1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለፋሽስት ክብር መስጠት ይቁም!

ቅዳሜ፣ መስከረም 12 2005

እናት አባት አያቶቻችን፣ ያኔ በዝያ ዘመን ጠላት አገራችንን ሲወር በፉከራ በአንድነት በባህላዊ መሳርያ በጦር በጋሻ ተዋግተዉ ህዝቡ ለነፃነቱ ቀናኢ የዉጭ ወራሪን የማይቀበል የራሱንም ዳር ደንበር ሃይማኖት እና ባህልም አይነካም ብሎ ማቆየቱ የኢትዮጵያዉያን ታሪክም ባህልም ነዉ።

https://p.dw.com/p/160Cd
ምስል DW

እናት አባት አያቶቻችን፣ ያኔ በዝያ ዘመን ጠላት አገራችንን ሲወር በፉከራ በአንድነት በባህላዊ መሳርያ በጦር በጋሻ ተዋግተዉ ህዝቡ ለነፃነቱ ቀናኢ የዉጭ ወራሪን የማይቀበል የራሱንም ዳር ደንበር ሃይማኖት እና ባህልም አይነካም ብሎ ማቆየቱ የኢትዮጵያዉያን  ታሪክም ባህልም ነዉ።

ተጉዘን ተጉዘን ምን እንበላ ይሆን

ጣልያን ለቁርሳችን ያልበቃን እንደሆን።

ቤልጅጉን ወልዉለን መንሽሩን ወልዉለን፥

መዉዜሩን ወልዉለን  እየጠበቅናቸዉ፥

እነዝያ አህዮች ቀሩ እንዳንጭናቸዉ።

ሊቢያ ዉስጥ በ1920ዎቹ ፊዛን በተባለዉ ደቡብ ምዕራባዊ ክፍለ ሃገርና በኋላም በኢትዮጵያ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ,ም አዲስ አበባ ዉስጥ  30 ሺ ያህል ህዝብ በአንድ ቀን የጨፈጨፈው ፣ ከዚያም  በደብረ ሊባኖስ ገዳም ፣ ከ 300 በላይ የሚሆኑ መነኮሳት ፤ ካህናትና  ዲያቆናትን የፈጀው ፣ የፋሺስቶች አውራ ቤኒ ሙሶሊኒ ቀኝ እጅ ፤ ለጀኔራል  ሮዶልፎ ግራዚያኒ ፤ ኢጣልያ ውስጥ፤ በላሲዮ ክፍለ ሀገር፣ አፊሌ በተባለች መንደር አንድ ቤተ መዘክር መሰራቱ በአለም ዙርያ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንን አስቆጥቶአል።  በለንድን ነዋሪ የሆኑ ሶስት ኢትዮጵያዉያን እና ሌሎች ሶስት ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች በጋራ ድርጊቱ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ንቀት ብቻ አለመሆኑን በማሰብ አባቶቻችን ያስቀመጡልንን አደራ በዚህ የታሪክ ጠባሳ የሚሻር እና የሚያሳፍር ስራ ሲሰራ ዝም ብለን አናይም ሲሉ የአለም ህዝብን የተቃዉሞ ስምምነት በማሰባሰብ ነገ  በለንደን የጣልያን ኢንባሲ ቅጥር ግቢ ፊት ለፊት በርካታ ኢትዮጵያዉያን እና ሌሎች ዜጎችን ያካተተ ትዕይንተ ህዝብ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ናቸዉ። የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ እና በለንደን ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ማህሌት ማዕረጉ የጣልያንን መንግስት ለመቃወም ከባልደረባቸዉ ከአቶ ሰለሞን አማረ ጋር በአለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመርያ ግዜ የአቤቱታ ማስተባበያ ፊርማ ማህደር አዘጋጅተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር ላይ በርካታ ዘመናትን ያሳለፉት እንግሊዛዊ ሪቻርድ ፓንክረስት ነገ አርብ ለንደን በሚገኘዉ የጣልያን ኤንባሲ ፊት ለፊት በሚደረገዉ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ተካፋይ መሆናቸዉ ታዉቆአል። ሪቻርድ ፓንክረሰት ሁኔታዉ በጣም አስደንግጦኛል ሲሉ ገልጸዉልናል።
«አንድ ጥቁር መዝገብ ዉስጥ የሰፈረ የጦር ወንጀለኛ በጣልያን ህዝብ ዛሪ ሽልማትን አገኘ የሚልን ስሰማ በጣም ነዉ ያስደነገጠኝ። ይህ ግለሰብ 1920  ዎቹ በሊቢያ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽሞአል። በጣልያን ወረራ ዘመን በኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ ፍጡርን ለመጨረስ የመርዝ ጋዝን ተጠቅሞአል። በዚህ ድርጊቱ የግራዝያኒ ጭፍጨፋ በሚል ነዉ የሚታወሰዉ። በኢትዮጵያ ምናልባትም ከ10,000 ለሚበልጥ ህዝብ እልቂት ተጠያቂ ነዉ» የሪቻርድ ፓንክረስት ባለቤት ወ/ሮ ሩት ፓንክረስትም በበኩላቸዉ «ከሁሉ በፊት ይህ የግራዝያኒ ማስታወሻ የቆመበት ትንሽ ከተማ ከንቲባ እና በምረቃዉ ስነ-ስርአት ላይ በቦታዉ ላይ የነበሩ የቫቲካን ተጠሪዎች በጣም ብዙ ክፉ ስራን የሰራና በርካታ ህዝብን የገደለ ሰዉ ለሽልማት በማብቃታቸዉ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል በሁለተኛ ደረጃ ይህንን የመታሰብያ ቦታ በግራዝያኒ ብትር በ1920ዎቹ በሊቢያ ለተጨፈጨፉ እንዲሁም በመቀጠል በኢትዮጵያ ለሶሶት ተከታታይ ቀናት የግፍ ጭፍጨፋ ለደረሰባቸዉ ኢትዮጵያዉያን እንዲሆን ነዉ። ይህን ያደረገዉ በእሱ ላይ የግድያ ሙከራ ስለተደረገበት ነዉ»  ሪቻርድ ፓንክረስት በመቀጠል ለጣልያን የማስተላልፈዉ መልክት አለኝ ይላሉ
«እዚህ ላይ ለጣልያን የማስተላልፈዉ መልዕክት ለግራዝያኒ ክብር መስጠት አቁሙ ነዉ። በስሙ ያቆሙለትን ማስታወሻም ፍቀዉ አንስተዉ፣ በምትኩ በእሱ እጅ ህይወታቸዉ ለጠፋ ሰዎች ሁሉ ለጣልያንያዉያንም ጭምር ማስታወሻ እንዲሆን ነዉ»
በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ የሆኑት እና ከ1972 ዓ,ም ጀምሮ በተመድ ስር በአስተዳደር መሻሻል በፕሮጀክት መሪነት አስር አገራት ዉስጥ እንዳገለገሉ የነገሩን በአለም አቀፉ ህብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጠሪ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ ህብረታቸዉ በበኩሉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዉን መጀመሩን ነግረዉናል። በወቅቱ የፋሽስት ጦር በተለይ የኢትዮጳያ ባህል በገለጫ አንዱ የሆነዉን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን አዉድሞአል።  የሰዉ ህይወት እና ንብረት ብቻ አይደለም የጠፋዉ፤ ተዘርፈናልም! በዪናይትድስቴትስ ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም ሰምወኑን ጉዳዩን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለመዉጣት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ሙሉዉን ቅንብር ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Äthiopien Yekatit 12 Denkmal in Addis Abeba
የየካቲት 12 መታሰብያምስል DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ