1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ፥አፍቃኒስታንና የኔቶ ልዩነት

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2003

የቃዛፊ ተባባሪ የነበሩ፥ የሕዝብን አመፅ በጠመንጃ ዉጊያ የጠለፉ፥ የጠመንጃዉን ዉጊያ በአለም አቀፉ ድብደባ ያጠናከሩ ወገኖች ለሊቢያ ሕዝብ ፍላጎት-ምኞት ምን ያሕል ተገዢዎች ናቸዉ-ነዉ ጥያቄዉ

https://p.dw.com/p/RTHP
ራስሙስንምስል DW

ሙላሕ ዑመር መሐመድ ከካቡል ቤተ-መንግሥት ከተወገዱ አስረኛ አመት ሊደፍን ወራት ቀሩት።ሳዳም ሁሴን ባደባባይ ከተንጠለጠሉ አምስት አመት ከመንፈቅ ተቆጠረ።ኦስማ ቢን ላደን ከተገደሉ ወር አለፈ።ሙዓመር ቃዛፊ ዳግማዊ ሙላሕ ዑመርን፥ ሳዳም ቢን ላደንን ሊሆኑ የዋሽንግተን፥ብራስልስ-ቤንጋዚ ሹማምንት እንደሚሉት ዕለታት ቢቀራቸዉ ነዉ።ከካቡል እስከ ባግዳድ፥ ከአቦታባድ እስከ ትሪፖሊ የተገኘና የሚገኘዉ ድል ለፀረ-ሽብር ዘመቻ ላበረዉ ዓለም አስደሳች፥ ለአዝማቾቹ አኩሪነቱ በርግጥ አላነጋገረም።አብዛኛዉን ዉጊያ የሚመራዉ ግዙፍ የዓለም የጦር ድርጅት ኔቶ አባል መንግሥታት ካስዘመቱት-ዉጊያ ድል ደስታ-ኩራት ይልቅ በአንድነታቸዉ መላላት መተከዛቸዉ ነዉ አነጋጋሪዉ። የድል-ደስታ ኩራት ትካዜዉን ቅይጥ እዉነት ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁን ቆዩ።

የፈረንሳይ፥ የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥትን ጦር መደብደብ እንደጀመሩ የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አለን ዡፔ የቃዛፊ ዘመነ-ሥልጣን በሳምንታት እንደሚለካ አስታዉቀዉ ነበር።የሰዉ ልጅ አዕምሮ በእስካሁን እድገቱ የፈጥረዉን ምርጥ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ የዓለም ምርጥ ጦር ሊቢያን መደብደብ ከጀመረ ሰወስተኛ ወሩን ሊደፍን እነሆ አምስት ቀን ቀረዉ ዛሬ።ሰዉዬዉ ግን ዛሬም ትሪፖሊ ናቸዉ።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የዛሬ ሰወስት ወር ግድም ያሉትን ባለፈዉ ዕሁድ በሌላ አባባል ደገሙት።«ቃዛፊ ከእንግዲሕ ያለፈዉ የሊቢያ ታሪክ አካል ናቸዉ።መጪዉ ዘመን የሊቢያ ሕዝብ ነዉ»

የትንሺቱ አዉሮጳዉት ሐገር ትልቅ ፖለቲከኛ ያንን የዓለምን ብቸኛ ግዙፍ የጦር ድርጅት እየመሩ ያሉትን የማይሉበት ምክንያት በርግጥ የለም።እና ዕሁድ ያሉትን ማግሰኞም ደገሙት።«ከግጭቱ በሕዋላ ሥለሚደረገዉ ለማቀድ ተስማምተናል።ቃዛፊ ታሪክ ናቸዉ።ከቃዛፊ ይወገዱ ይሆን ወይ ብሎ ጥያቄ ከእንግዲሕ የለም።የሚወገዱት መቼ የሚለዉ እንጂ።ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።ግን ነገም ሊሆን ይችላል።እና ሲወገዱ ለሚደረገዉ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ መዘጋጀት አለበት።»

የትንሺቱ የኔቶ አባል ሐገር ትልቅ ፖለቲከኛ ያሉት እንደሚሆን እርገጠኛ ናቸዉ።«ነገም---»እያሉ የፓሪስ፥ ብራስልስ፥ ዋሽንግተን ወዳጅ አለቆቻቸዉን ካስደሰቱ ግን ሳምንት ተቆጠረ።ሊቢያ ሕዝብ እጅግ ተበታትኖ የሚኖርባት ሐገር ናት።በኮሚዉተር፥ በርቀት መቆጣጠሪያ እና በጨረር የሚታዘዘዉ የሰማይ-የባሕር ሚሳዬል-ቦምብ ሌሎችን ሳይነካ ዒላማዉን ነጥሎ ለመምታት የሚያነቅፈዉ የለም።

Tripolis Gaddafi Libyen Luftangriff NATO
የኔቶ ቦምብ ዉጤት ትሪፖሊምስል picture alliance/dpa

በረጅም ጊዜ ማዕቀብ ምክንያት የታደከመዉ።የበረሐ-ንዳድ አሸዋ ያዛገዉ፥ ያረጀ፥ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ በሕዝባዊዉ አመፅ ምክንያት አዛዥ ጄኔራሎቹ ሳይቀሩ የከዱት የሊቢያ ጦር ዘመናዊ ጠላቱን የቦምብ ሚሳዬል ዉርጂቢኝ ጨርሶ ሊቋቋመዉ አይችልም።ራስሙስን የሚመሩት ድርጅት ረቂቅ የጦር ጄቶች ያላንዳች እንቅፋት በቀን አንድ መቶ ሐምሳ ጊዜ እየበረሩ ያቺን በረሐማ፥ የነዳጅ ሐገር ያነዳሉ።

ሊቢያ በርግጥ ጋይታለች።መንገድ፥ ድልድይ፥ ሕንፃ፥ ከተሞቿ ወድመዋል።እየወደሙም ነዉ።የቃዛፊ ሐይል፥ አማፂያኑ፥ የምዕራባዉኑ ጦር የሚተጋተጉባት ሐገር ዜጎችም እየረገፉ፥ እየቆሰሉ፥ እየተሰቃዩ፥ እየተሰደዱባት ነዉ። ጦርነቱ የሐገሬዉን ሕዝብ፥ ሐብት፥ማጥፋት-ማዉደሙ አልበቃ ብሎ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞችን የቦምብ-ጥይት፥ የበረሐ ንዳድ የዉሐ ማዕበል ሲሳይ እያደረገ ነዉ።በለስ የቀናዉ በርግጥ አዉሮጳ ተሻጋሮ-ቢያንስ ሕይወቱ ተርፋለች።

ኑሮን ከማሸነፍ፥ ችግር ከማቃለል ተስፋ ምኖቹ ጋር እስከወዲያኛዉ የተሰናበተዉን፥ ተደፍራም፥ ተደብድባም ሕይወቷን ያጣችዉን አፍሪቃዊት ስንትነት ቤቱ፥ ቤቷ ይቁጥራቸዉ እንጂ-ከቁም የዶለዉ የለም።ካለም እራሱም በከአለም ሐያላን ዘንድ ከቁብ የማይገበ ጥቂት ደካማም ነዉ።ራስሙስን የድብደባዉን ጥፋት መጠን፥ የጦራቸዉን አይደፈሬነት፥ የጠላት ወዳጆቹን ድክመት-ብርታት በትክክል ያዉቁታል። በበላይነት የሚመሩትን የጦር ድርጅት አንድነት ግን አንድም ዘንግተዉታል፥ አለያም እንደ ፖለቲከኛ መደበቅ ነበረባቸዉ።

ራስሙስን የሚመሩትን ድርጅት ፅናት ተሳትተዉም ሆነ አዉቀዉ ደብቀዉት የቃዛፊን ዘመነ-ሥልጣን በሳምንታት በመለካታቸዉ የለንደን፥ ፓሪስ የበላዮቻቸዉን፥ የቤንጋዚ ተባባሪዎቻቸዉን ማስደሰታቸዉ አልቀረም።የኔቶ መስራች፥መሪም ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ግን የራስሙስን የርግጠኝነት መልዕክት በርግጠኝነት ደስታ አልተቀበለችዉም።ራስሙስን ቃዛፊ ምናልባትም ነገ ይወገዳሉ ባሉ ማግሥት ተረኛዋ ተናጋሪ የዩናይትድ ስቴስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ነበሩ።ሮብ።«ለቃዛፊ በሚቀርቡ ሰዎች መካካል በርካታና ተካካይ ዉይይቶች እየተደረጉ ነዉ።ይሕን እናዉቃለን። ዉይይቶቹ ከሚያካትቷቸዉ ነገሮች አንዱ ለሽግግር የሚመች ሁኔታ አለበት።»

ሰዉዬዉ አሁንም በነበሩበት አሉ።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ።ከፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እስከ ፕሬዝዳት ኒካላይ ሳርኮዚ፥ ከጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን እስከ ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ያሉ መሪዎች በተደጋጋሚ እንደተናገሩት ጦራቸዉ የሊቢያን መንግሥት ጦር የሚወጋዉ የሊቢያን ሕዝብ ከቃዛፊ ጦር ጥቃት ለመከላከል፥ የተባበሩት መንሥግሥታት ድርጅትን ዉሳኔ ለማስከበር ነዉ።

Nato Angriff auf von Taliban entführten Tanklaster
የኔቶ ድብደባ አፍቃኒስታንምስል AP

የቀድሞዉ የሊቢያ የፍትሕ ሚንስትር እና ያሁኑ የአማፂያን መሪ ሙስጠፋ መሐመድ አብደል-ጀሊልም በዚሕ ይስማማሉ።ደብዳቢዉን ጦር ያዘሙት መንግሥታት፥ መሪዎች በደብዳቢዉ ጦር የሚታገዙት አማፂያን በተደጋጋሚ ያሉት እንዳይዘነጋ ይመስላል የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን ባለፈዉ ዕሁድ በተደጋጋሚ ያሉትን እንደገና ብለዉት ነበር።«ለሊቢያ ሕዝብ ያለን መልዕክት ግልፅ ነዉ።ኔቶና ተባባሪዎቹ ከጥቃት ይከላከላችኋል።ለቃዛፊ ሥርዓት ያለን መልዕክትም ግልፅ ነዉ።ዘመቻዉን ጀምረነዋል እንፈፅመዋለንም።»

በኔቶ ድብደባ፥ በአማፂያኑ ዉጊያ ከኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አገዛዝ የሚላቀቀዉ የሊቢያ ሕዝብ የሚከፍለዉን መስዋዕት ከፍሎ እንዳጠናቀቀ፥ በነፃነት፥ በሠላም፥ በፍላጎቱ በሚመርጠዉ መንግሥት ይተዳደራል ነዉ ቃል፥ ተስፋ-ምኞቱ።አማፂያኑ ግን ካሁኑ «የሽግግር» ያሉትን መንግሥት መሥርተዋል።ለዲሞክራሲ የቆሙት፥ ለዲሞክራሲ የሚዋጉት ዲሞክራሲያዉያኑ መንግሥታትም ያለ ምርጫ በጠመንጃ ታጣቂዎች ስብስብ ለተመሠረተዉ የሽግግር መንግሥት ሙሉ እዉቅና ሰጥተዋል።

የቤንጋዚን ርዕሠ-ከተማነት አፅድቀዉ ፅፈት ቤት ከፍተዋል።ሕዝብን እየጨቆኑ፥ የሕዝብን ጥያቄ እየጨፈለቁ፥ ፍትሕን እየደፈለቁ ከአርባ ዘመን በላይ ለገዙት ለኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ሥርዓት በሚንስትር ያዉም በፍትሕ ሚንስትርነት ያገለገሉት ሙስጠፋ መሐመድ አብዱጀሊል እንደ ሐገር መሪ የመንግሥታቸዉን እቅድ አላማ መዘርዘር የጀመሩት ገና የሽግግር የተባለዉ ምክር ቤት ከመመስረቱም በፊት ነበር።

አብዱጀል ባለፈዉ መጋቢት አጋማሽ ፋይናንሻል ታይምስ ለተሰኘዉ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ በይፋ የሚባለዉን ሳይሆን በተግባር የሚሆንና የሚደረገዉን በግልፅ ነበር ያስታወቁት።ሊቢያዊዉ ፖለቲከኛ ለዲሞክራሲ የሚዋጉ መንግሥታትን ትክክለኛ ፍላጎት ማወቃቸዉንም ገና ያኔ ነበር ያመሰከሩት።

እሳቸዉ ምናልባት ከሚንስትርነትም በላይ ከፍ ባለ ማዕረግ የሚያዙት የወደፊቱ የሊቢያ መንግሥት የሐገሪቱን የነዳጅ ዘይት የሚያኮናትረዉ ተኮናታሪዎች ቃዛፊን ለማስወገድ በሚደረገዉ ዉጊያ ለአማፂያኑ በሚሰጡት ድጋፍ መጠን እየለካ ነዉ።በአብዱጀሊል ስሌት-እቅድ መሠረት የወደፊቱ መንግሥታቸዉ ነዳጅ ዘይት ከሚያከፋፍላቸዉ መንግሥታት ከፍተኛዉን ድርሻ የሚወስዱት በድብደባዉ የተካፈሉት ስምንቱ የኔቶ አባል ሐገራት ናቸዉ።ቤልጂግ፥ብሪታንያ፥ካናዳ፥ ዴንማርክ፥ ፈረንሳይ፥ኢታሊ፥ኖርዌ እና ዩናይትድ ስቴትስ።

ከሃያ ስምንቱ የኔቶ አባል ሐገራት ሃያዉ በድብደባዉ በቀጥታ አልተካፈሉም።ይሕ አብዱጀሊል እንዳሉት ወደፊት የሊቢያን ነዳጅ ዘይት ለመቀራመት ለሥምንቱ ሐገራት ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩ አልቀረም። ከዚያ የሚደረስበት መንገድ ዡፔ፥ ራስሙስን ቃል እንደገቡት፥ አብዱጀሊል እንዳሰቡት ቀላል አለመሆኑ እንጂ ጭንቁ።

ኔቶ በጥቅል አቅሙ ከሁለት ሚሊን በላይ ጦር ያዛል።የሃያ-ሰባቱ ሐገራት ጦርና የጦር መሳሪያ ቢደመር ግን በብዛትም፥ በጥራትም ያንዲት ዩናይትድ ስቴትስን አያክልም።አፍቃኒስታን ዉስጥ ከሚዋጋዉ ወደ 140 ሺሕ ከሚገመተዉ የኔቶ ጦር ሃያ-ሰባቱ ሐገራት ያዘመቱት ቢደመር ከአርባ ሺሕ ብዙ አይበልጥም።የተቀረዉ የአሜሪካ ነዉ።ብዙ የሚሞተዉም አሜሪካዊ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቁ ጦርነት ከስምንት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሳለች።ለአፍቃኒስታኑ ዉጊያ ደግሞ ወደ አምስት መቶ ቢሊዮን።

የሊቢያዉን ድብደባ ሰወስት አራተኛዉን ወጪ የምትሸፍነዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ድብደባዉ የፊታችን ቅዳሜ ሰወስተኛ ወሩን ሲደፍን አሜሪካ ያወጣችዉ ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይቆጠራል።የተቀሩት ሰባቱ ሐገራት ለሊቢያዉ ድብደባ ያወጡት ቢደመር ሁለት መቶ ሐምሳ ሚሊዮን አይበልጥም። ተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ጌትስ ባለፈዉ አርብ ለሃያ-ሰባቱ አቻዎቻቸዉ እንደነገሩት አሜሪካኖች ይሕን ሁሉ ተሸክመዉ ኔቶ በእስካሁን ጉዞዉ መቀጠሉ አጠራጣሪ ነዉ።

«በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትና በአሜሪካ ፖለቲካዊ አካል ዉስጥ ባጠቃላይ አስፈላጊዉን ሐብት ለማዋጣት ለማይፈቅዱ ወይም አስፈላጊዉ ለዉጥ እንዲደረግ ከልብ ለማይጥሩና የራሳቸዉን ደሕንነት ለማስጠበቅ ፍላጎቱና አቅሙ ለሌላቸዉ መንግሥታት እጅግ ዉድ የሆነዉን ገንዘብ ማዉጥ የለበንም የሚለዉ ስሜት ሥር እየሰደደ መጣቱ የፈጠጠ ሐቅ ነዉ።አዉሮጳ ዉስጥ በተደረገዉ የመከላከያ በጀት የጎደለዉን ለማሟላት የአሜሪካ ቀረጥ ከፋዮችን ገንዘብ ማዉጣቱ አያስፈልግም የሚለዉ አስተሳሰብ እየዳበረ ነዉ።»

የቃዛፊን መወገድ ከጥቂት የሥርዓታቸዉ ተተቃሚዎች ባለፍ የሚጠላ በርግጥ የለም።የቃዛፊ ተባባሪ የነበሩ፥ የሕዝብን አመፅ በጠመንጃ ዉጊያ የጠለፉ፥ የጠመንጃዉን ዉጊያ በአለም አቀፉ ድብደባ ያጠናከሩ ወገኖች ለሊቢያ ሕዝብ ፍላጎት-ምኞት ምን ያሕል ተገዢዎች ናቸዉ-ነዉ ጥያቄዉ።

ሙላሕ ዑመር በተወገዱ ማግሥት የካቡልን ቤተ-መንግሥት ከዋሽንግተኖች የተረከቡት ሐሚድ ካርዛይ አፍቃኒስታንን ሙላሕ ዑመር ከገዙት ዘመን በላይ እየገዟት ነዉ።ካርዛይ ተመረጡ መባላሉን እንጂ የመረጣቸዉን ሕዝብ ፍልጎት ማሟላታቸዉን የሚያዉቅ የለም።የሳዳም ሁሴን ሐዉልት ከባግዳድ አደባባይ ሲገነደስ አብዛኛዉ ኢራቃዊ ጨፍሮ፥ ፈንድቆ ነበር።ከቦምብ ጥይት አረር ተርፎ ሐዉልቱ የተገነደሰበትን አምስተኛ አመት ለመዘከር የታደለዉን ቤቱ ይቁጥረዉ።

ኔቶ ፈጠነም ዘገየ-አንድነቱን መጠበቁ አይቀርም።ቃዛፊም ዳግም ሙላሕ ዑመር፥ ሳዳም፥ ወይም ቢን ላደንን መሆናቸዉ አላከራከረም።የድሕረ-ቃዛፊዋ ሊቢያ የዛሬዋን አፍቃኒስታን፥ኢራቅ ወይም ፓኪስታን ላለመሆንዋ ምንም ዋስትና አለመኖሩ ነዉ-ጭንቁ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።


ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ