1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ የፊልም ጥበብንና ጥበበኞች ሽልማት

ሐሙስ፣ መጋቢት 4 2006

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ባለቀለም ፊልም በሆነው «ጉማ» በተሰኘው የሚሸል ፓፓታኪስ ፊልም ስም የተሰየመው የፊልም ስራ ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በብሄራዊ ቴአትር ባለፈው ሰምወን በድምቀት ተከናውኗል።

https://p.dw.com/p/1BPAf
Gumma Filmpreis Äthiopien
ምስል DW/A. Tadesse Hahn

የዛሬ አር በተለያዩ የፊልም ሙያዎች ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እውቅና ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀው «ጉማ የፊልም ሽልማት» ባ ዓመት የተሰራዉን የመጀመርያ የቀለም ዘጋቢ ፊልምን አንግቦ ነዉ።

ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየዉ የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ባለፉት አስርት ዓመታት የጎሉ እንቅስቃሴዎች ታይተዉበታል። ለዚህም በቅርቡ በጀርመን ታዋቂ በሆነዉ ዓለማቀፍ የፊልም ዉድድር በርሊናለ እና መድረክ እና በዩናይትድ ስቴትሱ የሰንዳንስ ፊልም ፊስቲቫል ላይ ሽልማትን ያገኘዉ የኢትዮጵያዉ «ድፍረት» የተባለዉ ፊልም ተጠቃሽ ነዉ። በፊልም ስራ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዩኤስ አሜሪካ ያጠናቀቀዉና ከአስራ ሁለት በላይ ፊልሞችን እንደሰራ የሚነገርለት የጉማ ፊልም ሽልማት ዋና አዘጋጅ አቶ ዩናስ ብርሃነ መዋ፤ እንደሚለዉ ዝግጅቱ የፊልም ጥበብንና ጥበበኞችን ለመደገፍ የታሰበ የሽልማት ስነ-ስርዓት ነዉ፤ በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ- ስርአት ላይ በአስራ ሰባት የፊልም ጥበብ ዘርፎች ሽልማት እንደ ተሰጠ የሚገልፀዉ የፊልም ሥራ ባለሞያዉ አቶ ዩናስ ብርሃነ መዋ እንደሚለዉ፤ ከሽልማቶቹ መካከል በተለይ አንዱ ለዉድድር የማይቀርብ ዘርፍ አለ፤ ያም ዘርፍ፤ የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሚሆነዉ ሰዉ መርጦ ማዉጣት ነዉ ። የመጀመርያዉ የጉማ ተሸላሚ፤ ከአርባ ዓመት በላይ በፊልም ጥበብ ስራ ላይ የቆዩት፤ የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ ፊልም ዳሬክተር ሚሼል ፓፓታኪስ ናቸዉ። በኢትዮጵያ የፊልም ስራ ትልቅ ሚና እንደነበራቸዉ የሚታወቀዉ እና የጉማ ፊልም ባለቤት ሚሼል ፓፓታኪስ ይላል የፊልም ስራ ባለሞያዉ ዮናስ ብርሃነ መዋ በመቀጠል፤ ሚሼል ፓፓታኪስ፤ አባታቸዉ አዲስ አበባ ዉስጥ የፊልም ቤት የከፈቱ የግሪክ ዜጋ፤ እናታቸዉ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ሲሆን ትዉልዳቸዉም እዚሁ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።

Gumma Filmpreis Äthiopien
ምስል DW/A. Tadesse Hahn

የፊልም ሽልማት ሥነስርዓቱን ጉማ ሲል መጠርያ የሰጠዉ የስነ-ስርዓቱ ዋና አዘጋጅ እና የፊልም ስራ ባለሞያዉ ዩናስ ብርሃነ መዋ፤ የዛሬ አርባ ዓመት በሚሼል ፓፓታኪስ የተሰራዉ ጉማ ፊልም፤ ስያሜዉን ከኦሮምኛ ቋንቋ እንደወሰደና፤ ካሳ ማለት እንደሆን ገልፆልናል። ፊልሙ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዉስጥ ስላለዉ የግጭት አፈታት ባህል ላይ የሚያዉጠነጥን ዘጋቢ ፊልም እንደሆነ በሰጠን ቃለምልልስ ገልፆልናል። በአሁኑ ወቅት ይህ ፊልም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ወመዘክር ወስጥ እንደሚገኝም ተመልክቶአል። ጉማ የፊልም ሽልማት ስነ-ስርዓት አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ላለዉ የቪዲዮፊልሞች ምርት መሰረት የጣሉትን ሰዎች ያስታወሰ፤ በዳኝነትም ሆነ አንጋፋ የፊልም ተዋናዮችን ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነበር ሲሉ የኢትዮጵያ የፊልም ሰሪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ኃይሉ ገልፀዉልናል።

የፊልም ኢንዱስትሪዉ እንዲያድግና፤ በኤኮኖሚዉ ፍርያማ እንዲሆን ሁሉም የተቻለዉን ጥረት እንዲያደርግ ብሎም የመንግስትን ድጋፍ ይሻል ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ ፊልሙ የሃገሬቱን ባህል በማስተዋወቁም ረገድ ሆነ ዓመታዊ ገቢን ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የፊልም ስራ እድግት ጥራትና ኢትዮዮጵያዊ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን የፊልም ሰራተኛ ማህበሩ ጥረት እያደረገ መሆኑን የነገሩን የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ኃይሉ፤ እንደሚሉት፤ የፊልም ሰራተኞችን ማበረታቻ የሚሰጥ እንዲህ አይነቶቹ የፍልም ሽልማቶች ፤ የፊልም ጥበብንና ጥበበኞችን ታላቅ ድጋፍ ይሰጣል፤ ያበረታታል፤ የፊልሙ ጥራትም እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ስለባህል መድረክ መሰናዶ ያላችሁን አስተያየት በተለመዱት አድራሻዎቻችን ብትልኩልን በደስታ እናስተናግዳለን፤ ሙሉዉን ዝግጅት ለማድመጥ የድምፅ መጠቆምያዉን በመጫን ይከታተሉ !

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኃላ