1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐርላ፡ አዲስ የጥንት ስልጣኔ ግኝት በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2009

ጥንታዊ የሙስሊሞች ከተማ ነዉ የተገኘዉ። ግኝቱም እጅግ ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለዉ ነዉ። ቦታዉ ላይ ተገኝተን የምርምሩን ስራ የጀመርነዉ የመጀመርያዎቹ  ተመራማሪዎች እኛ ነን። እየሰራን ያለነዉ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ከመንግሥት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር  በጋራ ሆነን ነዉ። የዚህ ታሪክ ምርምር ዋና ጠቀሜታ በሁለት መንገድ ማየት እንችላለን።

https://p.dw.com/p/2fDCt
Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

ሐርላ፡ አዲስ የጥንት ስልጣኔ ግኝት በኢትዮጵያ

«በተለይ የታሪክ ዘመን አርኪዮሎጂ የሚባሉት፤ በታችኛዉ ሸለቆና በአፋር አካባቢ የሚካሄዱ ናቸዉ። ነገር ግን ከእስልምና ጋር የተያያዙ እስላሚክ አርኪዮሎጂ የምንለዉ ብዙም ያልተሰራበትና ብዙም ያልተሄደበት ስለሆነ ፤ ይህ የአሁኑ ግኝት ትልቅ ፍን ጭ ሰጥቶናል»

Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኝና ሐርላ በሚባል ቦታ ቅርሶችን በቁፋሮ በመፈለግ ጥንታዊ ታሪክ ጥናት የሚያካሂዱ ምሁራን ማለትም አርኪዮሎጂስቶች በ10ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበርን ከተማ ማግኘታቸዉን ይፋ ማድረጋቸዉን ተከትሎ አቶ ደሳለኝ አበባዉ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ማሰባሰብ ማደራጀትና ላብራቶሪ ጥናት ዳሪክቶሪት ዳሬክተር ከሰጡን አስተያየት ነዉ። በኢትዮጵያ የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ጥናትን በተመለከተ ሰሞኑን ይፋ የሆነዉ ዜና በምስራቅ ኢትዮጵያ የተገኘዉ ጥንታዊ ቅርሳቅርስ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ብርሃን ፈንጣቂ ነዉ ይላል። የጥንታዊ ታሪክ ቁሳቁስ ጥናት ባለሞያዎች ማለት አርኪዮሎጂስቶች በምስራቅ ኢትዮጵያ በ10ኛ ክፍለ ዘመን የነበረ ከተማን በቁፋሮ ስለማግኘታቸዉ አጫዉተዉናል።   

ሰሞኑን የጥንታዊ ቅርስ ጥናት ተመራማሪዎች በምስራቅ ኢትዮጵያ ሐርላ በሚባል አካባቢ ጥንታዊ የእስላም ስልጣኔ መኖሩን በምርምር ማግኘታቸዉን ይፋ አድርገዋል። ይህ ሐርላ ተብሎ የሚጠራዉ ስፍራ በምስራቅ ኢትዮጵያ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኝ ነዉ። በአካባቢዉ በሚነገር አፈታሪክ በስፍራዉ በጣም ግዚፍና ረዣዥም ሰዎች ይኖሩ እንደነበረና ከፍተኛ ስልጣኔ እንደነበራቸዉም ያሳያል፡፡ ይሁን አንጂ አካባቢዉና ስልጣኔዉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምንም አይነት በቂና ትክክለኛ ጥናትና ምርምር ሳይደረግበት የቆየ ስፍራ መሆኑን ተመራማሪዎች ያወጡት የጥናት መረጃ ያመለክታል።፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ማሰባሰብ ማደራጀትና ላብራቶሪ ጥናት ዳሪክቶሪት ዳሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባዉ ሐርላ ከተማ ይላሉ፤ ከድሬደዋ ወደ 35 ኪሎሜትር የሚርቅ አካባቢ ነዉ። የአርኪዮሎጂ መስክ ነዉ። ከ 10ኛዉ እስከ 12ኛዉ ክፍለዘመን የእስልምና ስልጣኔ፤ ይህም ስልጣኔ ከተለያዩ ሃገሮች ጋር ግንኙነት እንደነበረዉ፤ ተመልክቶአል። ያ ብቻ አይደለም የተለያዩ ጌጣጌጦች ቦታዉ ላይ ተገኝ,ዋል። ጌጣጌጦቹ እዝያ ቦታ ላይ ይሰሩ እንደነበረ እስከ መካከለኛዉ ምስራቅ የንግድ ግንኙነት እንደነበረበት ተመራማሪዎች የጥናታቸዉን ዉጤት አስቀምጠዋል።»  

ፕሮፌሰር ቲሞቲ እንሶል
ፕሮፌሰር ቲሞቲ እንሶልምስል Timothy Insoll

ባለፉት ሁለት ዓመታት  ብሪታንያ  ከሚገኘዉ ኤክስተር፤ ቤሊጂየም ሀገር ከሚገኘዉ ሊዩቨን እና ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እንዲሁም  ከቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን የተወጣጡ የጥንታዊ ታሪክ በቁፋሮ ፍለጋ ተመራማሪዎች ማለት አርኪዮሎጂስቶች  በብሪታንያ ኤክስተር ዩኒቨርሲቲ የእስልምናና አራቢክ አርኪሎጂ ፕሮፌሰር በሆኑት ቲሞቲ እንሶል መሪነት ጥናታቸዉን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ ፕሮፊስር ተሞቲ እንደሚሉት በሐርላ ያገኘነዉ ጥንታዊ የሙስሊም ከተማን ነዉ። 

«ልክ ነዉ። ጥንታዊ የሙስሊሞች ከተማ ነዉ የተገኘዉ። ግኝቱም እጅግ ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለዉ ነዉ። ቦታዉ ላይ ተገኝተን የምርምሩን ስራ የጀመርነዉ የመጀመርያዎቹ  ተመራማሪዎች እኛ ነን ።  እየሰራን ያለነዉ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ከመንግሥት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር  በጋራ ሆነን ነዉ። የዚህ ታሪክ ምርምር ዋና ጠቀሜታ በሁለት መንገድ ማየት እንችላለን። በመጀመርያ በኢትዮጵያ የእስላም የቅርስ ጥናት ቁፋሮ ታሪካዊ ምርምር እስከዛሬ እምብዛም አልተካሄደም። ምክንያቱም የታሪክ ጥናት ተመራማሪዎች በተለይም ቁሳቁሶችና ቅርሳቅርሶችን በመፈለጉ ረገድ እስከዛሬ ትኩረታቸዉ በሌላ አቅጣጫ በመሆኑ ነበር። ለምሳሌ የቅድመ ሰዉ አካል ቅሪትን፤ አልያም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ክርስትና ሃይማኖት ታሪክ ላይ ብቻ ነበር ሰፊ ምርምርና ትኩረታቸዉን ያደረጉት። በሁለተኛ ይህ ምርምር ጠቃሚ ያለዉ በቁፈራ ባገኘናቸዉ የቁሳቁስ አይነቶች ላይ ነዉ። ቁሳቁሶቹ በተለይ በጥንት ዘመን ከባሕር ማዶ የነበረዉን የንግድ ግንኙነት የሚያመላክቱ  ናቸዉ። በተለይ ደግሞ በ 10ኛዉ እና 14ኛዉ ክፍለ ዘመን መካከል ላይ ያለዉን የንግድ እንቅስቃሴ የሚጠቁሙ ቁሳቁሶች ናቸዉ።»

Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

እንጊሊዛዊዉ ተመራማሪ ቲሞቲ እንሶል የዛሬ ሦስት ዓመት ፈቃድ አግኝተዉ ድሬደዋ አካባቢ ምርምር መጀመራቸዉን የሚናገሩት አቶ ደሳለን አበባዉ ተናግረዋል።

Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በእስምና አርኪዮሎጂ ጥናት ዘርፍ ብዙ አጥጋቢ ጥናቶች ያልተካሄዱና የነበሩ ስልጣኔዎችም ሳይታወቁ የቀሩበት ሁኔታ ቢኖርም ይህ ጥናት በተለያዩ ዘርፎች ለነበሩን የጥናት ክፍተቶች መልስ የሠጠ ነዉ ማለት ይቻላል ያሉት እንጊሊዛዊዉ ተመራማሪ በመቀጠል፤

« በቁፋሮዉ በ 13ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበረ የመስጊድ ቅሪቶችን አግኝተናል። በሃራላ አካባቢ ትንሽ የሙስሊም ማኅበረሰብ ይኖር እንደነበር አመላካች ነዉ። በበአክሱም ዘመነ መንግሥት ኢስላም ሃገራትና በኢትዮጵያዉያን ነጋዴዎች መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንደነበር ቀደም ሲል በታሪክ የታየ ነዉ።  አሁን ባገኘነዉ ምርምር ደግሞ በኢትዮጵያ ድሪዳዋ አካባቢ ቢያንስ ከ 12ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስልምና እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ ነዉ።»   

ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት አርኪዮሎጂ ጥናት በሐርላ አካባቢ ያልተካሔደ ሲሆን በስፍራዉ የሚገኙ አርሶ አደሮች በእርሻ ወቅት የተለያዩ ከሸክላ የተሰሩ ቁሳቁሶች   የጥንት ሳንቲሞችን በስፋት ያገኙ እንደነበረ  ይሔም በስፍራዉ ከመሬት በታች በጥንት ለነበረዉ ስልጣኔ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ የአርኪዮሎጂ ቅሪቶች መኖር ሰፊ መረጃ መስጠቱ ተመልክቶአል።  እንጊዛዊዉ የጥንታዊ እስልምና ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፊስር ተሞቲ  በሐርላ ወደ 300 ጥንታዊ መካነ መቃብሮች መገኘታቸዉን ገልፀዉልናል።

«አካባቢዉ ላይ ያገኘነዉ 300 ቅሬተ አፅሞችን ሳይሆን 300 የመቃብር ቦታዎችን ነዉ። እነዚህን መቃብሮች ልንነካቸዉ ማለት ልንከፍታቸዉ አልፈለግንም።  ከነዚህ መካከል ሦስት መቃብሮችን ብቻ ከፍተን ለምርምር የሚሆነን ናሙና ወስደናል።  ይህ ቅሪተ አጽም የሚሰጠን መረጃ ሰዎች በዝያ ዘመን ምን አይነት ምግብን ይመገቡ እንደነበር ነዉ።  ይህን ምርምር ተከትሎ አካባቢዉ ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ብቻ ናቸዉ አልያስ ከከሩቅ ሃገራት የመጡ ነጋዴዎች ናቸዉ የሚለዉንም እንመለከታለን። »

Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

የመካነ ቅርሱ የሚገኝበት ቦታ ሰፉ ቦታን የሚሸፍን ሲሆን በአካባቢዉ ላይ የሚገኝ የመኖሪያ ስፍራ ከትላልቅ ድንዮች የተሰራ በመሆኑ በአካባቢዉ ማኅበረሰብ የሐርላ ሰዎች በጣም ረዣዥምና ትላልቆች ናቸዉ ለሚለዉ አፈ-ታሪክ እንደማጠናከሪያ ይጠቀሙበት እንደነበር ተነግሮአል፡፡ ይሁንና እስካሁን በተደረገዉ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮና ጥናት ይህ አፈ-ታሪክ ልክ አለመሆኑ የተረጋገጠ  መሆኑና በአካባቢዉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ይኖሩ እንደነበረ ማሳያ የሚሆኑ መረጃዎች መገኘታቸዉን አቶ ደሳለኝ አበባዉ ተናግረዋል።

ይህ ግኝት በኢትዮጵያ የሙስሊምን ወይም ደግሞ የእስልምናን ጥንታዊነት ያመለክታል? 

በምርምር ስራዉ ላይ ተካፋይ የነበሩት የጥንታዊ ታሪክና ቅርስ ተመራማሪ አቶ ብላዴ እንግዳ እንደሚሉት፤ ሐርላ ላይ የተደረገዉ ምርምር ገና የሚቀጥል ቢሆንም እስካሁን የተደረገዉ ምርምር አስር ኪሎሜትር የሚሸፍን ነዉ።

ይህ አዲስ ግኝትና ጥናት ከ10ኛዉ እስከ 15 ክፍለ ዘመን በሀገሪቱ ለነበረዉ የዓለም አቀፍ ንግድና በአካባቢው የእስልምና መጀመር አዲስ መረጃ መሆኑን የወጣዉ ጥናት መረጃ አመልክቶአል። ይህም ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ምስራቅ ኢትዮጵያ ከባህረ ሰላጤ ሀገራት፣ ግብፅና ህንድ ጋር የጠነከረ ግንኙነት እንደነበረዉ የሚያሳይ የመጀመሪያ መረጃ መሆኑም ነዉ የተጠቀሰዉ። ከዚህ በተጨማሪ 12ኛዉ ክፍለ ዘመን በሐርላ የነበረን መስጊድ፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ የእስልምና መቃብር መረጃ፤ የጌጣ ጌጥ ስራ መረጃ፤   የተለያዩ ቁሳቁሶች ማለትም የብርጭቆ ስባሪዉች፣ የድንጋይ ክርስታሎች፣ ጨሌዎች፣ የማዳጋስካር፣ የቻይና እና የየመን ሸክላ ቁሳቁሶችና ሌሎችም የመገልገያ መሳሪያዎች መገኘታቸዉን እንጊሊዛዊዉ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፊሰር ቲሞቴ ገልፀዉልናል።  በ13ኛዉ ክፍለ ዘመን በግብፅ ይሰሩ የነበሩ ከነሐስና ከብር የተቀረፁ የመገበያያ ሳንቲሞች በጥናት ቡድኑ  ተግኝቷል፡፡

«ግኝቶቹ በተካሄዱባቸዉ ቦታዎች በርካታ ከንኬል ከብር የተሰሩ ጌጣጌጦች የክብር ድንጋዮች እንዲሁም  ከጠርሙስ አይነት ነገሮች የተሰሩ የተለያዩ ጌጣጌጦችን አግኝተናል።  ለንግድ ልዉዉጥ የሚዉሉ ሳንቲሞች እና ከሸክላ የተሰሩ ማሰሮዎችና ሳህኖችንም አግኝተናል።  የመካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት ባህል የሚታይባቸዉ ማሰሮዎች ፤ የቻይና ማሰሮዎችንም ጭምር ሁሉ አግኝተናል።  ስለዚህ ቦታዉ ላይ ትልቅ የጌጣጌጥ ስራ ምርት እንደነበር የሚያመላክትም ጭምር ነዉ።»

Äthiopien Ausgrabung einer alten Stadt
ምስል Timothy Insoll

የተገኙት መረጃዎች ሐርላ የጥንት ንግድና የጌጣጌጥ ማምረቻ ማዕከል መሆኑን ይጠቁማል ያሉት ቲሞቴ የተገኙት ጌጣጌጦችም ከፍተኛ ጥራት ያላቸዉና የሚመረቱትም ከብር፣ ነሃስና ጨሌ ሆኖ በኣባቢዉና ከአካባቢዉ ዉጭ ይሸጡ እንደነበር በጥናታቸዉ ጠቁመዋል።  ለዚህ ስራ ጥቅም ላይ ይዉል የነበረዉ ህንድ ሀገር ከነበረዉ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ መሆኑን ይህም የንግድ ወይንም የሰዉ ፍልሰትን የሚያሳይ እና የዉጭ ሀገር ዜጎች ከአካባቢዉ ማኅበረሰብ ጋር ተደባልቀዉ የሚኖሩ እንደነበር  የንግድ መስመሩም እስከ ቀይ ባህር፣ የህንድ ዉቅኖስና ምናልባትም እስከ አረብ ባህረ ሰላጤ የቀጠለ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቶአል።  በአካባቢዉ የተገኘዉ መስጊድ ህንፃ አሰራር በደቡብ ታንዛኒያና በሶማሊላንድ ካሉ የጥንት መስጊዶች ጋር የሚመሳሰል መሆኑንና ይህም በአፍሪቃ ባሉ የተለያዩ የሙሲሊም ማህበረሰቦች መካከል ግንኙነት መኖሩን አመላካች እንደሆን ፕሮፊሰር ቲሞቲ  እንሶል ተናግረዋል ።

የአርኪዮሎጂ ጥናት በአብዛኛዉ በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ይዘወተር እንደነበረ የጠቆሙት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ማሰባሰብ ማደራጀትና ላብራቶሪ ጥናት ዳሪክቶሪት ዳሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባዉ የሐርላዉ ጥናት ትልቅ ፍንጭን የፈነጠቀ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።  

በጎርጎረሳዊዉ 2015 ዓ,ም ምስራቅ ኢትዮጵያ ድሪደዋ ሐርላ ላይ የጀመረዉ ይህ የአርኪዮሎጂ ጥናት በአዉሮጳ የምርምር ምክር ቤት የሚደገፍ እንደሆን የተናገሩት በብሪታንያ ኤክስተር ዩኒቨርሲቲ የእስልምናና አራቢክ የጥንታዊ ታሪክና ቅርሳቅርስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር  ቲሞቲ እንሶል በሐርላ አካባቢ ቤተ-መዘክር ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸዉን ተናግረዋል።  

ፕሮፌሰር ቲሞቲ እንሶል
ፕሮፌሰር ቲሞቲ እንሶልምስል Timothy Insoll

«ይህ ታሪካዊ ግኝት ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ማመስገን እወዳለሁ። በሌላ በኩል ገንዘብ በማሰባሰብ ለአካባቢዉ ማኅበረሰብ ቤተ- መዘክር በመገንባት ሃርላን እና አካባቢዋን በመጠበቅ ከጎብኝዎች የሚገኘዉን መጠነኛ ገቢ የአካባቢዊዉ ማኅበረሰ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራን ነዉ። ስለዚህም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ዉስጥ አካባቢዉ ላይ ቤተ- መዘክርን መገንባት በመረሃ ግብራችን ያካተትነዉ  እቅዳች ነዉ።»  በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኘዉ ሐርላ በሚባል ቦታ አርኪዮሎጂስቶች ያገኙት በ10ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበርን ከተማ ምርምር ጥናት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደሚቀጥል ተመልክቶአል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ