1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ሰባት ዓመት ስንት ነው?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ የመግባት እቅድ ወጥኗል። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት አገሪቱ ከታቀደው አማካኝ የገቢ ደረጃ ለመድረስ በየዓመቱ በ10.7% ማደግ ይጠበቃባታል።

https://p.dw.com/p/2gpNo
Äthiopien Windpark
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughn

ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ሰባት ዓመት ስንት ነው?

ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የአገራትን ኤኮኖሚ ከአራት በሚመድብበት አጠቃላይ ብሔራዊ ዓመታዊ ገቢ አነስተኛ ከሚባሉት ጎራ ተመድባለች። ኤርትራ፤ቻድ እና ቡሩንዲን የመሳሰሉ የአፍሪቃ አገራትም የዜጎች አማካኝ አመታዊ ገቢ ከ1,005 ዶላር በታች ከሆነባቸው መካከል ይገኛሉ። 
የኢትዮጵያ መንግሥት የእድገት እና ለውጥ ሁለተኛ እቅድ ''አማካይ የነፍስ-ወከፍ ገቢ በ2002 ከነበረበት 377 የአሜሪካን ዶላር በ2007 መጨረሻ ወደ 691 የአሜሪካን ዶላር'' ማደጉን ያትታል። "በ2017 ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገርን እውን ማድረግ" የዕቅዱ ንሸጣ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ሰነድ ያትታል። 
ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ዝቅተኛ ገቢ ካላቸውም ይሁን ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ፈጣን ኤኮኖሚያዊ እድገት ነበራት የሚሉት የዓለም ባንክ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያው ጌራርድ ካምቡ ባለፈው ዓመት ግን መቀዛቀዙን ይናገራሉ። ካምቡ እንደሚሉት ድርቅ እና ውጪያዊ ተፅዕኖዎች ኤኮኖሚውን ወደ ኋላ የጎተቱ ዋንኛ ጉዳዮች ናቸው። 
"በ2016 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ አፈፃጸም በድርቅ እና ውጪያዊ ሁኔታዎች ክፉኛ ተጎድቷል። ድርቁ የኤኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ጎድቶታል። ኢትዮጵያ ቡና እና የቅባት እህሎች የመሳሰሉ ምርቶቿ ዋጋ በዓለም ገበያ አሽቆልቁሏል። በእነዚህ ምክንያቶች የአገሪቱ እድገት በ2014/15 ከነበረበት አማካኝ ከነበረበት 10 በመቶ  ወደ ሰባት በመቶ ቀንሷል።"
ወትሮም ከማያጣት ድርቅ ባሻገር ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄም ሲንጣት እየተስተዋለ ነው። የተቃውሞ እና ኹከቱ ወላፈን ጥሪታቸውን ቋጥረው በኢትዮጵያ የከተሙ ባለ ወረቶችን ጭምር መግረፉ አልቀረም። ኢትዮጵያ እቅዷን ማሳካት ከፈለገች ባለፈው አመት ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ ያለውን ኤኮኖሚያዊ እድገት መልሶ እንዲያንሰራራ ማድረግ ይጠበቅባታል። ለዚህ ደግሞ ያላት ሰባት ዓመታት ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያው የኤኮኖሚ ባለሙያ ሰባቱ አመታት በቂ ለመሆናቸው ጥያቄ አላቸው። 
ጌራርድ ካምቡም የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እንደ ባለፈው ዓመት ካዘገመ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ላይ ለመድረስ የተያዘው ውጥን እንደማይሰምር እርግጠኛ ናቸው። ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያው የኢትዮጵያ መንግሥት በ2016 ዓ.ም. የገጠመውን በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሊያካክስ ይገባዋል የሚል ጥቆማ አላቸው።
"የሁለተኛው የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ቁልፍ ግብ በአምስት ዓመታት ውስጥ በ11 በመቶ አማካኝ ኤኮኖሚያዊ እድገት ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር መሆን ነው። የዕቅዱ የመጀመሪያ ዓመት በሆነው የ2016 ዓ.ም. ተጨባጭ እድገት ግን ከመንግስት እቅድ በታች ነበር። ይኸ የሚጠቁመው የኢትዮጵያ መንግሥት እቅዱን ለማሳካት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚኖረውን እድገት ማፋጠን እንደሚኖርበት ነው።"የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ጉባኤ (UNCTAD) ባለፈው ታኅሳስ ይፋ ያደረገው የደሐ አገሮች ዘገባ ኢትዮጵያ ካቀደችው መድረስ እንደማትችል አትቷል።  በእርግጥ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ጉባኤ የዓለም አገራትን ኤኮኖሚ ለመመዘን የሚጠቀምባቸው መለኪያዎች ከዓለም ባንክ የተለዩ ናቸው። መመዘኛዎቹ ከኤኮኖሚያዊ ቁጥሮች ተሻግሮ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትንም ይፈትሻሉ። የአማካኝ ስሌቶች ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የመምራት እድል እንዳላቸው የሚናገሩት የኤኮኖሚ ባለሙያው የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ጉባኤ በበኩሉ ተጨማሪ ማኅበረሰባዊ መለኪያዎች እንደሚጠቀም ይናገራሉ።
የዓለም ባንክ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያ ሆነው የሚያገለግሉት ጌራርድ ካምቡ ባለፉት ዓመታት በመሰረተ-ልማት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ የተጠመደው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፊቱ ፈተናዎች እንዳሉበት ይናገራሉ። 
"አገሪቱ የምትጋፈጣቸው በርካታ ፈተናዎች አሉ። ምክንያቱም ፈጣን ኤኮኖሚያዊ እድገትን ለማስቀጠል ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ ይጠይቃል። ይኸ ደግሞ ከግሉ ዘርፍ ከዚህ ቀደም ካየነው የበለጠ መዋዕለ-ንዋይ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በአገሪቱ የቢዝነስ ከባቢን ማሻሻል ይሻል።"
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ 
 

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes
Äthiopien Schuhfabrik Fabrik Herstellung Schuhe
ምስል Getty Images/Z. Abubeker