1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢራቅ ደህንነት የመከረዉ ጉባኤ በባግዳድ

ሰኞ፣ መጋቢት 3 1999

ባሳለፍነዉ የሳምንት መጨረሻ ሰላም በራቃት ኢራቅ ደህንነት ሊመጣ በሚችልበት መንገድ ላይ የመከረ በባግዳድ ጉባኤ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/E885

ይህም እንደታዛቢዎች እምነት ከሆነ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለታለመዉ ረዥም ጉዞ መነሻ ነዉ። በኢራቅ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀዉ ይህ ዓለም ዓቀፍ ዉይይትም ችግሩና ተፈላጊዉ እርምጃ ላይ በማትኮር የአገሪቱን ፀጥታና ደህንነት ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ ለመቃኘት ሞክሯል። ሆኖም በአገሪቱ በየዕለቱ የሚፈሰዉ ደም ወዲያዉ ሊቆም ይችላል የሚል ተስፋ ማንም አላደረበትም። ይልቁንም ለአገሪቱ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማስገኘት ጉባኤዉ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑ ነዉ የታመነበት።
በኢራቅ የተካሄደዉ የቅዳሜ ዕለቱ ዉይይት በትክክለኛዉ ጎዳና ለመሄድ የሚያስችል የመጀመሪያዉ ርምጃ ነዉ ማለት ይቻላል። ጎረቤት ኢራንን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ ጥቃትና ሞት የየዕለት ተግባር በሆኑባት በኢራቅ ደህነትን ሁኔታዎች ወደነበሩበት እንዴት መመለስ ይቻላል በሚለዉ ዋነኛ ጉዳይ ላይ አትኩሯል። በጉባኤዉ የመጀመሪያ እርምጃነት ማንም በቀላሉ ይስማማል። ብቻ ከሁሉም የትኛዉ ነዉ ትክክለኛ ጎዳና? ግቡስ የቱ ነዉ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ምክንያቱም ችግሩ ጎረቤት ከሆኑትና ጉዳዩ በቀጥታ ብዙም ከማይነካቸዉ ሀገሮች እይታ በኢራቅ ዉስጥ ጥቃቱ ከተባባሰ አካባቢዉን ሁሉ ሊያጣቅስ ይችላልና ኢራቅ መረጋጋት አለባት የሚል መልዕክ ይሰማል። በአንድ ወገን አሜሪካና ኢራቅ የዉጪ ጣልቃገብነት የኢራቅን ችግር እያባባሰዉ ነዉና ይቁም የሚል አቋም አላቸዉ። በሌላ ወገን ሶሪያና በተለይ ኢራን ደግሞ የኢራቅ ወረራ ያብቃ ባይ ናቸዉ። የተለያየ ፍላጎት ባለበት መካከል መጠነኛ ልዩነት የራሱ ጫና ቢኖርም የሁሉም ሃሳብ ሲታይ በመካከላቸዉ መሰረታዊ ቅራኔ ያለ አይመስልም። ያ ነዉ እንግዴህ የቅዳሜዉን ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ አዎንታዊ አንድምታ ያለዉ የመጀመሪያ እርምጃ ያስባለዉ። ይህም የሳዳም ዘመን ካከተመ ወዲህ በባግዳድ የተካሄደ የ16 መንግስታት ተወካዮች የተካፈሉበት የመጀመሪያ ትልቅ ጉባኤ ነዉ። ሁሉም ወደኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዝ የሚፈሰዉ የንፁሃን ደም እንዲያቆም ይፈልጋሉ። ሁሉም በኢራቅ ነገር ሁሉ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ፍላጎት አላቸዉ። አሁንም ሆነ ሰንብቶ ሁሉም የአሜሪካ ጦር ከዚያች ምድር እንዲወጣ ይሻሉ። ሁሉም ይህን ይፈልጋሉ። ባልተለመደ ሁኔታ ሶሪያና ኢራን በተገኙበት በባግዳዱ ጉባኤ የተገኘችዉ ራሷ ዩናይትድ ስቴትስም ብትሆን ትፈልገዋለች።
ምንም እንኳን አንዱ ሌላዉን የሚጫንበትና የሚገፋበት ቢኖርም በንግዱ ዘርፍ ባለዉ ግንኙነት እየተራረመ አንዱ ከሌላዉ ጋ የሚጓዝበት ሁኔታ አለ። ። እዚህ ጋ የኢራን የአቶም ዉዝግብ ወይም የሊባኖስን ልማት መጥቀስ ይቻላል።
አሁን በባግዳድ የተካሄደዉ የመጀመሪያ ዙር ዉይይት ይህ ነዉ የሚባል ዉጤት ባያሳይም በቀጣይ የሚደረጉት ስብሰባዎች፤ እንዲሁም የተለያዩ ቡድኖች እየተገናኙ የሚያካሂዱት ንግግር አንድ ነገር ይኖረዋል ተብሎ ታስቧል። በባግዳድ የሚደረገዉ የመሳሪያ ፍተሻዉ፤ማዕቀቡና የተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ ሁሉ ለመረጋጋቷ ያመጣላት ነገር የለም ለኢራቅ። እንግዲህ በቀጥታ በሚደረገዉ ንግግር ጠብ የሚል ነገር ይኖር ይሆናል ተብሎ ነዉ የሚታሰበዉ።
ሰላም በወዳጆች መካከል ሳይሆን በባላንጣዎች መካከል መምጣት አለበት። በኢራቅ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣትም ያን መሰሉ ጥረት ነዉ መደረግ ያለበት። ያለፈዉን ወደጎን በመተዉ ሁሉም ወገኖች የተለያየ አለካከት እንደያዙ ለንድ ግብ በጋራ ማለም ከቻሉ ያኔ አንዱ ከሌላዉ ጋ መነጋገር ይችላሉ ማለት ነዉ። ያኔ ደግሞ ለትብብር የሚረዳ ነገር ማድረግ ይችላሉ። ሳዳም ሁሴን ከስልጣን እንደተወገዱ አሜሪካኖችና ኢራኖች ማድሪድ ላይ ኢራቅን በተመለከተ ጉባኤ ላይ ተገናኝተዉ ያችን አገር ለመርዳት ቃል ገብተዉ ነበር። ከዚያ ወዲህ ከዛሬ ነገ ኢራቅ ዲሞክራሲ የሰፈነባት የበለፀገች አገር ትሆናለች የሚለዉ ተስፋ ብቻ ነዉ የሚነገረዉ። የሚታሰበዉን ለዉጥ ለማምጣት እያንዳንዱ ያለበትን ሃላፊነት ማስተዋል ይኖርበታል። የባግዳዱ ጉባኤም ይህን በይፋ ለማሳወቅና ለመናገር የመጀመሪያዉ ነዉ የሆነዉ። ለጊዜዉ የታየ ለዉጥ ባይኖርም ወደፊት ሊያራምድ የሚያስችል ብርሃን በዋሻዉ ጥግ ቦግ አድርጓል ተብሎለታል።