1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ልማት፤ የውሃ እጥረትና አሳሳቢ ውዝግብ

ሐሙስ፣ መጋቢት 7 1998
https://p.dw.com/p/E0dx

የውሃው ችግር በተለይ በውዝግብ ትርምስ ውስጥ የሚገኘውን የመካከለኛውን ምሥራቅ አካባቢ ያህል ጎልቶ የሚታይበት ሌላ ቦታ የለም። እርግጥ በአፍሪቃም የአባይ ተፋሰስ አገሮች የውሃን አጠቃቀም በተመለከተ ከአንድ ጭብጥ የጋራ ስምምነት አለመድረሳቸው እንዲሁ የተባባሰ የውዝግብ መንስዔ እንዳይሆን በጣሙን ነው የሚያሰጋው። አንዳንድ ለጉዳዩ ቀረብ ያሉ ታዛቢዎች እንዲያውም የውሃው ጦርነት ከፈነዳ ሰንበት ብሏል እስከማለት ደርሰዋል።

የውሃ እጥረት ዛሬ ከሕዝብ ቁጥር በተፋጠነ ሁኔታ መናር ጋር ተጣምሮ ለብዙዎች፤ በተለይም ታዳጊ አገሮች የሕልውና ፈተና፤ የልማት መሰናክልም እየሆነ ሲሄድ ነው የሚታየው። በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትና በዓለም የውሃ ጉዳይ ሸንጎ መረጃዎች መሠረት በአሁኑ ጊዜ 1.4 ሚሊያርድ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያገኝም። ከሁለት ሚሊያርድ ተኩል በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ደግሞ አግባብ-ያለው የመጸዳጃ ሁኔታ የተዘጋጀለት አይደለም።

ከዚህ የተነሣ በተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ልማት ዕቅድ መሠረት የተጠቀሰውን ችግር ተቋቁሞ ከተጣለው ግብ ለመድረስ አሁን ካለው እጥፍ ገንዘብ፤ ማለትም ሰላሣ ሚሊያርድ ዶላር በሥራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ነው የሚገመተው። የሚሌኒየሙ ግብ እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ንጹህ ውሃና መጸዳጃ የሌለውን ሕዝብ ቁጥር ከ 1990 መጠን አንጻር በግማሽ መቀነስ መሆኑ ይታወቃል። በነገራችን ላይ የውሃ ፍጆት ባለፈው ሃያኛ ምዕተ-ዓመት በስድሥት ዕጅ ነው የጨመረው። ከሃምሣ ዓመታት በፊት ፍጆቱ በነፍስ-ወከፍ 17 ሺህ ሜትር-ኩብ ገደማ ይጠጋ ነበር።
ከዚያን ወዲህ ግን በጣም እያቆለቆለ መጥቷል፤ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከሃያ ዓመታት በኋላ ሥምንት ሚሊያርድ ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን የነፍስ-ወከፉ ፍጆት ወደ አምሥት ሺህ ሜትር-ኩብ እንደሚያቆለቁል ነው የሚነገረው። ይሄው የውሃ አጠቃቀም ጉዳይና መብት አከራካሪ እየሆነ የቀጠለ ሲሆን ለጦርነት መንስዔ እንዳይሆን ስጋት መፈጠሩም አልቀረም። የውሃ እጥረት ያስከተለው ችግር ዛሬ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል፤ እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ደቡብ-ምሥራቅ እሢያ ጎልቶ የሚታይ ነው።

በፖለቲካ ይዞታው ከጥግ እስከ ጥግ በተመሰቃቀለው በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ፣ የጎሣና የሃይማኖት ልዩነት ብዙውን ነገር ወስኖ ነው የሚገኘው። ሆኖም ለዘመናት የአካባቢው የሕይወት እስትንፋስ የሆነው ዮርዳን ይህ ሁሉ ሳይገታው ከሄርሞን ተራሮች ተነስቶ በስተደቡብ አቅጣጫ በማምራት ወደ ዮርዳኖስና እሥራኤል ድንበር ይፈሣል። የዚሁኑ ወንዝ ያህል በብዙ ትውልድ በግጥም፣ በተረትና በዜማ ሲወደስ የኖረ ሌላ አይገኝም ነው የሚባለው።

ወንዙ በ ጌናዛሬት ባሕር ሸክሙን በማቃለል በዮርዳኖስ ምድር የመጨረሻ ጉዞውን ከቀጠለ በኋላ ወደ ሙት ባሕር ገብቶ መንገዱን ያበቃል። እርግጥ ከዚያ የሚደርሰው ሲበዛ ጥቂት ውሃ ብቻ ነው። ምክንያቱም ወንዙን የሚገለገለው የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝብ ለመጠጥም ሆነ ለመስኖ ውሃውን የሚጠቀምበት መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው። በአካባቢው ገና ከአሁኑ የሚታየው የውሃ እጥረት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የውሃው እጥረት በነዋሪው ብዛት በነፍስ-ወከፍ በዓመት ከ 250 ሜትር-ኩብ አይበልጥም። ይህም በዓለም ላይ ዝቅተኛው መሆኑ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም፤ Globaler wandel “ዓለምአቀፍ የለውጥ ሂደት” እየተባለ የሚጠራውን በዮርዳኖስ ወንዝ የሚካሄድ ፕሮዤ የሚመሩት ጀርመናዊት ፕሮፌሰር ካቲያ ቲልቡርገር እንደሚሉት ሁኔታው በቅርቡ ይበልጥ መባባሱ የማይቀር ጉዳይ ነው። “ምናልባት የዚህ የአካባቢ አየር ለውጥ የመጀመሪያ ክስተት የሚሆነው ለምሳሌ ያህል የድርቅ በአካባቢው መስፋፋት ነው። ይህም ማለት የዝናብ መጠን እየቀነሰ ይሄዳል፤ ከዚሁ ተያይዞ የጠንካራ ድርቅና የእርጥብ አመታት ውጣ-ውረድም መከተሉ አይቀርም። ይህ ደግሞ በውሃ ይዞታ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው።”

በፕሮፌሰር ቲልቡርገር የሚመራው የቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ ጠበብት ቡድን የዮርዳኖስን አካባቢ የውሃ ይዞታ ሲመረምር አምሥት ዓመታት ሆኖታል። ቡድኑ የአካባቢ አየርና የመሬት አጠቃቀም ሁኔታ የዛሬውን ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ትስስር Globalisation ተከትሎ ሲቀየር የሚያስልፈውን ለውጥ ለማመላከትም ይሞክራል። በአሕጽሮት Glowa እየተባለ የሚጠራው ፕሮዤ የሚራመደው ከጀርመን ፌደራላዊ የምርምር ሚኒስትር ተቋም በሚቀርብለት የገንዘብ ድጋፍ ነው።

ተመራማሪው ቡድን ያቀረበው የጥናት ውጤት በውሃ ጉዳይ የተፈጠረውን ብርቱ ስጋት በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣል። ሃቁ ይህን ነው የሚመስለው። የውሃ አቅርቦት እየመነመነ ሲሄድ በተመሳሳይ ጊዜ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየናረ ነው። ይህ በእሥራኤል፤ ከዚያም ጠንከር ባለ ሁኔታ በዮርዳኖስና በፍልሥጤም ራስ-ገዝ አካባቢዎች ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ሆኗል። ችግሩ በቀላሉ የሚለዝብም አይመስልም። የአካባቢው የውሃ ፍጆት እስከ 2040 ማለት በመጪዎቹ ሰላሣ ዓመታት በእጥፍ እንደሚጨምር ጠበብት ይገምታሉ።

አዝማሚያው በመካከለኛው ምሥራቅ ውሃ ዓበይት የውዝግብ መንስዔ የመሆኑ ሁኔታ እያደገ መሄድ ነው። በሰሜናዊቱ የጀርመን ከተማ የተፈጥሮ ጥበቃ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሩዲገር ፕራሰ የውሃው ጦርነት ከተነሣ ሰንበት ብሏል ባይ ናቸው። “ለውሃ የሚደረገው ጦርነት ገና የሚነሣ ነገር አይደለም፤ ፈንድቷል። ብዙው በአካባቢው የምንታዘበው ለውሃ የሚደረገው ትግል አንድ ክፍል እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። እና ይህን የውሃ ድህነት ለመቋቋም ዘዴ ማግኘት ይኖርብናል። አንዳንድ ወይም ጥቂት ማሕበረሰቦች በቂ ውሃ ማግኘት እየቻሉ ሌሎች በጥቂት እንዲወሰኑ መሆን የለበትም።”

ሁኔታው ይህን የመሰለ ሲሆን እስካሁን ዮርዳኖስና እሥራኤል ሲሦው የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ ወደ ግዛታቸው እንዲዘልቅ ሲያድጉ ቆይተዋል። ግን በሌላ በኩል የዕርሻ ልማት በነዚህ አገሮች ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር ግፋ ቢል አምሥት በመቶ ገደማ ቢጠጋ ነው። በመሆኑም ይህን መሰሉ የውሃ ይዞታ የፖለቲካ ዘይቤ ብርቱ ችግር ማስከተሉ አልቀረም። ከሆነ መፍትሄው ምንድነው፤ ምን መደረግ ይኖርበታል? የግሎቫ ፕሮዤ ተመራማሪዎች በወቅቱ ፖለቲከኞችና ሌሎች ባለሥልጣናት ውስብስብ ለሆነው የውሃ ችግር እንዲነቁና፤ እንዲያም ሲል አስፈላጊ ለሆነው ከብሄራዊ ወሰን የተሻገረ የአካባቢ ንግግር ዓይናቸውን የሚገልጹበትን ዘዴ ገሃድ ለማድረግ እየጣሩ ነው። የምርምሩ ውጤት አንድ ቀን ለሚመለከታቸው መንግሥታት ግልጋሎት እንዲውል የጥንቅር ዘዴ ለማዘጋጀትም ይታሰባል።

የተመራማሪዎቹ ዓላማ ይህ ወይም ያ ወገን አንድን ነገር እንዲቀይር ማስገደድ አይደለም። ይሁንና ሩዲገር ፕራሰ እንደሚሉት በመካከለኛው ምሥራቅ ተወዛጋቢ ወገኖች መካከል ንግግር ከሌለ ግሎቫ ጣልቃ መግባቱ ግድ ነው። “እኛ ጠበብት ፖለቲከኞች ከሚችሉት በላይ በገለልተኛ ቦታ መገናኘት እንችላለን። እርግጥ ፖለቲካ ከበስተጀርባ በመኖሩ ጠበብት ራሳቸው ሁልጊዜ በቀጥታ መገናኘት የማይችሉበት ሁኔታም አለ። ለአንድ የዮርዳኖስ ተመራማሪ ለምሳሌ ከአንድ የእሥራኤል መሰሉ ጋር መገናኘቱ ሁሌ ቀላል ነገር አይደለም። ግን የጀርመናውያኑን መሰል አንድ ገለልተኛ አካል በሚኖርበር ጊዜ ግንኙነቱ ይሣካል።” ሩዲገር ፕራሰ የጀርመን የፕሮዤው ተሳታፊዎች በወቅቱ ዕውቀትን በእሥራኤል፣ በፍልሥጤምና በዮርዳኖስ ጠበብት መካከል ወዲያ ወዲህ በማንሸራሸር የአማካይነት ሚና ይዘው እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ዛሬ ውሃ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በቀላሉ የማይገኝ ውድ የተፈጥሮ ጸጋ በሆነበት ወቅት የብዙዎች አገሮችን ወሰን የሚያቋርጡ ወንዞች የይገባኛል ጥያቄ እጅግ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ጉዳይ ነው። ይህ አሥር አገሮችን አቋርጦ ወደ ሜዴትራኒያን ባሕር የሚፈሰውን አባይን ጭምር ይጠቀልላል። ኢትዮጵያን የመሳሰሉት የወንዙ ተፋሰስ አገሮች ሁሉም ለዕድገታቸው በአጠቃቀሙ ላይ ጥገኛ ሲሆኑ ተገቢው ስምምነት እስካሁን አለመስፈኑ ውዝግቡን እንዳያባብስ ማስጋቱ አልቀረም።
ድርቅና የሕዝብ ቁጥር መናር የውሃ ክፍፍሉን ትግል ሊያካርረው ይችላል ብለው የሚሰጉት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። እርግጥ በዚህ በኩል የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ወገኖችም አልጠፉም። ከነዚሁ መካከል አንዱም በአሕጽሮት GTZ እየተባለ የሚጠራው የጀርመን ቴኪካዊ ተራድኦ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በአካባቢው ወሰን አቋራጭ ወንዞችን አብሮ መጠቀም የሚያስችል የጋራ መፍትሄ እንዲሰፍን ለማገዝ ይጥራል።

እርግጥ አፍሪቃ ውስጥ ዋነኛው ይሁን እንጂ ተፋሰስ አገሮችን አጠቃቀም ችግር ላይ ጥሎ የሚገኘው የአባይ ጥያቄ ብቻ አይደለም። የቻድ ባሕር፣ የኮንጎ ወንዝና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚገኙት የሊምፖፖና የኦራኒዬ ወንዞችም የተራድኦው ድርጅት ያተኮረባቸው ጉዳዮች ናቸው። GTZ ለአካባቢ ትብብር ግንባታ የሚረዱ የወንዝ አካባቢ ኮሚሢዮኖች ምሥረታዎችን ያራምዳል። የድርጅቱ ባልደረባ አክሰል ሺልድ ስለዚሁ ሲያስረዱ ”ዓላማው የአካባቢው አገሮች የተፈጥሮውን ጸጋ በጋራ እንዲጠቀሙና የውሃ አጠቃቀም ፖሊሲን ማስፈን እንዲችሉ አጠቃላይ ስምምነት ማስፈን፤ አሸናፊና ተሸናፊ እንዳይኖር ማድረግ ነው። በወንዙ መነሻ ላይ የሚገኘው አገር አቆልቁሎ በሚፈስበት ቦታ ላይ ላለው ምንጩን እንዲዘጋበት መሆን የለበትም። ውዝግብን የሚቀሰቅሰውም ይሄው ነው።”

ሜክሢኮ ውስጥ ከዛሬ ጀምሮ አንድ ሣምንት የሚፈጅ የዓለም የውሃ መድረክ ዓቢይ ጉባዔ ይካሄዳል። በዚሁ ጉባዔ በውሃ አስተዳደርና በክፍፍሉ በኩል ዓለምአቀፍ ሥልጣዊ ዘዴን ለማስፈን ነው ጥረት የሚደረገው። ከችግሩ አጣዳፊነት አንጻር አስቸኳይ መፍትሄ መገኘቱ ግድ ነው።