1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ ፣ ግድያና ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2003

በሊቢያ ሰልፈኞች ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሏል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል እያለ ነው። ቱርክ ለሊቢያ ባለስልጣናት ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰዳለች።

https://p.dw.com/p/R3Ap
ጋዳፊ ከዓለም ዙሪያ ተቃውሞ ገጥሞአቸዋልምስል picture alliance/dpa

ዓለም በአንድ ድምጽ በአንድ ቃል እጅግ አሳዛኝ ፈጽሞ መደረግ የሌለበት ሲል ከዳር እስከ ዳር አወገዘው። ቱኒዚያ ተጀምሮ፤ ግብጽ ላይ ተፋፍሞ ወደ ሌሎች ሀገራት የተዛመተው የህዝብ ቁጣ ሶስተኛውን መሪ ከቤተመንግስት ገፍትሮ ሊያስወጣ የተቃረበ በሚመስልበት በሰሞኑ ሊቢያ ላይ ቀውሱ ከፍተኛ እልቂትን አስከትሏል። 41ኛ ዓመት ስልጣናቸውን እያገባደዱ ባሉት የ68 ዓመቱ የሊቢያ መሪ ኮነሬል ሞሃመድ ጋዳፊ ላይ የተቀስቀሰው ተቃውሞ ከሁለተኛዋ ከተማ ቤንጋዚ ወደ ዋናዋ ከተማ ትሪፖሊ ሲቀጣጠል በእርግጥ ልጃቸው ሳይፍ ጋዳፊ አንድ ሰው አንድ ጥይት እስኪቀር እንፋለማታለን ካሉ ወዲህ ነበር ቀውሱ ተካሮ ዕልቂቱም ተጠናክሮ የቀጠለው። በቱኒዚያና በግብጽ የቅርብ ጊዜ አብዮቶች የተደመመው ዓለም በሊቢያው ዕልቂት ይረበሽ ይደናገጥ ይዟል። ትላንት የአውሮፕላኑ ጥቃት እንደተፈጸመ መግለጪያ የሰጡት የመንግስታቱ ድርጅት ባንኪሙን በህዝቡ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።

ድምጽ

«የሊቢያ ባለስልጣናት ከጦር አውሮፕላን ህዝቡ ላይ ሲተኩሱ ነበር። ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። በአስቸኳይ መቆም አለበት።»

ትላንት ሰኞ ለ40 ደቂቃዎች ከጋዳፊ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩበት የገለጹት ባን ኪሙን በግብጽና በቱኒዚያ የህዝብ ተቃውሞ ያመጣውን ለውጥ በግልጽ ለጋዳፊ አስርድቼአቸዋለሁ ብለዋል። የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በዚሁ የሊቢያ ዕልቂት ላይ ለመነጋገር ዛሬ ስብሰባ ጠርቷል። አሜሪካ የጋዳፊን እርምጃ በማውገዝ ዕልቂቱን ለማስቆም ጋዳፊ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ጠይቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ትላንት በሰጡት መግለጪያ የሊቢያ መንግስት ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅና የመሰብሰብ መብትን የማክበር ግዴታ አለበት ሲሉ አሳስበዋል። የአውሮፓ ሀገራት ውግዘት ተቃውሞአቸውን ማሰማት የጀመሩት ቤንጋዚ በተቃውሞ መናጥ፤ ሰላማዊ ሰው ላይም መንግስት እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ነው።  የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ካተሪን አሽተን የሰላማዊ ህዝብ መገደል  እንደተለመደው በተለመደው ቃል አሳስቦናል አሉ- ትላቱኑ።

Libyen Unruhen Gaddafi Tripolis 20.02.2011
ምስል picture alliance/dpa

ድምጽ

« በሊቢያ እየተጸሙ ያሉት ድርጊቶች በጽኑ አሳስበውናል። ሰላማዊው ሰልፈኛ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃና ግድያ እናወግዛለን።»

ጀርመን ጠንከር ያለ በጨረፍታም የጋዳፊ መንግስት ስልጣኑን እንዲለቅ የሚያሳይ መግለጪያ ነው የሰጠችው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬሌ ዛሬ እንዳሉት የጋዳፊ ቤተሰብ የሚመራውን ህዝብ በእርስ በእርስ ጦርነት እያስፈራራ ነው። ሰላማዊ ህዝብ ከአውሮፕላን ሲደበደብ በመትረየስ ሲጨፈጨፍ ዝምብለን ማየት አንችልም ብለዋል። ጋዳፊ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸውም በተዘዋዋሪ የጠይቁት ቤስተር ቬሌ በሊቢያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ አድርገዋል። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን የአረብ ሀገራትን በሚያካልለው ጉብኝታቸው ላይ እንዳሉ በሰጡት መግለጪያ የጋዳፊ እርምጃ የበለጠ ጥፋትን ከማስከተል ያለፈ ውጤት የለውም ብለዋል።የሩሲያው ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በሊቢያው ሰሞንኛ ዕልቂት ላይ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ በአጠቃላይ ሰሜን አፍሪካንና መካከለኛው ምስራቅን እያመሰው ያለው የለውጥ ንቅናቄ ያሰጋቸው መሆኑን ነው የገለጽት። ጽንፈኞች የአረብ ሀገራትን ወደ ቁርጥራጭ መንግስታት ቀይረው ሃይሉን የሚጨብጡበት ዕድል ሊኖር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገለጹ ሚድቬዴቭ። ቱርክ የትላንቱ የአውሮፕላን ጥቃት ለሊቢያ ባለስልጣናት የማስጠንቀቂያ ደውል ነው ነበር ያለችው። የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር የሊቢያ ባለስልጣናት የህዝብን ጥያቄና ፍላጎት ወደጎን አድርገው እየፈጸሙ ባሉት ከባድ ስህተት ሃላፊነት ሊወስዱ ይገባል በማለት በማስጠንቀቂያ የታጀበ መግለጪያ ሰጥተዋል። የቀድሞ የሊቢያ ቀኝ ገዢ ኢጣሊያን እየደረሰ ካለው ዕልቂት ይልቅ የአመጹ እምብርት በሆነችው ቤንጋዚ እየሆነ ያለው አሳስቧታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንኮ ፍራቲኒ በቤንጋዜ እስላማዊ አስተዳደር መዋቀሩ ከባድ ስጋት ብለውታል።

ድምጽ

«በቤንጋዜ የተዋቀረው እስላማዊ የራስ አስተዳደር አዋጅ ፍጹም አሳስቦኛል። በአውሮፓ ደንበሮች ጫፍ ላይ እስላማዊ የአረብ መንግስት ሲመሰረት ሊሆን የሚችለውን አስበኸው ታውቃለህ? ይሄ ነው ከፍተኛው ስጋት።»

በእርግጥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተፈጸመ ያለው የሰላማዊ ሰው ዕልቂት ያሰጋው ዓለም እያወገዘ እያሰጠነቀቀ እንጂ እስከአሁን ገፍቶ የሄደበት እርምጃ የለም። የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሊቢያ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ከማውገዝ ያለፈ ጋዳፊን ከስልጣን ማስወገዱ የእኛ ጉዳይ አይደለም ማለታቸው፤ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ እስከየት ለመሆኑ አመላክቷል።

ድምጽ

«አሁን ያለንበት ሁኔታ እንደሚመስለኝ ለምሳሌ የሊቢያውን ጉዳይ ብንመለከት እርምጃውን ማውገዝ ብቻ ነው የምንችለው። በዚሁ አንጻርም የሊቢያውን መሪ የመለወጡ ስራ የእኛ አይደለም። ህዝቡን ማዳመጥ ያለበት የሊቢያ አስተዳደር ነው። እውነት ለመናገር ህዝብን ማዳመጥ ማለት የጦር መሳሪያ መጠቀም ማለት አይደለም።»

Libyen Unruhen Gaddafi Bengasi 20.02.2011
ምስል picture alliance/dpa

ቤንጋዚ ከጋዳፊ እጅ ወጥታለች። ትሪፖሊ ተነቅንቃለች። ጋዳፊ አለሁ። የትም አልሂድኩም እያሉ ነው። ሚኒስትሮቻቸው አምባሳደሮቻቸው ወታደራዊ ሹሞቻቸው ጀርባቸውን ይሰጡ ጀምረዋል። በየአቅጣጫው ጋዳፊን መክዳቱ ቀጥሏል። ህዝቡም እየሞተ ወይ ፍንክች እንዳለ ነው። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በሊቢያ እየሆነ ያለው እንዳሳሰበው መሆኑን ከመግለጽ ያለፈ በእርግጥ እስከአሁን የወሰደው እርምጃ የለም። ምናልባት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የጋዳፊ እርምጃ በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል ማለቱ ምናልባት ለጊዜ ጠንከር ያለው መግለጪያ ይሆናል።

Mesay Mamo

Hirut Melesse