1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ላይቤሪያ እና የኢቦላ ትግል

ሰኞ፣ የካቲት 30 2007

ላይቤሪያ ከገዳዩ የኢቦላ ተህዋሲ ነጻ የምትሆንበትን ቀን በጉጉት እየጠበቀች ነው። ባለፈው ሳምንት የመጨረሻዋ የኢቦላ ህመምተኛ ከሆስፒታል ወጥተዋል።ላለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ የኢቦላ ህመምተኛ አለመገኘቱ ተሰምቷል።ባለፈው አመት በምዕራብ አፍሪቃ የተከሰተው የኢቦላ ተህዋሲ ወረርሽኝ ከሶስት ሺ በላይ ላይቤሪያውያንን ለሞት ዳርጓል።

https://p.dw.com/p/1Enl3
Afrika Ebola in Liberia (Symbolbild)
ምስል Z. Dosso/AFP/Getty Images

የኢቦላ ተህዋሲን ወረርሽኝ ለመግታት ለአንድ አመት ያህል ትንቅንቅ ውስጥ የከረመችው ላይቤሪያ ለድል የቀረበች ይመስላል። በተህዋሲው ተይዘው የነበሩት የ58 አመቷ መምህርት ቢያትሪስ ያርዶሎ በቻይናውያን የኢቦላ ህክምና ማዕከል የሚደረግላቸውን ክትትል አጠናቀው ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል። መምህርቷ ከኢቦላ በ21 ቀን ውስጥ ቢያገግሙም ልጃቸውን በተህዋሲው በሞት ተነጥቀዋል። ከኢቦላ ተህዋሲ ነጻ በመሆናቸው ደስታቸውን የሚገልጹት ቢያትሪስ ያርዶሎ ላይቤሪያውያን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራሉ።

«አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉን መቀጠል አለባቸው። ልጄ ለሞት ከመዳረጓ በፊት የታመመችው በኢቦላ መሆኑን አናውቅም ነበር።»
ቢያትሪስ ያርዶሎ በተህዋሲው የተያዙት የታመመች ልጃቸውን ሲንከባከቡ መሆኑን እና በኢቦላ መታመሟን አለማወቃቸውን ተናግረዋል።የመምህርቷ ቢያትሪስ ያርዶሎ ከኢቦላ ነጻ መሆን በላይቤሪያ ከተህዋሲው ጋር ለሚደረገው ትግል መሰረት መሆኑን የሃገሪቱ ረዳት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና የኢቦላ ክትትል እና ቁጥጥር ማዕከል ሃላፊ ቶልበርት ኒዬንስዋህ ይናገራሉ።

«የቻይና የኢቦላ ህክምና ማዕከል ነጻ መሆናቸው የተረጋገጠውን የመጨረሻ ህመምተኛ ወደ ቤታቸው ሸኝቷል። ላለፉት አስራ ሶስት ቀናት አዲስ የኢቦላ ህመምተኛ አልተገኘም። ይህ ጥሩ ዜና ነው። ሁላችንም ደስተኞች ሆነናል። ይህን ለ21 ቀናት እስከ መጋቢት 12 ከዛም ለ42 ቀናት እስከ ሚያዝያ ይዘልቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህም የዓለም ጤና ድርጅት በሁኔታው እርግጠኛ ይሆናል በላይቤሪያም በላይቤሪያ የኢቦላ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ይውላል ብለን እንጠብቃለን።»
ቶልበርት ኒዬንስዋህ ከኢቦላ ተህዋሲ የተፈወሱት የመጨረሻ ህመምተኛ ነጻ መባል ኢቦላ ከላይቤሪያ ጠፋ ማለት አለመሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ። የላይቤሪያ ዜጎች የኢቦላን ወረርሽኝw በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰራው ስራ ደስተኛ ቢሆኑም ብዙዎች ደህና ነኝ በማለት የሚደበቁ ህሙማን ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

«ለሁሉም ሰዎች እና የታመሙ ሰዎች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ራሳችሁን አትደብቁ። ገና ህመም ሲጀምራችሁ ለህክምና ማዕከላት አሳውቁ። ህክምና ታገኛላችሁ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድም ትድናላችሁ። የመከላከል እርምጃችንን አጠናክረን እንድንቀጥል በሂደትም አሸናፊ እንደምንሆን ጸሎቴ ነው።»

Wiedereröffnung einer Schule in Liberia
ምስል DW/Julius Kanubah
Ebola in Sierra Leone
ምስል Reuters/R. Ratner


«ማንኛውም ህመም የተሰማው ሰው ወደ ኢቦላ ህክምና ማዕከል በመሄድ ምርመራ እንዲያደርግ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ። የምርመራው ውጤት ነጻ ከሆነ በእርግጠኝነት ወደ ቤታችሁ ትሄዳላችሁ። ቤታችሁ ተቀምጣችሁ እስኪረፍድ አትጠብቁ።»
በላይቤሪያ ስጋት ከተጫናቸው አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው። ትምህርት ቤቶች እንደገና ተከፍተዋል። እጅ የመታጠብ እና በቋሚነት የሰውነት የሙቀት መጠንን የመለካት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጀምረዋል። ይሁንና እነዚህን የጥንቃቄ እርምጃዎች ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እያደረጉ አይደለም የሚል ፍርሃት አለ። ኢብራሂም ፎርቹን በሞኖሮቪያ ከተማ የሙስሊም ኮንግረስ ከፍተኛ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ናቸው።

«እንደ ተማሪ አማካሪ ከትምህርት ሚኒስቴር የታዘዙትን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተማሪዎች በማክበር መንግስት የኢቦላ ስርጭትን ለመከላከል ከሚሰራው ስራ ጋር እኩል ለመጓዝ የተቻለንን በሙሉ በማድረግ ላይ እንገኛለን። አስቸጋሪ ቢሆንም ተማሪዎቻችን ሁኔታውን በሚገባ የሚረዱ በመሆኑ ጥሩ እየሄድን ነው።
«በሚቀጥለው አንድ ወር ነገሮች ሁሉ እንደታሰበው መሄድ ከቻሉ ላይቤሪያ በስተመጨረሻ ከኢቦላ ነጻ መሆኗን ልታውጅ ትችላለች። ቢሆንም ተህዋሲው የላይቤሪያ ጎረቤት በሆኑት ጊኒ እና ሴራሊዮን የሚገኝ በመሆኑ አሁንም ጥንቃቄ ያሻል።


ጁሊየስ ካኑባህ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ