1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ይኖር ይሆን?

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 28 2002

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም የብዙ ሰው ህይወትን በማጥፋት ላይ ስላለው የወባ በሽታ በኬንያ መዲና ናይሮቢ አንድ ዓቢይ ስብሰባ ተካሄደ።

https://p.dw.com/p/KQJC

በዚሁ ካለፈው ሰኞ እስከ ትናንት ድረስ በዘለቀው የአንድ ሳምንት ስብሰባ ላይ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ የሚበልጡ ጠበብት፡ የመንግስታት ተወካዮች እና ሌሎች ባለሙያዎች መታገል ስለሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል። ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መድሀኒት በማግኘቱ ጥረት አኳያ አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ በመታየት በያዘበት ባሁኑ ጊዜ ብዙዎች በወባ በሽታ ይሞታሉ። ለዚሁ በያመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዘጠኝ መቶ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን፡ በተለይም፡ ህጻናትን ለሚገድለው የወባ በሽታ ማጥፊያ መድሀኒት የማግኘቱ ጥረቱ የናይሮቢው ጉባዔ ዋነኛ ዓላማ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ በያመቱ ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ሰዎች እንዳዲስ በሚያዙበት የወባ በሽታ ላይ የተወያየው ይኸው ጉባዔ ለሁለተኛ ጊዜ በተከታታይ በአንድ አፍሪቃዊት ሀገር መካሄዱ እንዳው ያጋጣሚ ነገር አልነበረም፤ እንደሚታወቀው፡ በወባ በሽታ ከሚሞቱት አስር ሰዎች መካከል ዘጠኙ አፍሪቃውያን ሲሆኑ፡ ከነዚህም ብዙዎቹ በናይጀሪያ፡ በኮንጎ፡ በኢትዮጵያ እና በታንዛንያ ነው የሚገኙት። በአሁኑ ጊዜ በወባ በሽታ አብዝታ በተጎዳችው የምዕራብ ኬንያ ከተማ፡ ኪሱሙ ከተማ የሚሰሩ ኬንያዊው የህጻናት ሀኪም ዶክተር ዋልተር ኦቲየኖ እንደገለጹት፡ የህክምና አገልግሎት ከሚሰጡዋቸው አስር ህጻናት መካከል ሰባቱ በወባ በሽታ የሚሰቃዩ ናቸው።
« እዚህ በምዕራብ ኬንያ የወባ በሽታ ትልቅ ችግር ደቅኖዋል። በዚሁ አካባቢ የወባን ያህል የብዙ ህጻናትን ህይወት ያጠፋ ሌላ በሽታ የለም። በመላ ኬንያ በያመቱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከሚሞቱባቸው አምስት የተለያዩ በሽታዎች መካከል አንዱ የወባ በሽታ ነው። በዚሁ በሽታ ሰላሳ ስድስት ሺህ ህጻናት ይሞታሉ። የኪሱሙ አካባቢም በዚሁ እጅግ የተጎዳ ነው። »
ኦቲየኖ ለወባ መከላከያ ይሆናል ተብሎ በታሰበው እና በወቅቱ ብዙ ተስፋ በተጣለበት ክትባት ላይ በመካሄድ ላይ ላለው የመጨረሻ ወሳኝ ሙከራ ተጠያቂ ናቸው። ጠበብት ካለፉት አሰረተ ዓመታት ወዲህ ማካሄድ በቀጠሉት ምርምር ያዘጋጁት የክትባት ዓይነት የወባ በሽታን የሚያስተላልፈው ፕላስሞዲየም የሚሰኘው ንዑስ ተህዋሲ፡ በጉበት በኩል አድርጎ ወደ ደም ስር ከመግባቱ እና በተለይ በአንጎል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ማጥፋት የሚቻልበትን ሙከራ በሰባት የአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ጀምረዋል። በነዚሁ አፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ በሁለተኛው ሙከራ ወቅት ክትባቱ ከተሰጣቸው አስራ ስድስት ሺህ ህጻናት መካከል ግማሾቹ በሽታውን መከላከል መቻላቸው ለተመራማሪዎቹ ጠበብት አበረታቺ ምልክት ፈንጥቆዋል። እንደ ጠበብቱ ግምት፡ አሁን የተጀመረው ሶስተኛ የሙከራ ርምጃ አዎንታዊ ውጤት ካስገኘም ከሶስት እስካ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ክትባቱን በገበያ ለማውጣት ሳይቻል እንደማይቀር ጠበብቱ ተስፋ አድርገዋል።
የናይሮቢው ጉባዔ ተሳታፊዎች ለጸረ ወባው መድሀኒት ለጀመሩት ምርምር ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ ጠይቀዋል። በተመ የጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ መሰረት፡ የወባ በሽታን ውጤታማ በሆነ ዘዴ መታገል ይቻል ዘንድ አሁን በያመቱ ለምርምር የሚቀርበው አንድ ሚልያርድ ዶላር ወደ አምስት ከፍ ማለት ይኖርበታል።
ኬምሪ በመባል የሚታወቀው፡ የኬንያውያኑ የምርምር ተቋም በናይሮቢ ስብሰባ ላይ ባቀረበው የጥናት ውጤት መሰረት፡ የወባ በሽታን የሚያስተላልፈውን ፕላስሞዲየም የሚሰኘውን ንዑስ ተህዋሲ ለምትሸከመውና አኖፖለስ ለምትባለዋ እንስቲቱ የወባ ትንኝ መከላከያነት የሚያገለግለው ጸረ ወባ በሽታ መድሀኒት የተረጨው አጎበር ጥቅም እየቀነሰ መምጣቱን አመልክቶዋል። ምክንያቱም በተለይ በዝናቡ ወራት በብዛት የምትራባዋ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ የምትነድፈው ካሁን ቀደም እንደሚታደርገው ሌሊት ሳይሆን ከቀትር በኋላ ማብቂያ እና ገና መሸት ማለት ሲጀምር ሆኖዋል። አጎበሮቹ ሁሌ ስለማይደረጉ ወይም በቀላሉ ስለሚበጣጠሱ ወይም ለአሳ ማጥመጃ ተግባር ስለሚውሉ በወባ በሽታ አንጻር ሀያ አምስት ከመቶ የሆነ ከለላ ብቻ እንደሚሰጡ ነው ጥናቱ ያመለከተው። በዚህም የተነሳ በናይሮቢው ጉባዔ የተሳተፉት የአንድ የዩኤስ አሜሪካ ቡድን ተጠሪ የወባ በሽታ ያለባቸው ህጻናት ፍቱን የሆነውን የተለያዩ መድሀኒቶች ስብስብን የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አስረድተዋል፤ ምንም እንኳን ይህንን ዓይነቱን መድሀኒት ማግኘቱ ለአንድ አፍሪቃዊ ቤተሰብ ከሚያገኘው ወርሀዊ ደሞዙ በስድሳ አምስት እጥፍ በልጦ ቢገኝም። መድሀኒቱ ውድ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በወባ በሽታ ከሚሰቃዩት ህጻናት መካከል አስራ አምስቱ ብቻ ናቸው ይህንኑ መድሀኒት የሚያገኙት፤ ሌሎቹ ሰማንያ አምስት ከመቶ በአውሮጳ ከገበያ ውጭ በሆኑት መድሀኒት መውስድ ይገዳዳሉ።
የወባ በሽታ ከተስፋፋባቸው አንድ መቶ አምስት የዓለም ሀገሮች መካከል እጅግ የተጎዱት ሰላሳዎቹ የሚገኙት በአፍሪቃ ሲሆን፡ አምስቱ እስያውያት ሀገሮች ናቸው።

አርያም ተክሌ
DPA/DW

Am 25. April 2008 Welt Malaria Tag Kind hinter Moskitonetz
ምስል picture-alliance/ dpa