1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ልገሳ፤ ጉባኤ፤ ሰብአዊ ርዳታ

ሰኞ፣ ግንቦት 15 2008

ዓለም፤ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በማታዉቀዉ ስደተኛ፤ ተፈናቃይና ረሐብተኛ ተጨናንቃለች።ኢስታንቡል ቱርክ ላይ ዛሬ እና ነገ የሚመክረዉ ጉባኤም በዓለም ታሪክ የመጀመሪያዉ ነዉ።ገና ሳይጀመር ከወቀሳ-ትችት ያላመለጠዉ ጉባኤ በሰባ-አምስት ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቀዉን ችግር ለማቃለል የሚረዳ ሥልት መተለሙን በርግጥ ጊዜ ነዉ በያኙ።

https://p.dw.com/p/1ItDG
ምስል Reuters/M. Sezer

ልገሳ፤ ጉባኤ፤ ሰብአዊ ርዳታ

ኢትዮጵያ ዓለምን ባነቃነቀ ረሐብ በተመታችበት በ1976-77 ዓለም አቀፍ እዉቅና ያላቸዉ መንግሥታዊ ያልሆነ የርዳታ ድርጅቶች (መያድ)40 ነበሩ።ከአስር ዓመት በኋላ የቀድሞዋ ይጎዝላቪያ በጦርነት በተፈረካከሰችበት በ1990ዎቹ አጋማሽ (ከዚሕ በኋላ ያለዉ ዘመን በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) 250 ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ነበሩ።ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር አፍቃኒስታንን በወረረ ባመቱ አፍቃኒስታን ዉስጥ ብቻ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ መያዶች ቁጥር 2500 ደረሰ።ኔዘርላንዳዊቷ ጋዜጠኛና ደራሲ ሊንዳ ፖልማን እንደምትለዉ ከቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ ሠብአዊ ርዳታ ጥቂቶች የሚከብሩበት፤ ክፉዎች የሚጠቀሙበት፤ ተቋማት የሚወዳደሩበት ኢንዱስትሪ ሆኗል።ንግድ።ዛሬ ኢስታንቡል-ቱርክ የተሠየመዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ «አማላዩን» ንግድ ለመቀየር ይጠቅም ይሆን?

እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ኢራቅ የምትባል ሐገር ነበረች።በነዳጅ ዘይት ሐብት ከዓለም የሰወስተኝነቱን ደረጃ የያዘች።ከራስዋ አልፋ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የሌሎች ሐገራት ዜጎች ሥራ በመስጠት የታወቀች።ትምሕርት እና ጤና ለዜጎችዋ በማደረስ ከዓረብ ሐገራት ተወዳዳሪ ያልነበራት፤ ኩርዶችን ካረቦች፤ ሺኦዎችን ከሱኒዎች፤ዛይዲዎችን ከክርስቲያኖች አሰባጥራ የያዘች ታሪካዊት፤ ሐብታም፤ ጠንካራ ሐገር ነበረች።

በ1991 በተደረገዉ ጦርነት በከፊል ወደመች።በማዕቀብ ደቀቀች።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና የብሪታንያ ተባባሪያቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የዚያች ሐገር ከፊል ዉድመት፤ ድቀት አላረካቸዉም።ለኢራቅ ሕዝብ ሠላም-ብልፅግና፤ ፍትሕ-ዴሞክራሲ ለማስፈን ቃል ገብተዉ ባዘመቱት ጦር ጨርሶ አጠፏት።ሚሊዮች አለቁ።ዛሬም እያለቁ ነዉ።ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧ ተሰደደ።ተመፅዋች ሆነ።

ያልሞተ-ያልተሰደደዉ በጦርነት፤ በሽብር፤ በሐይማኖት ሐራጥቃ ግጭት እየተሸማቀቀ-የሚሞት የሚቆስል፤ የሚሰደድ-የሚፈናቀልበትን ጊዜ ያሰላል።በ1985- ኢትዮጵያን በመታዉ ድርቅ የተራበዉ ሕዝብ ከሁለት እስከ አራት ሚሊዮን የሚገመትነበር።ዛሬ በ31ኛ ዓመቱ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ ርዳታ ተመፅዋች ነዉ።ልዩነቱ ነዉ አነጋጋሪዉ።ሶማሊያ በርስ በርስ ጦርነት በምትወድምበት፤ሩዋንዳ በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በተመሰቃቀለችበት በ1990ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ከአፍሪቃ ቀንድ እስከ ምሥራቅ አፍሪቃ ባሉት ሐገራት የተሰደደና የተፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚገመት ነበር።

Türkei Humanitärer Weltgipfel
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ዘንድሮ ዘጠኝ ሚሊዮን ምሥራቅ አፍሪቃዊ ተሠድዷል።6,5 ሚሊዮን ተፈናቅሏል።ከኢራቅ እስከ ኢትዮጵያ፤ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ ጦርነት፤ ግጭት፤ ረሐብ እና ጭቆና ያሰደደ፤ ያፈናቀ፤ ለችግር ያጋለጠዉን ሕዝብ ለመርዳት፤ የርዳታ ድርጅቶች፣ እንደሚሉት በቂ ገንዘብ የለም።

የአፍሪቃ ስደተኞች አዉሮጳ እንዳይገቡ ለማገድ ግን የአዉሮጳ ሕብረት ብቻዉን 1,8 ቢሊዮን ዩሮ መድቧል።ገንዘቡ፤ በጀርመን ምክር ቤት የተቃዋሚዉ የግራዎቹ እንደራሴ ኒኤማ ሞቫሳት እንደሚሉት ለልማት ርዳታ ከተመደበዉ የሚቀነስ ነዉ።የጀርመን መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ)ን የመሳሰሉ ድርጅቶች ደግሞ ሞቫሳት እንደሚሉት አፍሪቃዉያን ችግረኞችን ከመርዳት ይልቅ የጨቋኝ መንግሥታትን የፀጥታ ሐይላት ማጣናከር ይዘዋል።

«GIZ ሠዎች የሚረዱበት ፕሮጄክቶችን (አፍሪቃ ዉስጥ) የሚያከናዉን ቢሆን፤ ለምሳሌ የስደተኞ እና የተፈናቃዮችን ሕይወት የሚለዉጥ ትምሕርት እና ሥልጠና ቢሰጥ ኖሮ መበረታታት የሚገባዉ ምግባር በሆነ ነበር።ግን GIZ ምንድነዉ የሚያደርገዉ? የተሻለ የስደተኞች አስተዳደር በሚል ሰበብ ከሚሠራቸዉ አንዱ ወደ ዉጪ ለመሰደድ የሚሞክሩ ስደተኞች የሚቆዩበትና የሚታሠሩበት ጣቢያ መገንባት ነዉ።የጀርመን መንግሥት የሚያስተዳድረዉ የርዳታ ድርጅት እስር ቤት ያለዉ፤ በታጠቁ ፀጥታ አስከባሪዎች የሚጠበቅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መገንባት በእዉነቱ ዓለማዉን የሚያረክስ ነዉ።»

Türkei Humanitärer Weltgipfel
ምስል Reuters/M. Sezer

ኔዘርላንዳዊቱ ጋዜጠኛ ሊንዳ ፖልማን እንደምትለዉ የርዳታ ድርጅቶች ተልዕኮ፤ ዓላማና ሥነ-ምግባር ከረከሠ ቆይቷል።በርዳታ አቅርቦት መርሕና አፈፃፀሙ ላይ ያተኮሩ ሰዎስት መፅሐፍት ያሳተመችዉ ጋዘጠኛ ከ1991 እስከ 2002 የዘለቀዉን የሴራሊዮን የርስ በርስ ጦርነት ታዝባ ነበር።«ሴራሊዮን ዉስጥ ተጠቃሚዎቹ ከዕርዳታ ድርጅቶቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸዉ ነጋዴ ልሒቃን ናቸዉ።በጦርነቱ ወቅት ጠመንጃ ይነግዱ ነበር።ጦርነቱ ሲቆም ቤቶቻቸዉን፤ መስሪያ ቤቶቻቸዉን፤ መኪኖቻቸዉን ለርዳታ ድርጅቶችና ለሠራተኞቹ እያከራዩ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኛሉ።የአማፂያንና የመንግሥት ታጣቂዎችም ለችግረኞች የተላከዉን የርዳታ ቁሳቁስና ገንዘብ ይቀራመቱታል። እርዳታዉ ይገባቸዋል ብዬ የማስባቸዉ ችግረኞች ምንም አያገኙም፤ ካገኙም ትንሽ ነዉ።እንያ መጥፎ ሰዎች እርዳታዉን ሲቀራመቱና ሲያተርፉበት ችግረኞቹ ቆመዉ ይመለከታሉ።»

ሠብአዊ ርዳታ ችግሩ ምድን ነዉ? ትጠይቃለች ጋዜጠኛዋ ባንዱ መፅሐፍዋ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየጊዜዉ እንደሚለዉ ችግሩ በቂ ገንዘብ አለመኖሩ ነዉ።ድርጅቱ እንደሚለዉ ሥልሳ ሚሊዮን ሕዝብ አንድም ስደተኛ አለያም ተፈናቃይ ነዉ።ስደተኛ፤ ተፈናቃይ ረሐብተኛዉ ሕዝብ 125 ሚሊዮን ነዉ።

ይሕን ሕዝብ ለመርዳት ዓለም አቀፉ ድርጅት 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ባይ ነዉ።እስካሁን የተገኘዉ ገንዘብ ግን ከሚያስፈልገዉ ግማሽ ያሕሉ ነዉ።አስር ቢሊዮን ገደማ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙንን ዛሬ የተሰየመዉ ጉባኤ ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ ያስገኛል የሚል ተስፋ አላቸዉ።«ርዕሳነ ብሔራትና መራሕያነ መንግሥታት፤የሰብአዊ ርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች፤የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ ተጠሪዎች፤ በቀዉስ የተመቱ ማሕበረሰብ ተወካዮች በጉባኤዉ ተሳታፊዎች ናቸዉ።ጉባኤዉ የ2030ዉን የዘላቂ ልማት ዕቅድን ያጠናክራል።ድሕነትን ለማስወገድ የተገባዉን ቃል ያድሳል።ሕይወትን ለማዳን የምናደርገዉን ጥረት አጠናክረን በተለያዩ ቀዉሶች ለተጎዱ ሰዎች ተስፋ እንሰጣለን»

በጉባኤዉ ላይ የስልሳ ሐገራት መሪዎች ተገኝተዋል።ከ6ሺሕ የሚበልጡ የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች፤የሐይማኖት ተጠሪዎች፤ የሠብአዊ ርዳታ ጉዳይ አጥኚዎችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።ይሁንና ብዙ የሠብሰዊ ርዳታ ጉዳይ አጥኚዎች ችግረኛዉን ለመርዳት ገንዘብ ማዋጣቱ፤ ገንዘብ እንዲዋጣ ጉባኤ መጥራቱም ሆነ የርዳታ ድርጅቶች ቁጥርን ማሳደጉ ችግሩን ከማባባስ በስተቀር የተከረዉ፤ የሚተክረዉም የለም ባይ ናቸዉ።ጋዜጠኛ ሊንዳ ፖልማን ከዚሕ ቀደም እንዳለችዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የርዳታ ድርጅቶችን ብዛት መቁጠር ጀምሮ ነበር።ሰላሳ-ሰባት ሺሕ ላይ ደረሰና መቁጠሩን አቆመ።ቁጥሩ ማብቂያም የለዉና።ገንዘቡስ?

Christina Bennett
ምስል ODI

«ከሰባ የሚበልጡ በግልፅ የሚታወቁ ርዳታ ሰጪዎች አሉ።የጀርመን መንግሥት፤ የኔዘርላንድስ መንግሥት፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እነዚሕ ሁሉ ርዳታ ይሰጣሉ።ሰባዎቹ ርዳታ ሰጪዎች ባጠቃላይ በየዓመቱ 130 ቢሊዮን ዶላር ለልማት እና ለሠብአዊ የዉጪ ርዳታ ይሰጣሉ።ይሕ ብዙ ገንዘብ ነዉ ብዬ አምናለሁ።»

ብዙ ነዉ። የተረጁዎችን ሕይወት ግን አልለወጠም።እንዲያዉም የተረጂዉ ቁጥር በየጊዜዉ እየጨመረ ነዉ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች (MSF በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) የተሰኘዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት በበኩሉ ሕዝብ የሚገድሉ፤የሚያሰቃዩ፤ የሚሰድዱ፤ የሚያፈናቅሉ መንግሥታት ወይም ቡድናት በሕግ ካልተጠየቁ በስተቀር ገንዘብ-ማዋጣት፤ ጉባኤ መጥራቱ ዋጋም የለዉ ባይ ነዉ።ድርጅቱ በተለያዩ ሐገራት ችግረኞችን የሚያክምበት 75 ሆስፒታሎች በቦምብ እና ሚሳዬል ተመትተዉበታል።አብዛኞቹን ሆስፒታሎች ያፈረሱት በከባድ የጦር መሳሪያ በተለይም በተዋጊ ጄቶች የሚዋጉ የመንግሥታት ሐይላት ናቸዉ።MSF እንደሚለዉ መንግሥታት ይሁኑ ታጣቂ ሐይላት ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ ሊገደዱ ይገባል።ድርጅቱ የኢስታንቡሉን ጉባኤ «ነዉርን መሸፈኛ» በማለት አጣጥሎ ነቅፎታል።እራሱንም ከጉባኤዉ አግልሏል።

የባሕር ማዶ ልማት ተቋም (ODI) የተሰኘዉ የብሪታንያ የርዳታ ጉዳይ አጥኚ ድርጅት ባልደረባ ክርስቲና ቤኔት እንደሚሉት የድንበር የለሽ ሐኪሞችና የብጤዎቹ ጥያቄ በኢስታንቡሉ ጉባኤ መልስ አለማግኘቱ በርግጥ አሳዛኝ ነዉ።«ድንበር የለሽ ሐኪሞችና ብጤዎቻቸዉ እንደጠቆሙት፤ ዛሬ ለምናየዉ የሠብአዊ ቀዉስ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸዉ መንግሥታት፤ ተጠያቂ የሚሆኑበትን መንገድ በጉባኤዉ ላይ ሊነሳ አለመታቀዱ አሳዛኝ ነዉ።የጦርነትን ዓለም አቀፍ ሕግ አለማክበራቸዉ ለብዙ ሰላማዊ ሰዎች መሰቃየት ምክንያት ነዉ።መንግሥታት ግጭትን ለማስወገድ አለመስማማታቸዉ አሳዛኝ ነዉ።»

Buchcover Die Mitleidsindustrie von Linda Polman
ምስል Campus Verlag

የሶሪያ መንግሥትን ማዉገዝ፤ ለወረራ-ማስፈራራት፤ በማዕቀብ መቅጣት ሐያሉን አለም በርግጥ አላቃተዉም።ሊቢያን ከሐብታም፤ ለጋሽ ሐገርነት ወደ ትቢያ፤ ተመፅዋችነት የለወጠዉ ማን ነዉ? ኢራቅንስ? የዓለም ሕግ አክባሪ-አስከባሪዉስ? አስፈሪ መልስ ቆስቋሽ ጥያቄ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአስፈሪዉ ጥያቄ-መልስ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ የMSF በጉባኤዉ ያለመሳተፍ «ዴሞክራሲያዊ መብት»ን ማክበሩን ነዉ የመረጠዉ።ለነገሩ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ከአባል መንግሥታት በተለይም የሐያላኑ መንግሥታትን ፍላጎት ከማስፈፀም ባለፍ ሕጋዊ ሥልጣን፤ አቅምም የለዉም።

ዛሬ እና ነገ የሚመክረዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መንግሥታትን ተጠያቂ ማድረጉ ቢያቅተዉ እስካሁን የሚሰራበትን የርዳታ መርሕ፤ ሥራና አሠራርን ዘመኑ በሚፈቅደዉ አኳኋን እንዲቀየር የሚረዱ ሐሳቦች ወይም የጥናት ዉጤቶች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል።ወይዘሮ ክርስቲና ቤኔት እንደሚሉት ከሰባ-አምስት ዓመት በፊት የተነደፈዉ የሰብአዊ ርዳታ ሥልትና አሠራር የዘመኑን ችግሮች ለማቃለል አይጠቅምም።

Linda Polman
ምስል Patricia Hofmeester

«የሠብአዊ ርዳታዉ ሥልት የተነደፈዉ ከሰባ-አምስት ዓመት በፊት ነዉ።ያኔ ዓለም ጭራሽ የተለየች ነበረች።ዛሬ ብዙ አደጋዎች አሉ። ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ አደጋዎች አሉ።ከአደጋዎቹ ለማገገም ብዙወጪ ይጠይቃል።ግጭቶቹ የተለዩ ናቸዉ።በአብዛኛዉ ዉስጣዊ፤ እና ከመንግሥት፤ለመንግሥት ጦርነቶች ይልቅ የታጣቂ ሐይላት ግጭቶች ናቸዉ።ዉጊያዎቹ የሚደረጉት ድሮን (ሰዉ አልባ አዉሮፕላንን) በመሳሰሉ ዘመናይ ጦር መሳሪያዎች ነዉ።በ1945 የነበረዉ ሥልት፤ ሥርዓት፤መዋቅር፤ ተቋምና ቅርፅ ዛሬ ለሚገጥሙን ሰብአዊ ቀዉሶች መልስ መስጠት አይችሉም።»

ዓለም፤ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በማታዉቀዉ ስደተኛ፤ ተፈናቃይና ረሐብተኛ ተጨናንቃለች።እንደ ስደተኛዉ መብዛት ሁሉ ኢስታንቡል ቱርክ ላይ ዛሬ እና ነገ የሚመክረዉ ጉባኤም በዓለም ታሪክ የመጀመሪያዉ ነዉ።ገና ሳይጀመር ከወቀሳ-ትችት ያላመለጠዉ ጉባኤ በሰባ-አምስት ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቀዉን ችግር ለማቃለል የሚረዳ ሥልት መተለሙን በርግጥ ጊዜ ነዉ በያኙ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ