የሚሰጠው የሽልማት መጠን 250,000 ዩውሮ ነው። ከታጩት መካከል ደግሞ አንደኛው፤ በፍራይቡርግ ከተማ የሚገኘው በተደጋጋሚ፤ የፀሐይን ሙቀት የሚስቡ ልዩና ስስ ጡቦች ይሠራ የነበረው ፤ አሁን ግን መጠኑ የክብሪት መያዣ ያክል አነስተኛና እጅግ ስስ ፣ እንዲሁ በቀላሉ በዐይን ብሌን ሊታይ የማይችል የሠራው የ «ፍራውን ሆፈር» የምርምር ተቋም ነው። ተቋሙ ባደረገው ምርምር መሠረት፤ የፀሐይን የጨረር ዓይነቶች በጅምላና በተናጠል በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። የፊዚክስ ምሁሩና ተመራማሪው Andreas Bett እንደሚሉት፤ ወደፊት የኃይል ምንጭን ፤ የልብስ ቁልፍ ከምታክል ክብ ነገር ማግኘት የሚያዳግት አይሆንም። 2,«አንድ እንደምሳሌ ሊቀርብ የሚችል፣ ቀስተ ደመና ነው። የማርያም- መቀነት ወይም ቀስተ ደመና ፤ የፀሐይን ብርሃን በተለያዩ ቀለማት እያንጸባረቀ የሚያሳይ መሆኑ እሙን ነው። በዚህም መሠረት ነው፤ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት የሚስቡት ጥቃቅኖቹ ስስ ጡብ መሰል መሣሪያዎቻችን ፣ በተለያዩት ባለ ኅብር ቀለም አንጸባራቂ ብርሃናት ደረጃ እንዲሠሩ ያደረግነው። እንደደረጃቸውም፣ የሚቀበሉትና የሚያመነጩት ሙቀት መጠን አለው። ይህን ጽንሰ ሐሳብ መሠረት በማድረግም ነው የተሠሩት።»

የላይኛው የስስ ብረቱ ጡብ አካል፣ በአጭር ሞገድ የሚፈነጥቀውን ሰማያዊውን የብርሃን ክፍል ያንጸባርቃል። መካከለኛው አካል አረንጓዴውን የታችኛውና የመጨረሻው ክፍል ወይም ንጣፍ ደግሞ ቀዩን ጨረር (infra-red)ይወክላል። በእንዲህ ሁኔታ ነው እንግዲህ በከፍተኛ ደረጃ ሙቀት ማጥመድ የሚቻለው።

«መደበኛውና የፀሐይ ሙቀት ሳቢ ስስ ጡብ መሰል መሳሪያ ከሚያስገኘው የሙቀት ኃይል 3 እጥፍ የላቀ ማግኘት የቻልንበት የምርምር ውጤት፣ የዓለምን ክብረወሰን የያዘና በዚህ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ከፀሐይ 41 ከመቶ የኃይል ምንጭ ማግኘት እንደሚቻል አሳይተናል። ይህ አስደናቂ ውጤት የተመዘገበው (እ ጎ አ በ 2009 ) ነው። ከዚህ ለመድረስ ደግሞ ፣ ለረጅም ጊዜ ሰፊ ጥረት አድርገናል።»

በኅዋ፣ ለውትድርና አገልግሎት የማይውሉ ከ 400 በላይ ሳቴላይቶች የሚገለገሉት፤ የፍራይቡርግ ሳይንቲስቶች በሠሯቸው «ሶላር ሴልስ» ነው። አንድሪያስ ቤት፤ ምርምሩ በቀላል ሙከራ የተመረኮዘ መሆኑን አልሸሸጉም። ወሳኙ፣ የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት ለመሳብ የሚያመች መስታውት ወይም ብርጭቆ ማቅረብ ነው። እናም የፀሐይ ሙቀት በጠባብ ቦታ ተከማችቶ እንዲሰበሰብ ያስችላል። እናም፣ በአሁኑ ጊዜ Silizium Solar System የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚያስገኘው ሙቀት በእጥፍ የበለጠ ከልዩው መስታውት ማግኘት ይቻላል ።

የተጠቀሰው የፋራይቡርጉ ተቋም፤ በፀሐይ ኃይል ኤልክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮችንም እየሠራ ለገበያ ማዋል ከጀመረ 4 ዓመት ሆኖታል። እ ጎ አ በ 2007 በመጀመሪያ ለእስፓኝ የሸጠው አውታር አንድ ሺ ያህል ቤተሰቦችን የኤልክትሪክ ተጠቃሚዎች አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ ይህን መሰል 13 አውታሮች፤ በዛ ባሉ አገሮች በዩናይትድ እስቴትስ ጭምር ሥራ ላይ ውለዋል። አውታሮቹ የሚፈልጉት አንድ ነገር ብቻ ነው። ደመናም ሆነ ጉም የማይሸፍነው የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት ወደ ምድር የሚደርስበት ሰማይ ነው።

ሌላው በእጩነት የቀረበው ከድረስደን ዩኒቨርስቲና የፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም ከንዑስ የተፈጥሮ ቁስ አካል፤ ብርሃን ማግኘት የሚቻልበትን ብልሃት ያገኘው የምርምር ቡድን ነው። ከኢምንት አካላት የኃይል ምንጭና ብርሃን ለማግኘት፤ ተመራማሪዎቹ፤ Organic Electronics በተሰኘው ዘርፍ ነበረ አትኩረው የሠሩት። በድሬስደን የቴክኒክ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ምሁር ካርል ሌዮ እንዲህ ይላሉ።

«እጅግ ተምኔታዊ የመሰለው ራእይ፤ ምን ነበረ? አዎ፣ የግድግዳና የኮርኒስ ልዩ ወረቀት ከተለጠፈ በኋላ፣ ጌጥ ብቻ ሳይሆን፤ ብርሃን እንዲሰጥ ነበረ የታሰበው፤ እናም የሚቻል ሆኗል። ለምሳሌም ያህል መስኮት ላይ መሸፈኛ ወረቀት ለጥፎ በተጨማሪ መብራት እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።»

ይህ የሥነ ቴክኒክ ውጤት፤ በ 6 እና 7 ዓመታት ውስጥ ለህዝብ ጥቅም ይሰጥ ዘንድ ገበያ ላይ እንደሚውል ፕሮፌሰር ካርል ሌዮ አስታውቀዋል።

ኢንጅኔር ዑቨ ፍራንክ ፤ ዶ/ር እስቴፋን ጌሪግ፣ እንዲሁም ዶ/ር ፣ ኢንጅኔር ክሌመንስ ራበ፣ ከዳይምለር አክሲዮን ድርጅት ጋር በመተባበር በ 6 ማዕዘናት ተንቀሳቃሽ ነገር ጉልቶ የሚያቀርበትን ዘዴ (6 D) ያሳዩ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከሰው ቀድሞ በፍጥነት፤ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ መሆኑ ታውቋል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ