1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያና ጦርነቱ፣

ሐሙስ፣ መጋቢት 15 2003

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፤ በሰሜን አፍሪቃዊቷ ሀገር ሊቢያ ሰማይ ላይ ፣ «የበረራ እገዳ» የሚሰኘውን ውሳኔ ካሳለፈ ወዲህ ፤ ያችው አገር የምዕራባውያን አገሮች አየር ኃይልና ሚሳይል ሲያናፍራት እንሆ 6 ቀን ሆነ።

https://p.dw.com/p/RCIt
ምስል dapd

የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙኧመር ጋዳፊ፤ እስከመጨረሻው እንደሚፋለሙና የሚያሸንፉም መሆናቸውን በንዴት ከመግለፅ የቦዘኑበት ጊዜ የለም። የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አላ ዡፔ፣ የጋዳፊን ጦር ኃይል ለመደምሰስ ቀናት ወይም ሳምንታት እንጂ ወራት አይወስድም ሲሉ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል። ስለሊቢያው ወቅታዊ ይዞታ ተክሌ የኋላ

የምዕራባውያን መንግሥታት ጦር አኤሮፕላኖች፣ ሊቢያን መደብደብ ከጀመሩ፣ ሳምንት ሊሆን ነው። ጋዳፊ በአገራቸው የተቃውሞ ወገኖች ላይ መልሶ የማጥቃት ዘመቻ ማካሄድ መጀመራቸውን ለመግታት፤ በአየር ኃይልና በሚሳይል ተኩስ በተከታታይ ድብደባ እየተካሄደ ሲሆን፤ የብሪታንያው አየር ኃይል (RAF)ምክትል አዛዥ፣ ግሬግ ባግዌል እንዳሉት ከሆነ የሊቢያ አየር ኃይል ተደምስሷል ።

«በአሁኑ ጊዜ፤ የሊቢያን ጦር ኃይሎች ባልተቋረጠ ድብደባ እያስጨነቅናቸው ነው። አየር ኃይላቸው፣ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። የሊቢያ የተቀናጀ የአየር መከላከያ ስልት፣ የእዝና ቁጥጥር መረብ እጅግ ስለተመታ፣ እንዳሻን ፣ በአገሪቱ ሰማይ ላይ ፣እርምጃ መውሰድ ከምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።»

ፈረንሳይና ብሪታንያ ፤ በጦርነቱ ከሚሳተፉ አገሮችና ከተባባሪ የዐረብ አገሮች ጋር አንድ አገናኝ ቡድን ለማቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፤ ይኸው ቡድን፣ ስለፖለቲካዊ አስተዳደርና ስለተልእኮው ስልት የሚመክር ይሆናል ማለት ነው። NATO የየዕለቱን ወታደራዊ እርምጃ ያስተባብራል ተብሏል።

በሊቢያ ላይ የአየር ድብደባው ብቻ አይደለም ተጠናክሮ የቀጠለው። ተጨማሪ የእገዳ እርምጃም እየተወሰደ ነው። የአውሮፓው ኅብረት ጦር መሳሪያ ወይም ወታደሮች ያሣፈሩ አኤሮፕላኖች ወደ ሊቢያ እንዳይበሩ አግዷል። የሊቢያ የነዳጅ ዘይት ኩባንያና የተባባሪዎቹ ድርጅቶች ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ተወስኗል። ዓለም አቀፉ ወታደራዊው ጥምረት አሁን ክዌትንና ዮርዳኖስን ለማቀፍ ይሻል። ባለፈው ሌሊት፤ ትሪፖሊ ውስጥ፣ የአየር መቃወሚያ አውታሮች የተደበደቡ ሲሆን፣ ያካባቢው ኑዋሪዎች እንደገለጹት፣ ሲብሎችም ህይወታቸውን አጥተዋል። የፈረናሳይ መንግሥት ቃል አቀባይ ቲየሪ ቡርክሃርድ እናዳብራሩት፤ ትናንት 15 ያህል የፈረንሳይ አኤሮፕላኖች ተሠማርተው ነበር። ባለፈው ሌሊትም አንድ ደርዘን የሚሆኑ ከሊቢያ የሚድትራንያን ባህር ጠረፍ ወደ የብሱ ግዛት 250 ኪሎሜትር ገደማ ዘልቀው በመብረር አንድ የአየር ኃይል ምሽግ በሚሳይል ደብድበዋል።

ከሊቢያ የሚገኘው ዜና ፤ እንደ መሪው እንደ ሙኧመር ጋዳፊ ባህርይ እርስ በርስ የሚቃረን ነው የሚሉ አሉ። በአገሪቱ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው? የበላይነቱን የያዘ ማን ነው? ትናንት ጋዳፊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሐሳብ አቅርበው ነበር። የአሜሪካ መንግሥት፣ አገኘሁ በሚለው መረጃ መሠረት ደግሞ፣ የሊቢያው መሪ ወደ ሌላ ሀገር የመሰደዱንም ምርጫ ሳያሰላስሉበት አልቀሩም።

ይሁንና፣ «በዓለም ዙሪያ ለእኛ ሲባል፤ በእስያ፤ አፍሪቃ አሜሪካና አውሮፓ የተቃውሞ ሰልፍ እየተደረገ ነው። ህዝብ ከእኛ ጎን ነው። እኛን የሚቃወሙት ግን ጥቂቶች ናቸው» ሲሉ ጋዳፊ መናገራቸው የሚታወስ ነው። አያይዘውም --እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በዚህ ታሪካዊ ጦርነት እንሳተፋለን እጃችንን አንሰጥም። በዚህ ወረራ ፣ ህገ-ወጥ- ወረራ ላይ ፣ በሁሉም ቦታ የተቃውሞ ሰልፍ እየተደረገ ነው።»

በሊቢያ ምሥራቃዊ ከፊል በተለይም የተቃውሞ ኃይሎች ተጠናክረው ከሚገኙበት ትልቅ ከተማ ፣ ቤንጋዚ 160 ኪሎሜትር ፈንጠር ብላ በምትገኘው አጃድቢያ አማጽያኑ አልፎ-አልፎ ሆኗል የሚዋጉት። በመሆኑም የጋዳፊን ኃይል ያን ያህል የሚያሠጉ መስለው አልታዩም። ስለዚህም ፣ የአሜሪካ ው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ለአማጽያኑ ጠንከር ያለ ድጋፍ እንዲሰጣቸው የሚደረግ መሆኑን ሳይጠቆሙ አልቀሩም። ስለጋዳፊም ሲናገሩ--

«--ከሥልጣን እስካልወረዱ ድረስ፤ አሁንም ለሊቢያ ህዝብ አሳሳቢ ሥጋት እንደተደቀነ መቆየቱ የማይቀር ነው። እናም የሊቢያን ህዝብ ለመጠበቅ ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን።»

የምዕራባውያን ተጓዳኝ አገሮች አየር ኃይል በሊቢያ መንግሥት ጦር ኃይል ላይ ብርቱ ጉዳት ቢያደርስም እንኳ ፤ በሚስራታ ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ ነው። ውጊያ ተፋፍሞ የቀጠለው የዐይን ምሥክሮች እንዳሉት፣ በከተማይቱ ዐቢይ ሆስፒታል ዙሪያ ነው። በዚያም አነጣጣሪ ተኳሾች ቢያንስ 16 ሰዎችን በጥይት ገድለዋል። ሲንታንና አጃዳቢያ በተባሉት ከተሞችም የጋዳፊና የተቃውሞው ወገን ጦር በመፋለም ላይ መሆናቸው ተነግሯል።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አላን ዡፔ፣ ከወታደራዊው ይዞታ ሌላ ፣ በሰነዘሩት ፖሊቲካዊ አስተያየት፤ የዐረብ መሪዎች፣ አካባቢውን ያጥለቀለቀውን ለውጥ ፍለጋ ነክ የህዝብ የተቃውሞ ሰልፍ ማዕበል የተሻለ ለውጥ ለማምጣት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል። ሁሉም የዐረብ አገሮች ስዑዲ ዐረቢያ ጭምር፤ የዐረቡን ዓለም ህዝብ የለውጥ ጥማት ሊገነዘቡ ይገባል። ሂደቱ የሚታጠፍ አይደለም።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ