1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕንድ፤ የ 60 ዓመት ነጻነትና የተፋጠነ ዕድገቷ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 9 1999

እንደ ቻይና ሁሉ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኘው ሕንድ በዛሬው ዕለት ከብሪታኒያ ቅኝ-አገዛዝ የተላቀቀችበትን 60ኛ ዓመት አክብራለች።

https://p.dw.com/p/E0cl

ሕንድ ከ 1947 ዓ.ም. ነጻነት ወዲህ ያመራችበት ጎዳና ብዙ ውጣ-ውረድ ባያጣውም ዴሞክራሲ እንዲቆናጠጥና የኤኮኖሚ ዕድገት እንዲሰፍን በማድረጓ በዓለም ሕብረተሰብ ውስጥ ክብደቷ እየጨመረ መሄዱ አልቀረም።

“ዛሬ ዓለም በሙሉ ተኝቶ ሳለ እኩለ-ሌሊት ላይ ሰዓቱ ሲደውል ሕንድ በሕይወትና በነጻነት ትነቃለች። የሰውልጅ ይህን ዓይነቱን ዕድል የሚያገኘው ደግሞ በታሪክ ውስጥ ከስንት አንዴ ብቻ ነው። ከአሮጌው ተሰናብተን አዲሱን እንጀምራለን። አንድ ዘመን በዚሁ ያከትማል፤ ለረጅም ጊዜ በጭቆና ሥር የቆየው የሕዝብ መንፈስ ከመሸማቀቅ በመላቀቅ ነጻ ሆኖ ይከሰታል”

ይህን የዛሬ 60 ዓመት የተናገሩት የሕንድ የነጻነት አባት የማሃትማ ጋንዲ የትግል አጋርና የመጀመሪያው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋሃርላር ኔህሩ ነበሩ። ሕንድ በዴሞክራሲና በብልጽግና አቅጣጫ እንድታመራ ከጅምሩ ጥሩ መሠረት የጣሉት የኔህሩ ራዕይ ይሄው ነበር፤ አገሪቱን በገለልተኛ ፖሊሲ በመምራትም ለዛሬው ዕድገት ወሣኝ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ሕንድ ዛሬ በፖለቲካም ሆነ በኤኮኖሚ ዓለምአቀፍ ክብደት የሚሰጣት አገር ናት። በተለይ የታፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃዋ ቻይናንና ብራዚልን ከመሳሰሉት ሃገራት ዕድገት ጋር ተጣምሮ በዓለም ንግድ ግንኙነት ላይ የሚዛን ለውጥ እንዲከሰት ማድረጉ በግልጽ የሚታይ ሆኗል።

ከብሪታኒያ ቅኝ-አገዛዝ የተላቀቀችበትን 60ኛ ዓመት ያከበረችው ሕንድ በወቅቱ በአማካይ 8 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ከቻይና ጎን ለጎን የእሢያ የኤኮኖሚ ዕርምጃ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር ናት። እርግጥ ያለፉት ስድሥት አሠርተ-ዓመታት ጉዞ ለሕንድ ቀላል አልነበረም። ከጅምሩ ፓኪስታን ተገንጥላ በሥላማዊ ሬፑብሊክነት መቋቋሟ ብዙ ጥፋትን ሲያደርስ የኋላ ኋላ የኑክሌያር ጦር መሣሪያ ባሌቤት ሊሆኑ የበቁት የሁለቱ መንግሥታት የግዛት ሽኩቻና ጥላቻ ዛሬም አላበቃም። በክፍፍሉ ሳቢያ በተፈጠረው ግጭት ቢያንስ 750 ሺህ ሰዎች ሲሞቱ የተፈናቀሉት ከ 17 ሚሊዮን ይበልጣሉ። ሕንድና ፓኪስታን በካሽሚር ግዛት ሳቢያም እስካሁን ሶሥት ጦርነቶች አካሂደዋል።
ምናልባት ውሎ-አድሮ ጦርነቱ ይደገም ይሆን? ከወቅቱ ለዘብ ያለ ግንኙነት አንጻር እንዲህ ብሎ መናገሩ ጥቂትም ቢሆን የሚያዳግት ነው። በሌላ በኩል ግን ችግሩ አሁንም ሁለቱ መንግሥታት ነጻነታቸውን ካገኙ ከ 60 ዓመታት በኋላም የአካባቢው ውጥረት መንስዔ ሆኖ መቀጠሉ ሃቅ ነው። ሆኖም ፓኪስታን በአምባገነን አገዛዝና በአክራሪ ሁኔታ ተወጥራ በምትገኝበት ወቅት በዓለም ላይ ታላቋ ዴሞክራሲ የምትባለው ሕንድ መጪውን አዲስ ዘመን የምትመለከተው በኩራትና ድህነትን ጨርሶ በማሸነፍ ታላቅ ተሥፋ ነው። ፕሬዚደንት ፕራቲባ ፓቲል የነጻነቱን ክብረ-በዓል ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት ቁልፍ መልዕክትም “የኤኮኖሚው ዕድገት ፍሬ በተለይ በድሀነት ዝቅተኛ መስፈርት ውስጥ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል የሥራና የኑሮ ሁኔታ በማሻሻሉ ጥረት ላይ የግድ ሊያልም ይገባዋል”የሚል ነው።

በእርግጥም በወቅቱ ትልቁ የሕንድ ችግር ከኤኮኖሚው የወደፊት ግስጋሤ አንጻር በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነት ሲበዛ እየሰፋ መምጣቱ ላይ ነው። ጥቂቶች ይበልጥ ይካብታሉ፤ ብዙሃኑ የባሰ ይደኸያሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከድህነት ዝቅተኛ መስፈርት በታች በከፋ ሁኔታ የሚኖረው የሕንድ ሕዝብ 250 ሚሊዮን ይጠጋል። ሊያስገርም ይችላል ዛሬ በዓለም ላይ ከሶሥት አንዱ የኮምፑተር ኤክስፐርም ሕንዳዊ ነው። በአገሪቱ ውስጥ ደግሞ ከሶሥት አንዱ ሕንድ ማንበብና መጻፍ አይችልም። በአጭሩ መሃይም ነው። የሕንድ ሕብረተሰብ ቅራኔ!

አጠቃላዩ ሃቅ ይህ ሲሆን በተለይም ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ የኤኮኖሚ ለውጥ ወዲህ የተፈጠረው ጥቂት ሃብታም ክፍል ቦምቤይ ወይም ዴልሂን በመሳሰሉት ታላላቅ ከተሞች የሚኖርበት የምቾት ሁኔታ ሊታሰብ የማይችል ነው። የኑሮው ልዩነት በዚህ መጠን እየሰፋ መሄድ የሕብረተሰቡን ሰላም ሊያውክና ለዕድገትም እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ይሁንና የመንግሥቱ ኮንግሬስ ፓርቲ ፖለቲከኛ ራሺድ አልቪ የእስካሁኑ የሕንድ ዕርምጃ የሚያኮራ እንደሆነ ይናገራሉ። በርሳቸው አባባል ላለፉት 60 ዓመታት ታላቅ ስኬት ዓለም ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል፤ ዴሞክራሲያዊው ሥርዓት በነዚህ ዓመታት በዓለም ላይ ከማንኛውም ዴሞክራሲ ሊፎካከር በሚችልበት ሁኔታ ጠንክሯል ባይም ናችው።

ሕንድ ዴሞክራሲን በማስፈን ያደረገችው ዕርምጃ የሰመረ መሆኑ ጨርሶ አያጠያይቅም። የነገው ዓቢይ ጥያቄ ግን የኤኮኖሚው ዕድገት ቀጣይነትና የብዙሃኑ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ አገሪቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዋን በማጠናከር እንደምትቀጥል፤ በተለይ ደግሞ አዳዲስ የሥራ መስኮችን ለመክፈትና ድህነትን ለማስወገድ በእርሻ ልማት ዘርፍ ሰፊ ገንዘብ እንደምታፈስ ቃል ገብተዋል። እንደርሳቸው አባባል የኢንዱስትሪው ዕድገት መቀጠሉ ግድ ነው። እርግጥ በኢንዱስትሪው መስፋፋት አርሶ አደሩ መሬቱን ወይም ሕልውናውን እንዳያጣ መንግሥት የሰፈራና የእንክንካቤ ፖሊሲ እየቀረጸና ታላላቅ ፕሮዤዎችን ለማራመድ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ሕንድ በተፋጠነ ዕድገት አቅጣጫ የምታደርገው ዕርምጃ በስኬት ለመቀጠሉ በመሠረቱ ተሥፋ የሚሰጡ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከነዚሁም አንዱና ዋነኛው አገሪቱ ያላት ወጣት የሥራ ሃይል ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ነው። ከአገሪቱ 1,1 ሚሊያርድ ሕዝብ 51 በመቶው በዕድሜ ከ 25 ዓመት በታች፤ ወይም በጠቃላይ ሁለት-ሶሥተኛው ከ 35 በታች ነው። ይህ የወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ድርሻ ደግሞ እስከ 2050 ዓ.ም. ገደማ ጎልቶ የሚቀጥል መሆኑ ሲታመን የአገሪቱ የወደፊት ዕድገት ዋስትና፤ ታላቅ ሃብቷ ሊሆን እንደሚችል ጨርሶ አያጠራጥርም። የሕንድ ለሥራ ዕድሜ የበቃ ዜጋ ቁጥር በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ውስጥ 761 ሚሊዮን እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው።
አዲሱ የሥራ ሃይል ተገቢው የትምሕርት ዕድል ከተሰጠውና የሚገባውን ያህል አዳዲስ የሙያ መስኮች ከተከፈቱ ውጤቱ ሃያል ነው። መንግሥት ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን የወጣቱ ብዛት ቀውስ እንጂ ተሥፋ ሊሆን አይችልም። ብቃት የጎደለው የትምሕርት ሥርዓት፣ ሙስናና ተሥፋ የቆረጠ ወጣት ትውልድ የኤኮኖሚ ዕድገትን የሚቀጭ፣ ሕብረተሰባዊ ዕርጋታን የሚያደፈርስና ዓመጽ እንዲፈለፈል የሚያደርግ ነው የሚሆነው። በሕንድ ዛሬ በትምሕርቱ መስክ የሚቀርበው ዘገባ ለተሥፋ ምንጭ የሚሆን አይደለም። የትምሕርቱ ሥርዓት ሙስና የተጠናወተው፣ የፈተና ወረቀቶች የሚሸጡበትና አስተማሪዎችም እስከ 25 በመቶ ገደማ ሥራቸውን የሚያስተጓጉሉ መሆኑ ነው የሚነገረው። ዩኔስኮ እንደዘገበው በዓለም ላይ ከሕንድ የባሰ አገር ካለ ኡጋንዳ ብቻ ናት።

ወደ ሥራው ሃይል እንመለስና ለማነጻጸር ያህል በ 2020 ዓ.ም. ገደማ በሕንድ አማካዩ ዕድሜ 29 እንደሚደርስ ይገመታል። በአንጻሩ በቻይና 37፤ በጃፓን ደግሞ 48 ይሆናል ነው የሚባለው። ሕንድ ብዙው ወጣት ወደ ሥራው ዓለም በሚገባበት አሁን በምትገኝበት ወቅት አስፈላጊው ሁኔታው ከተሟላ በቁጠባ መዳበርና በመዋዕለ-ነዋይ መስፋፋት ብዙ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች። ቻይና በ 80ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ገደማ ታላቁን የኤኮኖሚ እመርታ ያደረገችው በዚህ የዕድሜ ሁኔታ በምትገኝበት ሰዓት ላይ ነበር። አሁን በቤይጂንግ አንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ በሚል ፖሊሲ ሳቢያ መገርጀፍ በጀማመረው ሕብረተሰብ ሂደት ውስጥ ዕድገቱ በ 2030 ገደማ እንደሚያቆለቁል የኤኮኖሚ ጠበብት ዕምነት ነው።
ሕንድ እንግዲህ ወጣት ሃይሏን የወደፊት ዕድገቷ መንኮራኩር አድርጋ በሚገባ ለመጠቀም አስፈላጊውን ለውጥ ሁሉ ሳይመሽ ከዛሬው ዕውን ማድረጉ ግድ ነው የሚሆንባት። እርግጥ የወቅቱን ሁኔታ ከተመለከትን አገሪቱ የወጣት ሃይል ጸጋዋን በአግባብ ለመጠቀም ገና ብዙ ይቀራታል። ከድሃው ገጠር አካባቢ ሥራ ፍለጋ ወደ ታላላቅ ከተሞች የሚጎርፉት ወጣቶች ብዙዎች ናቸው። ሆኖም በርካቶቹ በቤተሰብ ችግርም ሆነ ሌላ ምክንያት ከአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ስለማያልፉ ከአሽከርነት የተሻለ ዕድል አይጠብቃችውም። ታዲያ የትምሕርት ተሃንጾው፣ የሥራና የጤና ጥበቃ አገልግሎት በገጠሩ መጓደል ተሥፋውን እንዳያጨልመው የሚያሰጋ ነው።

ሕንድ በአንድ በኩል ባለፉት ዓመታት የተፋጠነ ዕድገቷ ድህነትን ለመቀነስ ብትችልም በሌላ በኩል ግን በተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ መሠረት በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ድህነትን በግማሽ ከመቀነሱ ግብ መድረሷ የሚያጠያይቅ ነው። ቢሆንም ዕድገቱ ከቀጠለና ሰፊውን ሕብረተሰብ ማቅረብ ከቻለ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕርምጃ መታየቱ የሚቀር አይመስልም።

ለማጠቃለል ሕንድ ባለፉት ስድሥት-አሠርተ-ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈንና በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ ለማምራትም በቅታለች። ከዛሬው የነጻነት ክብረ-በዓል በኋላ የወደፊቱን በተሥፋ ነው የምትጀምረው። የጥረቱ መሣካት-አለመሣካት በተቀረው ታዳጊ ዓለም፤ በተለይም በአፍሪቃ በየትኛውም አቅጣጫ ትምሕርታዊነት ይኖረዋል። ሕንድና ቻይና በፖለቲካ ሥርዓታቸው የሚጻረሩ ቢሆኑም ሁለቱም በታዳጊው ዓለም ዕድገት በውጭ መርህ ሣይሆን በራስ እንደሚቻል የየበኩላቸውን ማስረጃ አቅርበዋል። ጥያቄው ትምሕርቱ ግንዛቤ ማግኘቱ ላይ ነው።