1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ አሳዳሪ ያጣች ሐገር

ሰኞ፣ የካቲት 16 2007

የሕዝቧን መሠረታዊ ፍላጎት አሟልታ በማኖር ከአፍሪቃ አቻ ያልነበራት ሐገር ዛሬ የአሸባሪዎች፤የጎጠኞች፤ የሽፍቶች፤የስደተኛ አስተላላፊዎች፤ የዘራፊዎች መናኸሪያ ሆናለች።ከአራት ዓመት በፊት አንድ መሪ ነበራት።ዛሬ አስራ-ሰባት ሺሕ መሪዎች የሚያዙት አስራ-ሰባት ሺሕ ታጣቂ ቡድናት ይርመሰመሱባታል።

https://p.dw.com/p/1EgET
ምስል Getty Images/AFP/M.Turkia

ከሜድትራኒያን ባሕር ደቡባዊ ጥግ-እስከ ሠሐራ በረሐ ወገብ የሚወርድ ሠፊ ግዛትን የምታዋስን አንድ ሐገር ነበረች።ድሆች የከበቧት፤ በረሐማ ግን ሐብታም ሐገር።ሊቢያ የሚሏት።እስከ ዛሬ አራት ዓመት ድረስ አንድ ጠንካራ መሪ፤ አንድ መንግሥት፤ አንድ ብሔራዊ ጦር ነበሯት።የዛሬ አራት ዓመት የዘመተባት የዓለም ምርጥ ጦር ከዓየርና ከባሕር ባወረደባት ቦምብ ሚሳዬል ሐብት ንብረትዋን አዉድሞ፤ ዜጎችዋን ፈጅቶ፤ መሪዋን ከነ-ሥርዓታቸዉ እጥፍቶ ዉልቅ አለባት።ዛሬ ሁለት መንግሥት፤ ሁለት ጠቅላይ ሚንስትር፤ ሁለት ምክር ቤት፤ 1700 የጦር ቡድናት ይፈነጩባታል።ሊቢያ፤ ሐብት-ዕዳ፤ ብልፅግና ጥፋት፤ ሥልታዊነት መከራ የሆነባት ሐገር።

ጥቅምት 20 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሰዉዬዉ ቆሰሉ፤ ተማረኩ፤ ወዲያዉ ተገደሉ።ለሰባት ወራት ሊቢያን ሲቀጠቅጥ ለነበረዉ ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አዛዦች ታላቅ ፌስታ፤ በተለይም ጦሩን ላዘመቱት ለፓሪስ-ለንደን-ለዋሽግተን-መሪዎች ከፍተኛ ድል ነበር።የሊቢያ ሕዝብም ከዋሽንግተን አዲስ ተስፋ ተንቆረቆረለት።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ።

«ይሕ ለሊቢያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ የሥቃይ ምዕራፍ ፍፃሜ ነዉ።ከእንግዲሕ የሐገሪቱ ሕዝቦች በአዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ሊቢያ የራሳቸዉን መሳኤ ዕድል መወሰን ይችላሉ።የጋዳፊ ሥርዓት ለአራት አስርታት ሊቢያን በብረት ጡንቻ ገዝቷል።መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ተገፈዋል።ንፁሐን ሰላማዊ ሰዎች ታሥረዋል።ተገርፈዋል።ተገድለዋል።የሐገሪቱ ሐብት ተመዝብሯልም።ሽብር እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አገልግሏል።ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ ከነበሩት አምባገነኞች አንዱ ከእንግዲሕ ተወግደዋል።ይሕ በሊቢያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ አለዉ።የሊቢያ ሕዝብ ከቃዳፊ ሥርዓት ጋር ጨርሶ የሚቃረን ሁሉን አቀፍ፤ ሁሉን አቻችላ የምታኖር ዴሞክራሲያዊት ሊቢያን የመገንባት ሐላፊነት አለበት።»

Libyen vor UN-Sicherheitsrat Gross Waffen IS
ምስል AP

ከቃላት ባለፍ በገቢር ምንም ያልነበረዉ የሠላም የዲሞክራሲ፤ የፍትሕ ተስፋ ከበነነ ከረመ።ዴሞክራሲዊ ሥርዓት እንገነባለን ብለዉ የፓሪስ፤ ለንደን ዋሽንግተኖችን ድጋፍ ለማግኘት ሲባትሉ የነበሩት ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል፤መሐመድ ጅብሪል፤ አብዱል አዚዝ ጎሐግና ብጤዎቻቸዉ ሐገር ሕዝባቸዉን አመሰቃቅለዉ ከፖለቲካዉ መድረክ ከጠፉ ዓመታት ተቆጠሩ።

የነሙስጠፋ አብዱል ጀሊልን የአማፂ ቡድናት ስብስብን ደገፎ ሊቢያን የደበደበዉ የሠሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አላም ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን እስከ-መግደል ማስገደል ከነበረ በርግጥ ተሳክቶለታል።ኦባማ እንዳሉት ሰላም፤ ዴሞክራሲ፤ ፍትሕ ማስፈን ከነበረ ግን የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ በርግጥ ዉል ስቷል።

የሕዝቧን መሠረታዊ ፍላጎት አሟልታ በማኖር ከአፍሪቃ አቻ ያልነበራት ሐገር ዛሬ የአሸባሪዎች፤የጎጠኞች፤ የሽፍቶች፤የስደተኛ አስተላላፊዎች፤ የዘራፊዎች መናኸሪያ ሆናለች።ከአራት ዓመት በፊት አንድ መሪ ነበራት።ዛሬ አስራ-ሰባት ሺሕ መሪዎች የሚያዙት አስራ-ሰባት ሺሕ ታጣቂ ቡድናት ይርመሰመሱባታል።

እንደ አንድ ሐገር አንድ መንግሥት ነበራት።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከነሥራዓታቸዉ ከተገደሉ ከ2011 ጀምሮ አምስት መሪዎችና መንግሥታት ተፈራርቀዉባታል።ዛሬም ርዕሰ-ከተማ ትሪሊፖሊ ላይ አንድ መንግሥትና አንድ ምክር ቤት አላት።ቶብሩክ ላይ ደግሞ ሌላ መንግሥትና ሌላ ምክር ቤት አላት።መንበሩን ቶብሩክ ያደረገዉና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እዉቅና ያገኘዉ መንግሥት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ አል ዳይሪ እንደሚያምኑት ዓለም አቀፉ ድርጅት በመንግሥታቸዉ ላይ የጣለዉ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ቢነሳ የሊቢያን ችግር ማቃለሉ አይገደዉም።

«ሊቢያ፤ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ወሳኝ እርምጃ ትሻለች።የራስዋን ብሔራዊ ጦር ሐይል መገንባት ትችል ዘንድ የተጣለባት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ሊነሳላት ይገባል።»

USA UNO Konferenz Libyen
ምስል Getty Images/A. Burton

የዳይሪ መንግሥት ትንሺቱ የወደብ ከተማ ቶብሩክ ለመሸሸግ የተገደደዉ ሊቢያን አይደለም ርዕሠ-ከተማ ትሪፖሊን እንኳ መቆጣጠር አቅቶት ነዉ።በትሪፖሊና በቶብሩክ መካከል አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ተዘርግቷል።አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትሩን የሞሉት ደግሞ እስካፍንጫቸዉ የታጠቁ፤በጎሳ፤ በጎጥ፤ በሐይማኖታዊ አስተሳሰብ የተከፋፈሉ፤ የኮሎኔል ሙዓመር ጦር ባልደረቦች የነበሩ፤ ታጣቂዎች ናቸዉ።

የቶብሩኩ መንግሥት በተቀናቃኞቹ የሚሰነዘርበትን ጥቃት የሚከላከለዉ ደግሞ ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍትር የሚመሩት ጦር ነዉ።ሐገር መንግሥታቸዉን ከድተዉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እስከ ኮበለሉበት ጊዜ ድረስ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ታማኝ የጦር መኮንን የነበሩት ሐፍትር የትሪፖሊንም፤ የቶብሩክንም መንግሥታት ፈነጋግለዉ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ለማስፈን እያደቡ ነዉ።

ለዚሕ ግባቸዉ ስኬት በሕዝብ የተመረጠ መሪ በሐይል አስወግደዉ የግብፅን የመሪነት ሥልጣን የያዙትን የጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ሲሲን ሙሉ ደጋፍ በሲሲ በኩልም የሳዑዲ አረቢያና የአረብ ኤሚሬቶች የጦርና የገንዘብ ርዳታ ይንቆረቆርላቸዋል።

«እዚያ ሊቢያ ከሶሪያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል፤ በምዕራቡ ፖለቲካዊዉ ሥርዓት ብዙም ያልተለመደ ነገር ይታያል።እስላማዊ ቡድናት አሉ።ወንጀለኛ ሚሊሻዎች አሉ።የቀድሞ ጦር ባልደረቦች አሉ።ኸሊፋ ሐፍታር ዋነኛዉ ናቸዉ።ከግብፅ፤ ከአረብ ኤምሬቶች እና ከሳዑዲ አረቢያ ርዳታ ይደረግላቸዋል።(አላማቸዉ) ለሐያማኖት ያልወገነ ወታደራዊ አምባገነን መመሥረት ነዉ።»

Anschlag in Bengasi Libyen
ምስል Reuters/E. Omran Al-Fetori

ይላሉ ጀርመናዊዉ የሽብር ጉዳይ አጥኚ ጊዶ ሽታይንበርግ።የግብፅና የአረብ ኤሜሬቶች የጦር ጄቶች መንበሩን ትሪፖሊ ያደረገዉን መንግሥት የሚደግፉትን ሚሊሻዎች በተደጋጋሚ የሚደበድቡትም ሲሆን ሐፍትርን ይሕ ቢቀር ሐፍትርን የሚደግፉ ሐይላትን ትሪፖሊ ቤተ-መንግሥት ለመዶል ነዉ።

ጄኔራል አል ሲሲ ከዚሕም ሌላ ትልቅ አላማ አላቸዉ።በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን መያዛቸዉን ከሚቃወሙ በተለይም ከሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር አባላት የሚደርስባቸዉን ወቀሳ፤ትችትና አመፅን ለመሸፈን ይጠቀሙበታል።

ይሁንና የአልሲሲ እርምጃ ለሊቢያ ደፈጣ ተዋጊ ቡድናት በተለይም ለፅንፈኞቹ ሐይላት ሰበብ ምክንያት ሆኖ ሲርት ዉስጥ 21 የግብፅ ኮፕቲክ ክርስቲያኖችን እስገድዷል።ከኮብቶቹ መገደል በሕዋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊቢያ አማፂያንን የሚወጋ ጦር እንዲያዘምት የካይሮ ገዢዎች እንከመጠየቅ ደርሰዉ ነበር።

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የጦር መሳሪ ማዕቀብ ይነሳ የሚለዉን የቶብሩክ መንግሥትንም ሆነ ዓለም ቀቀፍ ጦር ይዝመት የሚለዉን የካይሮዎችን ጥያቄ አልተቀበለዉም።ምክንያቱ ሁለት ነዉ።የመጀመሪያዉ ሊቢያ ጠንካራ መንግሥት የላትም የሚለዉ-አንድ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀናቃኝ ሐይላትን ለማስታረቅ የጀመረዉ ጥረት ይደናቀፋል የሚለዉ-ሁለት።

የአል-ሲሲ መንግሥት ግን ሊቢያን ማስደብደቡን እንደቀጠለ ነዉ።የግብፅን ጣልቃ ገብነት ቀጠርና ቱርክ በግልፅ ሲቃወሙት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና ሳዑዲ አረቢያ ለድብደባዉ ስኬት ሙሉ ድጋፋቸዉን እየሰጡ ነዉ።

ምዕራባዉን መንግሥታት የሊቢያ ሉዓላዊነት መደፈርም ሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸዉ የገጠሙት የእጅ አዙር ጦርነት ብዙም ያሳሰባቸዉ አይመስልም።ሶሪያ እና ኢራቅ ዉስጥ ሰፋፊ ግዛቶችን የሚቆጣጠረዉ እስላማዊ መንግሥት የተሰኘዉ አሸባሪ ቡድን ሊቢያ ዉስጥም እየተደራጀ ነዉ መባሉ ግን በተለይም የአዉሮጳ መንግሥታትን እያሳሰበ ነዉ።

የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ አዉሮጶች ከሊቢያ የሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠዉ ከሚገቡ የአረብና የአፍሪቃ ስደተኞች ጋር አሸባሪዎችም ወደ አዉሮጳ ሊሻገሩ ይችላሉ የሚል ሥጋት አድሮባቸዋል።

Libyen Sirte Unruhen IS
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. B. Khalifa

የአረብ ሊግ ዋና፤ ዋና አባላቱ ፤ አባሉ የሆነችዉን ሊቢያን ሲያመሰቃቅሉ ሊጉ ራሱ የሌለ ያክል ድምፁን አጥፍቷል።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጦር ሊቢያን መዉረሩን አጥብቆ ተቃወሞ የነበረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ከሰሐራ በረሐ በስተ-ሰሜን የምትገኝ አባሉን ለማየት በረሐዉ የጋረደዉ መስሏል።

ሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ ከተቀሰቀሰባት-ከየካቲት 2011 ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ እስከተገደሉበት እስከ ጥቅምት 2011-በተቆጠረዉ ስምንት ወር ግድም ከአስራ-አራት ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቆባታል።ቃዛፊ ከተገደሉበት-ሁለት መንግሥት እስከተመሠረተበት እስካለፈዉ ግንቦት ድረስ ሁለት ሺሕ ሰዎች ተገድለዋል።ከአምና ግንቦት እስካለፈዉ ጥር ድረስ አራት ሺሕ ሰዉ አልቆባታል።ዛሬም ትነዳለች።አሳዳሪ ያጣች ሐገር።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ