1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል በማለታቸው የተሰናበቱት ዳኛ

ዓርብ፣ የካቲት 11 2008

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በስነ-ምግባር ጉድለት የከሰሳቸውን ሶስት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አሰናብቷል። ከሶስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል የሚል አቋም መያዛቸው አንዱ መሆኑ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/1Hynu
Symbolbild Justitia Justizia
ምስል Imago

[No title]

አቶ ግዛቸው ምትኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስነ-ምግባር ችግር ታይቶባቸዋል በማለት ካሰናበታቸው ሶስት የኢትዮጵያ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትዳኞች መካከል አንዱ ናቸው። የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ማስረጃ በአቶ ግዛቸው ምትኩ ላይ አራት ክሶች የመሰረተ ሲሆን "ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ የሚጠቅሱ በመሆኑ፣ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ባለመሆናቸው" የሚለው ይገኝበታል።

የህግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሐይለማርያም የምክር ቤቱ ውሳኔ በፍርድ ሒደት ጣልቃ መግባት ነው ሲሉ ኮንነውታል።

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ምክር ቤቱ አቶ ግዛቸው ምትኩን «ህገ-መንግስቱን በታማኝነት ሙሉ ለሙሉ ባለመቀበላቸውና የዳኝነትነ ጻነትና ገለልተኝነት የጎደለባቸው» በማለት ሲያሰናብት ግፍ ፈጽሟል ሲሉ ይተቻሉ።

አቶ ግዛቸው ምትኩ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከተከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል ''ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ያልሆነችው መንግስት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰት ስለ ሚፈጽም ተጠያቂ ላለመሆን ነው፣በኢትዮጵያ የብሔር እኩልነት አልተረጋገጠም"ብለዋል የሚል ይገኝበታል። አቶ ግዛቸው ምትኩ በያዙት አቋም ገለልተኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ከዳኝነታቸው ተሰናብተዋል። ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሐይለማርያም ለሕገ-መንግስት መሻሻል እንደ አቶ ግዛቸው ምትኩ በዳኝነት መንበር የተቀመጡ ባለሙያዎች ቀስቃሽ ሚና እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የኢትዮጵያ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አወቃቀር የዳኞችን ነጻነት የሚነካ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከአቶ ግዛቸው ምትኩ በተጨማሪ በስነ-ምግባር ግድፈት የተከሰሱ ሁለት ዳኞች በተወካዮች ምክር ቤት ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። የኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስቴር በአምስት አቃብያነ ህግጋት ላይ የስነ-ምግባር ክስ መመስረቱን አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ