1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለዩክሬን ቀዉስ አዲስ ተስፋ

ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2006

በምሥራቅ ዩክሬን ለተባባሰዉ ዉጊያ መፍትሄ ለመፈለግ ሁለት እንቅስቃሴዎች በተከታታይ ተይዘዋል። በመጪዉ ሳምንት የዩክሬን ፕሬዝደንት ፔትሮ ፕሮሼንኮና በሀገራቸዉ በተፈጠረዉ ብጥብጥ እጇን ከታለች በማለት የሚከሷት የሩሲያ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን ቤላሩስ ላይ ተገናኝተዉ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1CzNq
Deutschland Ukraine Petro Poroschenko bei Angela Merkel in Berlin
ምስል imago

ከዚያ አስቀድሞዉ በነገዉ ዕለት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኪየቭ ላይ ከፕሬዝዳንት ፕሮሼንኮና ከጠቅላይ ሚኒስትር አርሴኔይ ያትሰኒዩክ ጋ ይወያያሉ። ዩክሬን ቀዉስ ዉስጥ ከገባች ወዲህ የጀርመን መራሂተ መንግስት ወደኪየቭ ሲሄዱ ይህ የመጀመሪያ ነዉ የሚሆነዉ። በዚህ ጉዞ ሊጫወቱት የሚችሉት ሚና ቀላል እንደማይሆን ነዉ የሚነገረዉ። የፊታችን ማክሰኞ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፕሮሼንኮና የሩሲያዉ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን በምሥራቅ ዩክሬን ስላለዉ ግጭት ለመነጋገር ሚኒስክ ቤላሩስ ላይ እንደሚገናኙ ይጠበቃል። ሁለቱ መሪዎች ባለፈዉ ግንቦት መጨረሻ ፈረንሳይ ላይ ፊት ለፊት የተነጋገሩ ናቸዉ። በሚኒስኩ ስብሰባ ላይም ከቤላሩስና ካዛኪስታን መንግሥታት ተወካዮች በተጨማሪ የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ግንኙነት ኃላፊ ካትሪን አሽተን፤ የንግድ ኮሚሽነር ካርል ደ ጉች እንዲሁም የኃይል ጉዳይ ተጠሪዉ ጉንተር ኦይቲንገርም ይገኛሉ።

Russland Wladimir Putin Rede auf der Krim 14.08.2014
ምስል picture-alliance/AP Photo

እንዲያም ሆኖ የሚኒስኩ ጉባኤ እንደታሰበዉ የሚከናወን ከሆነ መካሄዱ ብቻ ብዙ የሚነገርለት ነዉ የሚሆነዉ። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት መጀመሪያ ላይ ፑቲንና ፕሮሼንኮ ተገናኝተዉ ከተነጋገሩ በኋላ በምሥራቅ ዩክሬን ዉጊያዉ መባባሱ ታይቷል። ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ኅብረትም ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ ሩሲያ ላይ ጥለዋል። ሩሲያም የተለያዩ የአጸፋ ማዕቀብ እርምጃዎችን ወስዳለች። በዚህ የተነሳም ሁኔታዉ በየአቅጣጫዉ ተባብሷል። እናም ይህ የማክሰኞዉ ስብሰባ ብቻዉን አንዳች ለዉጥ ያመጣል ብሎ ተስፋ ያደረገ ሊያዝን ይችላል። ምክንያቱም አሁንም ዉጊያዉና የየአቅጣጫዉ የአፀፋ ምላሽ ተባብሷልና። ብራስልስ ከሚገኘዉ የአዉሮጳ የመርህ ማዕከል የምሥራቅ አዉሮጳ ጉዳዮች ተመራማሪ አማንዳ ፓዉል በዩክሬን ቀዉስ ላይ ከሚካሄዱት ዉይይቶች ይህ ነዉ የሚባል መፍትሄ እንደማይጠብቁ ነዉ የሚናገሩት። ያም ቢሆን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የግንኙነቱ መስመር እንዲቀጥል መደረጉ በጎ ርምጃ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። ከዉይይቱ ዉጤት የመገኘቱን ነገር የተጠራጠሩበት ምክንያትም ሁለቱ ወገኖች ሚኒስክ ላይ ይዘዉ የሚቀርቡት የተለያየ ፍላጎታቸዉን የሚያንፀባርቅ ሃሳብ መሆኑን በመገመት ነዉ። ለፕሮሼንኮ ምሥራቅ ዩክሬን መረጋጋት ዋና ጉዳይ ነዉ ፤ ፑቲን ደግሞ በዚያ አካባቢ የሰብዓዊ ሁኔታዉ እየከፋ ሄዷል የሚል የቃል አቀባይነት ሚና እንደሚጫወቱ ይገምታሉ። ለኪየቭና ብራስልስ ፖለቲከኞች ግን የፑቲን ስለሰብዓዊ ይዞታ መከራከር፤ ምሥራቅ ዩክሬን ዉስጥ ጣልቃ ለመግባት ያላቸዉ ፍላጎት መገለጫ ነዉ። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ግን ጠንካራ ዉይይት ከተካሄደ መፍትሄ ማምጣቱ አይቸግርም ነዉ ያሉት፤

Russischer Konvoi an der Grenze zur Ukraine 21.08.0214 bei Donezk
ምስል picture-alliance/dpa

«ለዩክሬንና ሩሲያ ጠብ ሰበብ የሆነዉ የምሥራቅ ዩክሬን ዉዝግብ አሁም ቢሆን መፍትሄ ሊገኝለት የሚችል ነዉ። ከባድ ዉይይት ካካሄድን በኋላ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ኪየቭና ምሥራቅ ዩክሬን የከረረ አቋማቸዉን ማማላላታቸዉን ለመገንዘብ ችያለሁ። ሁለቱም ተኩስ የሚቆምበትን መላ ለማግኘት በመጣር ላይ መሆናቸዉንም ተገንዝቤያለሁ።»

ሩሲያ ወደምሥራቅ ዩክሬን አካባቢ የላከቻቸዉ የእርዳታ እሕልና ቁሳቁስ ጭነዋል የተባሉ ወደሶስት መቶ የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች ከሳምንት በኋላ ትናንት ወደ ዩክሬን ግዛት መግባት ጀምረዋል።20 የሚሆኑት ደግሞ በአማፅያኑ መሪነት ወደሉንስክ መጓዝ መጀመራቸዉን የአይን ምስክሮችን የጠቀሰዉ የሮይተርስ ዘገባ ያስረዳል። ዩክሬን ተሽከርካሪዎቹ ያለፈቃዷ ወደግዛቷ መግባታቸዉን በማመልከት ሩሲያ ወረራ ፈጸመችብኝ እያለች ነዉ። ፕሬዝደንት ፕሮሼንኮም ድርጊቱ ዓለም ዓቀፍ ሕግን የጣሰ ነዉ ብለዋል። ሞስኮ ለሳምንት የነበረዉን ቆይታ ትርጉም የለሽ በማለት ተሽከርካሪዎቹ ጥቃት ቢደርስባቸዉ «ዉርድ ከራሴ» ብለላለች። የሩሲያን ርዳታ የጫኑትን የተሽከርካሪዎች አጀብ ቀይ መስቀል እየመራ እንዲገቡ የቀረበለትን ጥያቄ ድርጅቱ በጸጥታ ስጋት ምክንያት አልተቀበለም።

Luhansk Ukraine Ostukraine Armee Truppen 21.08.2014
ምስል Reuters

የአዉሮጳ ኅብረት በሚኒስኩ ስብሰባ የሚኖረዉ ሚና ብዙ ባይባልለትም የኃይል ጉዳዮች ኮሚሽነሩ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተካረረዉን ዉዝግብ በተለይም የጋዝ ጉዳይን የመሸምገል ሚና እንደሚኖር ጠቁመዋል። የሩሲያ ጋዝ አብዛኛዉ ወደአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የሚሸጋገረዉ በዩክሬን በኩል በመሆኑም በግርግር የሚመጣዉን ችግር ከወዲሁ ለመከላከል ያለመ ነዉ። የንግድ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደ ጉች ኅብረቱ ከዩክሬን ጋ የሚኖረዉ የነፃ ገበያ ስምምነት ሩሲያን የሚፃረር አለመሆኑን፤ እንደዉም በተቃራኒዉ ራሷ ሞስኮ ልትጠቀምበት የምትችል መሆኑን እንደሚያስረዱ ይጠበቃል። ሩሲያ፣ ዩክሬን ከኅብረቱ ጋ የምትመሠርተዉን ስምምነት ትታ ከቀድሞዉ የሶቭየት ሪፐብሊክ በመሠረተችዉ የንግድ ትስስር እንድትቀጥል ትሻለች። ሜርክል በነገዉ የኪየቭ ቆይታቸዉ ከዩክሬን መሪዎች ጋ በግልፅ በመነጋገር ነገሮችን መስመር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል። የአዉሮጳ ኅብረት የተረጋጋች ዩክሬንን ማየት እንደሚሻ በመግለፅም ድጋፉን እንደማይነፍግ፤ በአንፃሩም ከኪየቭ መሪዎች ምን እንደሚጠበቅ አስረግጠዉ እንደሚነግሩ ይገመታል። ተቺዎቻቸዉ የኪየቭ ፖለቲከኞች መራሂተ መንግሥቷ ከፑቲን ጋ ባላቸዉ ቅርርብ ምክንያት የሩሲያ ተጓዳኝ አድርገዉ ያይዋቸዋል ቢሉም የሜርክል የኪየቭ ጉዞ በተቃራኒዉ ከዩክሬን ወገን ከፍተኛ ማሳደሩ ነዉ የሚነገረዉ። እንዲያም ሆኖ ሜርክል ምዕራብ ዩክሬን ከአዉሮጳ ኅብረትና ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ጋ የፈጠረዉ ትስስር በሞስኮና ብራስልስ መካከል ያስከተለዉን ፍጥጫ የማርገብ ከፍተኛ ሚና ይጠብቃቸዋል። ይህም ፈታኝ መሆኑን ታዛቢዎች ይገምታሉ።

ክሪስቶፍ ሀሰልባህ / ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ