1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕዝባዊ አመፅና የመገናኛ ዘዴዎች ሚና

ሰኞ፣ የካቲት 28 2003

መገናኛ ዘዴዉ ለሕዝባዊዉ አመፅ መሠረት አይሁን እንጂ የኑሮ ዉድነት፥ ሥራ አጥነት፥ የዲሞክራሲ እጦት፥ የመናገር፥ የመሰብሰብ መብት የተነፈገዉ ሕዝብ በጣሙን ወጣቱ የየገዢዎቹን ጠንካራ አፈና ተጋፍጦ እንዲያምፅና አመፁን ለማቀጣጠል---

https://p.dw.com/p/R6wz
ምስል AP/DW

07 03 11

ቤን ዓሊን ከቱኒዝ፣ ሙባረክን ከካይሮ አብያተ-መንግስታት ያሽቀነጠረዉ፣የቃዛፊን እና የሳሌሕን በትረ-ሥልጣን የሚገዘግዘዉ፣ከአልጀርስ እስከ ማናማ የሚገኙ ብጤዎቻቸዉን የሚያርበደብደዉ ሕዝባዊ አመፅ መሠረቱ ጭቆና-ረገጣ ሕዝባዊ ብሶት፣የአመፁ አቀጣጣይ-አዛማቹ መገነኛ ዘዴ መሆኑ ብዙዉን አለም አላጠረጠረም።የዩናይትድ ስቴትሷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በቀደም እንዳሉት ግን እሳቸዉ ወይም መንግሥታቸዉ አንድም የብዙዎቹን እምነት ይፃረራሉ።ሁለትም አምባገነኖችን ለማስወገድ የመገናኛ ዘዴዎችን አስተዋፅ ዘንግተዉታል።ወይም ሌላ።እንዴት? ደሞስ ለምን? ጥያቄዉ ማጣቀሻ፣ ሕዝባዊዉ አመፅ መነሻ፣ የመገናኛ ዘዴዎች ሚና ትኩረታችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ሰኔ 6 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጠር ነዉ) አሌክሳደሪያ ሥርቻ ዉስጥ ተሸንቅሮ የተገኘዉ የተቦዳደሰ አስከሬን የማንነት፣ የተጣለበት ምክንያት፣የአሰቃይ-ገዳዮቹ ማንነት ለመላዉ ግብፅ ይሕ ቢቀር ለከተማይቱ መገናኛ ዘዴዎች ትልቅ ዜና-ለአንባቢ፣ አድማጭ ተመልካቾቻቸዉ የመነጋገሪያ ርዕሥ፣ለወንጀል ተከላካይ መርማሪዎች ትኩረትን ሳቢ በሆነ ነበር።

የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች-የሥርዓቱን ወንጀል የሚዘግቡበት፣ የሥርዓቱን ወንጀል የሚፈፅሙት ፖሊሶችም የራሳቸዉን ወንጀል በርግጥ አይመረምሩም።ተዉት።

የወጣቱ የኮምፒዉተር አዋቂ ሞት፣ ከሞቱ አሟሟቱ፣ ከአሟሟቱ የገዳዮቹ ጭካኔ፣ ከጭካኔዉ የመንግስት መገናኛ ዘዴዎች ዝምታ፣ የፖሊሶች ሸፍጥ ያንገበገባቸዉ የሟች የእድሜ-ሙያ ባልንጀሮች ግን ድርጊቱን ሊዘነጉት አልቻሉም።የሃያ ስምንት አመቱ ወጣት ጓደኛቸዉ ከመያዙ በፊት ፖሊሶች ከአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ጋር ተመሳጥረዉ እፁን ሲያስተላልፉ በድብቅ የተነሳ የቪዲዮ ፊልም ለመቅዳት ከኮፒተሩ ጋር ሲታገል አይተዉታል።

Proteste in Tunesien
ሕዝባዊዉ አመፅ-ቱኒዚያምስል dapd

ሰይዲ ጋቤር በሚባለዉ መንደር ከሚሠራበት የኢንተርነት ካፌ አንጠልጥለዉ የወሰዱት ሁለት ሰዎች ሲቢል ይልበሱ እንጂ የዚያዉ መንደር ፖሊስ ጣቢያ ባልደረቦች መሆናቸዉንም ያዉቃሉ።አስከሬኑን እንዳገኙ ለፖሊስ ጣቢያዉ አመለከቱ።የጣቢያዉ ምክትል አዛዥ «ፖሊስ ሲደርስበት የያዘዉን ሐሺሽ ለመዋጥ ሲታገል ሐሺሹ አንቆት ነዉ የሞተዉ» ብለዉ አሰናበቷቸዉ።በቃ።ጓደኛቸዉ እንዲያ አይነት ሰዉ እንዳልነበር ግን ያዉቁታል።

ገዳዮችን፣ የተገደለበትን ምክንያትም ለማወቅ ከዚያ በላይ መጠበቅ መልፋትም አላስፈለጋቸዉም። ሟቹን ለመዘከር ሰደቃ አላወጡም።ሐዉልትም አልጠረቡም።ግን አልረሱትም። እንደ ወጣት፣ እንደ ባለሙያም በሚወዱት መገናኛ ዘዴ የሚወዱትን ጓደኟቸዉን ዘከሩት።በፌስ ቡክ።ገፁንም-እራሳቸዉንም በስሙ ሰየሙት።«እኛ ሁላችንም ኻሊድ ሰኢድ ነን» ብለዉ።የተፈረካከሰ እና የተቦዳደሰ አስከሬኑን ፎቶ ለጠፉት።የአሟሟቱን ታሪክ፣ የተጠርጣሪ ገዳዮቹን ማንነት ዘከዘኩት።

ድንበር የለሽ ዘገባዊች የተሰኘዉ አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና አዘጋጅ ሺል ሎርዴ እንደሚሉት የነባሮቹና የአዳዲሶቹ መገናኛ ዘዴዎች ቅንጅት የአንድ አካባቢ ጉዳይ ብቻ የሚመስለዉን ክስተት አለም አቀፋዊ አድርገዉታል።

«መገናኛ ዘዴዉዎቹ በመጀመሪያ አካባቢያዊ ብቻ ይመስል የነበረዉን ጉዳይ አለም አቀፋዊ ጉዳይ አድርገዉታል።የመገናኛ ዘዴዎች መኖር፥ የጋዜጠኞቹ ጥረት፥እና ሕዝቡ በኢንተርኔት መሳተፉ ፎቶዎችን፥ ፊልሞችን ማሰራጨቱ ሁኔታዉን ሁሉም በፍጥነት እንዲያዉቀዉ አድርጎታል።የምንናገረዉ ሙያዉን ሥለሚያዉቁ ጋዜጠኞች ብቻ አይደለም።ሥለ ብሎገሮች እና ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ዜጎችን ጭምር ነዉ።የሚላኩት መረጃዎች ግብፅና ቱኒዚያ ዉስጥ ሥላለዉ ሁኔታ እንዲያዉቅ አድርጎታል። ከበአካባቢዉ አልፎ በአለም ደረጃም እንዲታወቅ አድርጓል።»

Ägypten Demonstration am Tahrir Platz in Kairo Proteste von Tunis bis Bagdad
ሕዝባዊዉ አመፅ-ተሕሪር አደባባይምስል dapd

የፈርኦኖችን ብልጠት፥የግሪኮችን ጥበብ፥ የሮሞችን ድፍረት፣ የቱርኮችን ጀግንነት፥ የአረቦችን ሥልጣኔ፣ የአዉሮጶችን እዉቀት፣በማይፈርስ አስከሬን-ፒራሚድ፣ በመፀሐፍት-ቅርስ፣ ሐዉልት-ሕንፃ የሚዘክረዉ ግብፃዊ በጣሙን ወጣቱ ለየራሱ የቋጠረ ብሶቱን በኻሊድ ሰበብ፣ በኻሊድ መታሰቢያ አምደ-መረብ አንዱ ለሌላዉ እየዘረገፈ ለአመፅ አገነገነ።

ግን የዘመኑን ፈርኦኖች የዘመኑ ካርቴጆች ቀደሟቸዉ።የዘይን አል አቢዲን ቤን ዓሊ ሥርዓት ኑሮ-ሕይወቱን «ጀሐነብ» ያደረገበት ቱኒዚያዊዉ ወጣት መሐመድ ቡዛዚ ሰዉነቱ ላይ የጫራት ክብሪት አካሉን ስታነድ፥ፌስቡክ ላይ የለጠፋት ኑዛዜ ሕዝባዊ አመፁን ታቀጣጥል ያዘች።የአሌክሳንደሪያ ፖሊስን ግፍ፥ የኻሊድን ግድያ፥ የመሐመድ ቡዛዚን እርምጃ-ኑዜዜን ከየኢንተርኔቱ እየቃረሙ አል-ጀዚራን የመሳሰሉት አዳዲስ ግን ትላልቅ አለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለአረብ በአረብኛ-ለድፍን ዓለም በእንግሊዝኛ ሲያሰራጩት የአብዛኛዉ አረብ ሕዝብ ብሶት በየሐገሩ ፈነዳ።

የቱኒስ፣ የካይሮ፥ የአልጀርስ፥ የሰነዓ፥ የአማን፥ የማናማ፥ የትሪፖሊ ገዢዎች ሕዝባዊዉን አመፅ ለማፋን አመፀኛዉን ከማስደብደብ-ማስገደል አልቦዘኑም። የተንቀሳቃሽ ሥልክ እና የኢንተርኔት፥ መስመሮችን ከመዝጋት፥ ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎችን ማፈናቸዉ ወይም ለማፈን መሞከራቸዉ አልቀረም።እንደገና ሎርዴ

«ለአካባቢ አስተዳዳሪዎች፥ ለፖሊስ ወይም ለጦር ሐይላት መጀመሪያ በቀላሉ የሚያደርጉት ነገር ምሥክር በሌለበት ሠላማዊ ሠልፎችንና የመናገር ነፃነትን በሐይል መደፍለቅ ነዉ።ጋዜጠኞቹ፥ የኢንተርኔት ፀሐፊዎቹ፥ ሕዝቡ ባጠቃላይ ከመንግሥት ሐይላት እርምጃ ተሽቀዳድሞ ሥለየአካባቢዉ ሁኔታ መረጃዎችን ሌላ ሥፍራ ላሉት ሲያሰራጭ ነበር።ይሕ የመረጃ ልዉዉጥ መንግሥታቱ በሆነ ደረጃም ቢሆን ለአለም አቀፍ ሕግጋት እንዲገዙ አስገድዷቸዋል።»

ገዢዎቹ ለአመታት እንደኖሩበት ሁሉ በስተመጨረሻ ሰአታቸዉም በሐገር፥ በሕዝብ፥ በሐብት ንብረት ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር በርግጥ አልተቻለም።አይቻልምም።ይሁንና የወጣቱ ቅልጥፍና የመገናኛ ዘዴዎቹ ብዛት፥ አለም ብዙ መቀራረቧ ምክንያት ሆኖ ገዢዎቹ በመጨረሻ ስትፋሳቸዉ ቢፍጨረጨሩም አንዱን ሲሉት ሌላዉ እያፈተለከባቸዉ ሥርዓታቸዉን ከመገርሰስ ወይም ከመንገዳገድ ሊያድኑት አልቻሉም።

ከመላዉ የአረብ ሕዝብ ኢንተርኔት የሚጠቀመዉ ሃያ አንድ ሚሊዮን ነዉ።የተቀረዉ ኢንተርኔት ባያገኝ ተንቀሳቃሽ ሥልክ፥ወይም የሳተላይት ቴሌቪዥን ባለቤት ነዉ።ከፈርጀ ብዙዉ መገናኛ ዘዴ አንዱ ወይም ሁለቱን የማያጣዉ ያ-ሕዝብ የወጣቶቹን ድርጊት፥ አመፅ እንቅስቃሴ በፍጥነት እና በቀላሉ ማወቅ አልተሳነዉም።አዉቆም ከወጣቶቹ ጎን በፅናት ቆመ።

የመገኛ ዘዴዎች ባለሙያዉ ጄይ ሮሰን እንደሚሉት መገናኛ ዘዴዎች ሰሜን አፍሪቃንና መካከለኛዉ ምሥራቅን ላጥለቀለቀዉ ሕዝባዊ አብዮት መሠረት አይደሉም።በርግጥም የየስሚን፣ የአባይ ይባል ወይም ሌላ ከቱኒዝ እስከ ሰነዓ በሚገኙ አምባገነኖች ላይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ መሠረቱ ገዢዎቹ የሚያደርሱት ጭቆና፥ ሐያሉ አለም ለየገዢዎቹ የሚሰጠዉ ድጋፍ በሕዝቡ ዘንድ ያሳደረዉ ምሬትና ብሶት ነዉ።

መገናኛ ዘዴዉ ለሕዝባዊዉ አመፅ መሠረት አይሁን እንጂ የኑሮ ዉድነት፥ ሥራ አጥነት፥ የዲሞክራሲ እጦት፥ የመናገር፥ የመሰብሰብ መብት የተነፈገዉ ሕዝብ በጣሙን ወጣቱ የየገዢዎቹን ጠንካራ አፈና ተጋፍጦ እንዲያምፅና አመፁን ለማቀጣጠል ሮሰን እንደሚሉት «ዋና ግብአት መሆናቸዉ አያጠራጥርም።»

ነባሩ መገናኛ ዘዴ በዘመናዊዉ እየተጋዘ ያቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ ቤን ዓሊንና ሙባረክን ከስልጣን ካስወገደ በሕዋላ ፥ የቃዛፊን እና የሳሌሕን ሥልጣነ-ሕልቅት ፈጥርቆ በያዘበት፥ከመካከለኛዉ ምሥራቅ እስከ አፍሪቃ፥ ከምሥራቅ አዉሮጳ እስከ እስያ ያሉ አምባገነኖችን በሚርበተብትበት ወቅት አሁን የዩናትድ ስቴትሷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ብቸኛዋ ልዕለ ሐያል ሐገር የመገናኛ ዘዴዎች ጦርነት ገጥማለች አሉ።ተሽንፋለችም።

የግብፅ ሕዝብ አመፅ ሰላሳ ዘመን የፀናዉን የሆስኒ ሙባረክን ሥርዓት ሲገረሰስ፥ ለሙባረክ መንግሥት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ሥትሰጥ ለቆየች ለዩናይትድ ስቴትስ የዉጪ መርሕ አንዳዶች እንደሚሉት ታላቅ ሽንፈት ይሆን ይሆናል።የቱኒዚያ ሕዝብ አመፅ የቤን ዓሊን የሃያ-ሰወስት ዘመን ሥርዓት ሲገረስ እስከ መጨረሻዉ ድረስ ከቤን ዓሊ ጋር የሙጥኝ ብላ የነበረችዉን የፈረንሳይን ካቢኔም መበጥበጡም ሐቅ ነዉ።

Libyen Aufstände Proteste
ሕዝባዊዉ አመፅ-ሊቢያምስል dapd

መገናኛ ዘዴዎች የየሐገሩን አብዛሐ ሕዝብ ብሶት፥ ምሬት፥ የዲሞክራሲ ፍላጎት ማንፀባረቃቸዉ ለዲሞክራሲያዊዉ ሥርዓት ቀንድሊቱ ሐገር «ጦርነት-እና ሽንፈት» መሆኑ ፈረንሳዊዉ የመገናኛ ዘዴ አዋቂ ሺል ሎርዴ እንደሚሉት አይገባም።

«የመገናኛ ዘዴዎች ጦርነት ሥለመኖሩ የማዉቀዉ ነገር የለም።የምትለዉ ሥለ ፕሮፓጋንዳ ጦርነት ከሆነ ጦርነቱ የነበረዉ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ነበር።አይደለም።አሁን ብዙ ሐገሮች በመገኛ ዘዴዎች ላይ እየወረቱ ነዉ።ይሕ ደግሞ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እንዲኖሩ፥ የተለያዩ ሐሳቦችን ለማስተናገድ ጠቃሚ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ በመገኛ ዘዴዎች ጦርነት ተሸንፋለች ማለት መቻላችንን አላዉቅም።ምክንያቱም ዩናይትድ ስቴትስ በጣም ጥሩ ጋዜጠች፥ መገናኛ ዘዴዎች እና ጠንካራ የጋዜጠኝነት ሥንፀሐሳብ አለ።ማለት የምንችለዉ አሁን ትላልቅና በጣም ጠቃሚ መገናኛ ዘዴዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ አሉ ነዉ።»

የፈረንሳይ ሶሻሊስቶች፥የሩሲያ ኮሚንስቶች፥የጀርመን ናትሲዎች፥ የኢጣሊያ ፋሺስቶች የመሯቸዉ አብዮቶች፥ ሌላዉ ቀርቶ የአረብና የአፍሪቃ የጦር መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት አነሰም በዛ የየዘመኑን ሕዝብ ድጋፍ አላጡም ነበር።በየሐገሩ ሥልጣን የያዙት ሐይላት ግን ከየቀዳሚዎቻቸዉ ገዢዎች መባሳቸዉን አለም በተደጋጋሚ መስክሯል።እራሳቸዉን የዲሞክራሲ ጠበቃ፥የሕዝብ መብት የፕረስ ነፃነት ተቆርቋሪ፥ የሚሉት ሐይላት አሽነፍን-ተሸንፍን ከማለት ይልቅ ያሑኑ ሕዝባዊ አብዮት የቀዳሚዎቹ እጣ እንዳይደርሰዉ ከጣሩ ነዉ የሚሉትን የሚሆኑት።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ