1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለውጥ በተማራማሪዎች ልውውጥ

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2004

Change by Exchange (Wandel durch Austausch)በሚል መሪ ዓርማ፣ የጀርመንና የአፍሪቃ ከፍተኛ ተቋማት የምርምር ትብብር ያሳዬ ጉባዔ፣ ከትናንት በስቲያ ሰኞ፣ ተካሄደ። ዋና ጽ/ቤቱ በቦን ከተማ የሚገኘው የጀርመን የአካደሚ

https://p.dw.com/p/14Kjf
አቶ ካይ ኤትሶልድምስል DW/T. Yewahla

Change by Exchange (Wandel durch Austausch)በሚል መሪ ዓርማ፣
የጀርመንና የአፍሪቃ ከፍተኛ ተቋማት የምርምር ትብብር ያሳዬ ጉባዔ፣ ከትናንት በስቲያ ሰኞ፣ ተካሄደ።
ዋና ጽ/ቤቱ በቦን ከተማ የሚገኘው የጀርመን የአካደሚ የልውውጥ አገልግሎት (Deutscher Akademischer Austausch Dienst)Welcome to Africa በሚል ርእስ በጋራ ትብብር ላይ ያተኮረ ፣ ከጧት እስከማታ የዘለቀ የአፍሪቃውያንና የጀርመናውያን ተማራማሪዎች ጉባዔ ያካሄደ ሲሆን፣ በጀርመን የትምህርትና ምርምር ሚንስቴር የበላይ ተቆጣጣሪነት ፤ DAAD ያሰናዳው ይኸው ጉባዔ፣ የጀርመን ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ከአፍሪቃውያን ተባባሪዎቻቸው ጋር፤ በኅብረት የምርምር ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ ለማብቃትና የአፍሪቃውያን ተመራማሪዎች አቅም በማጎልበት ጎን -ለጎን የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የሚያስችልበትን አሠራር የዳሰሰ ነበር። የ DAAD የምርምር ጽሑፍም ሆነ ንግግር አቀራረብ ጉዳይ ኀላፊ Cay Etzold ባስተባበሩትና የሳይንስ ጋዜጠኛና ፕሮግራም መሪ፣ ኢዛቤል ሊዝበርግ-ሃግ ፤ በሊቀ-መንበርነት በመሩት በዚሁ ዐቢይ የምርምር ሰዎች ጉባዔ ፣ ላቅ ያለ ግምት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የተመረጡ ፕሮጀክቶችና ሥራ አስኪያጆቻቸውን ለጉባዔው ተሳታፊዎች ማስተዋወቅ ሲሆን ፤ የፕሮጀክቶቹ መሪዎች መድረክ ላይ እየወጡ በተንቀሳቃሽ ስዕልና በመሳሰለው በመታገዝ ማብራሪያ አቅርበዋል።

DAAD Deutscher Akademischer Austausch Dienst neues Hochschulkooperationsprogramm
የጉባዔው ዓርማምስል DW/T. Yewahla

ስለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማብራሪያ ካቀረቡት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምህንድስና ፤ ህንጻ ግንባታና የከተማ ልማት ተቋም ፕሮፌሰር ፤ የሆኑት ጀርመናዊው ዶ/ር ዲርክ ዶናት ናቸው። ለማስተማርና ለማማከር አዲስ አባባ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጥ ከጀመሩ 3 ዓመት እንደሆናቸው የገለጡት ፕሮፌሰር፣ በጀርመንና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ትብብር እንዲህ ያብራራሉ።
« የተቀየሰው መርኀ-ግብር ECBP የሚባለው ነው።(Engineering Capacity Building Programme)
ይህ ሁለቱም ወገኖች፣ ውሉ ያሥተሣሠራቸው ክፍሎች፣ ማለትጀርመንና ኢትዮጵያየኢንጀሪጉን ዘርፍ በተለይ መሠረተ -ልማትን ፤ የከተማ አቅድን ምህንድስናን ፤ የውሃ ልማትን፣ የተፈጥሮ አካባቢ አያያዝን በሰፊው ማጠናከር የው የሚሹት። ይህም ባንድ በኩል፤ ባለፉት ዓመታት በጀርመን እርዳታ የተገነቡትን 10-12 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎችን የሚመለከት ነው። የኔም ሥራ በዚህ ዘርፍ ያለውን የሚመለከት ነው። አርአያነት ያለው ይኸው የከፍተኛ ተቋማት ግንባታ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ተቋማት፣ ፋክልቲዎች፤ ሥርዓተ-ትምህርት የመሳሰለውን ያጠቃልላል።»

ጀርመን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር አይደለችም። ጥንትም ሆነ የኢንዱስትሪው አብዮት ተቋዳሽ ከሆነችበት ዘመን አንስቶ የምትመካበት ዋና ጥሬ ሀብቷ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ዕውቀት ነው። ለዚህም ነው ጀርመን የምጡቅ ሐሳብ አፍላቂዎች ሀገር የሚል ተቀጥላ ስም ያገኘችው።
ጀርመን የቀለም ትምህርት (Academy)እና የቀለም ትምህርትን ከተግባር ጋር በማዋኻድ የታወቁ በዛ ያሉ የሳይንስ ዩንቨርስቲ ኮሌጆች አሏት። ራሳቸውን የቻሉ፣ የዩንቨርስቲ ያልሆኑ ተቋማት፤ በኩባንያዎችና በፌደራሉ መንግሥት ወይም በፌደራል ክፍለ ሀገር ተግባራቸውን የሚያከናውኑ አያሌ ተቋማትም አሉ። አገሪቱ ፤ በኢንዱስትሪ ማኅበራት ድጋፍ ከሚንቀሳቀሱት የልማት ማዕከላት ውጭ ባጠቃላይ ፣በግምት፣ ከ 750 የማያንሱ በመንግሥት የሚደገፉ የምርምር ተቋማት እንዳሏት የታወቀ ነው። ከታወቁት አያሌ የምርምር ተቋማት መካከል፤
1,የማክስ ፕላንክ የምርምር ማኅበር
2, ፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም፣
3, ሄልምሆልትዝ የምርምር ማዕከላት ማኅበር
4, ላይብኒትዝ እናየመሳሰሉት ይገኙበታል።
እነዚህ ተቋማት በተለይም በትምህርትና ምርምር ሚንስቴር የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚመራው የጀርመን የአካደሚ ልውውጥ አገልግሎት፣ ከብዙ አዳጊ አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በሳይንቲስቶች፤ ተመራማሪችና ተማሪዎች ልውውጥ ረገድ ዐቢይ ተሳትፎ አለው። የልውውጥ ጉዳይ ከተነሳ ፤ እንዴት ቢደረግ ከሞላ ጎደል የሠመረ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል፤ በመጠቆም፤ አሁን በባዝል፤ እስዊትስዘርላንድ ዩኒቨርስቲ፣ የአፍሪቃ ጥናት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሞዛምቢካዊው ፕሮፌሰር ኤሊሲዮ ማካሞ ለጉባዔው ያሰሙትን ንግግር ፍሬሐሳብ ባጭሩ ሲያስረዱ--
«የዛሬው ንግግሬ ዋና መልእክት፣ DAADን ስለመርኀ-ግብሩ ለማመሥገንና በተጨማሪ፣ የጀርመን ባለሥልጣናት በተለይ የትምህርትና ምርምር ሚንስቴር ፤ አፍሪቃውያን ምሁራን እርስ-በርስ እንዲተጋገዙ፤ ለአነርሱ ኀላፊነቱን መተው፤ የሚበጅ መሆኑን ማሳሰብ ነበር። እንዲሁ፤ ስለአፍሪቃ ባጠኑና በዚያው መስክ በሚሠሩ፣ እንዲሁም እናውቃለን ብለው በሚያስቡ ጀርመናውያን መመካቱ የማያዛልቅ መሆኑን ለማስገንዘብ ነበር።»

Konferenz Teilnehmer Deutscher Akademischer Austausch Dienst
የጉባዔው ተሳታፊዎችምስል DW/T. Yewahla


ጀርመናውያኑ የምርምር ሰዎች በተለያዩ አዳጊ አገሮች ለትብብር በሚሠማሩበት ጊዜ ተቀዳሚው ትኩረት ምን ሊሆን እንደሚገባ ከድሬስደን ዩንቨርስቲ ዓለም አቀፍ የደን ጥበቃና የእንጨት ነክ ኤኮኖሚ ጉዳይ ተቋም ፕሮፌሰር ዶ/ር Jürgen Pretzsch እንዲህ ነበረ ያሉት--
«በዚያው ምርምር በሚደረግበት ቦታ ያለውን ዕውቀት አስቀድሞ ያጤኗል። በሀገሬው ነባር ዕውቀት መሠረት ከጣሉ በኋላ ነው ተጨማሪ ምርምር ማዳበር የሚቻለው። ቀላል አይደለም፤ የረጅም ጊዜ ልፋትን፣ ጥረትን የሚጠይቅ ነው። ባለፉት 10 ዓመታት በዋናነት ዐቢይ ግምት የሰጠነው ለዚህ ጉዳይ ነበር። ሥርዓቱ፤ የማኅበራዊ ኑሮ ሥርዓቱ፣ በአፍሪቃም ሆነ በላቲን አሜሪካ ከተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጋር ያለውን ቁርኝት ይበልጥ ለመገንዘብ ጥረት ተደርጓል።»
በኢንዱስትሪ በበለጸጉትና በአዳጊ አገሮች ተቋማት መካከል የሚደረገው ትብብር ያስገኘው ውጤት ምልክቱ ይታያል? በማለት ያስረዱን ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩትን ፕሮፌሰር ዲርክ ዶናትን እንደገና ጠይቄአቸዋልሁ።
«እንዴታ!፤ እንዴታ!አኀዙን ልብ ብለን ብንመለከት፣ ከ 5፤ 6፤ 7 ዓመት በፊት በግምት40 ያህል መሃንዲሶች ነበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በያመቱ የሚመረቁት። ከዚያ ወዲህ ግን፤ ከ 300-400 ገደማ የሚሆኑ ናቸው እንደሚገመተው የሚመረቁት። ይህ እንግዲህ በ 10 እጥፍ ጨምሯል ማለት ነው። በግምት እንዳልሁት፤ ከ 300-400 እዚህ ላይ ደግሞ የጥራት ጉዳይም አብሮ ይነሣል። በሰፊው ሰሚናሮች ይዘጋጃሉ። ጠበብት ይመጣሉ። ከሁሉም በኩል በትጋት ይሠራል። በጀርመን የአካደሚ ልውውጥ አገልግሎት ፣ የጀርመን ጠበብት ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ፤ የኢትዮጵያ ሳይንቲስቶችም ወደ ጀርመን ይመጣሉ። በመርኀ ግብር በመታቀፍ ይሠለፋሉ። በሌላ በኩል ወደፊት በብሩኅ መልኩ ለሚ,ት ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ያልነበረው ምርምር ፣ምክክር፤ በተለይ በእኛ ተቋም EIABC ----ስሙ ረዘም ያለ ይመስላል፤ ግን ይህን መሠረታዊ መመሪያውን አቋሙን ይዞ ከመንግሥት ዘርፍ እስከ ምህንድስና አያያዝና አቅድ አወጣጥ ነው የሚንቀሳቀሰው።»

በጀርመን የአካደሚ ልውውጥ አገልግሎት ረገድ ፤ አንዱ ከሌካው የሚመረው ብዙ ነገር እንዳለየጠቆሙት ፕሮፌሰር ዲርክ ዶናት፤ ኢትዮጵያ ስላላት የማደግ ተስፋ ይህን ብለዋል።--
«ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሮችን ለመቋቋም በሚደረግ ጥረት፤ ኢትዮጵያን እንደ ላቦራቷር ወይም እንደ ሠርቶ ማሳያ ጣቢያ ማየት ይቻላል። በህዝብ ቁጥር የህዝቧ አኀዝ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጨመርባቸው አገሮች አንዷ ናት በሚመጡት 10ተ-ዓመታት በከተሞች አያያዝ በተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ፤ የመሠረተ-ልማት ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምላሽ ማግኘት አሁኑኑ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ጀርመንም፤ ከዚህ መማር ትችላለች፤ ከኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችና የሙያ ሠልጣኞች ጋር ተግባሩን ማከናወን ትችላለች።»

Dirk Donath Ethiopian Institute of Architecture
ፕሮፌሰር ዲርክ ዶናትምስል DW/T. Yewahla

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ