1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገ ወጡን የአውራሪስ ንግድ የማስቆሙ ሳይንሳዊ ጥረት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 2007

በአፍሪቃ የመጥፋት ስጋት የተደቀነባቸውን አውራሪሶች ከሕገ ወጥ አዳኞች ለመጠበቅ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ከነዚሁ መካከል የደቡብ አፍሪቃ ተመራማሪዎች የጀመሩት በዘመናዩ የ«ዲ ኤን ኤ» ምርመራ ቴክኒክ የሚያደርጉት ምዝገባ እና በዩኤስ አሜሪካ የተጀመረው የአውራሪስን ቀንድ በቤተ ሙከራ የማምረቱ ስራ ይጠቀሳል።

https://p.dw.com/p/1GLi2
Wilderei Nashornjagd
ምስል BIJU BORO/AFP/GettyImages

ሕገ ወጡን የአውራሪስ ንግድ የማስቆሙ ሳይንሳዊ ጥረት

በዓለም ዝሆን፣ አውራሪስ፣ ነብር፣ አንበሳ እና ጎሽን የመሳሰሉ የዱር አራዊት የመጥፋት ስጋት ተደቅኖባቸዋል። በተለይ ለመድሀኒትነት ይፈለጋሉ የሚባሉት የአafeሪቃ አውራሪሶች ሕገ ወጥ አደን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ነው። ደቡባዊ አፍሪቃ ዉስጥ ምንም እንኳን አራዊቱ የሚኖሩባቸው የብሔራዊ መካነ አራዊት ወይም የፓርኮች ጠባቂዎች፣ የሃገራቱ ፖሊስ እና የጦር ኃይላት ፣ እንዲሁም ፣ መንግሥታት የሚያወጡዋቸው ሕጎች፣ የተደራጁ ቡድኖች ያስፋፉትን ሕገ ወጡን አደን ለማስቆም ጥረት ቢያደርጉም፣ በያመቱ እጅግ ብዙ የዱር አራዊት ይገደላሉ። ለምሳሌ በዚችዉ ሀገር ባለፈው አውሮጳዊ ዓመት 2014 ብቻ ከ1,200 የሚበልጡ አውራሪሶች በሕገ ወጦቹ አዳኞች ተገድለዋል። ይህም እአአ በ2007 ከነበረው በ9000 ከመቶ በልጦ ነው የተገኘው። በ2015 ያለፉት ስድስት ወራት ደግሞ 596 አውራሪሶች ነበሩ በሕገ ወጦቹ አዳኞች የተገደሉት። ይህ ሕገ ወጡ አደን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ማሳየቱን ለዱር አራዊት ጥበቃ እና ልማት የሚሰራው የ«Born Free Foundation» የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ዘላለም ተፈራ አመልክተዋል።

Südafrika Kruger National Park Nashörner
ምስል Bobby Bascomb

በመድሀኒትነት ያገለግላል በሚባለው የተለያየው የአውራሪስ የሰውነት አካል፣ በተለይ በቀንዱ የሚካሄደው ንግድ በጣም ትርፋማ በመሆኑ ነው እነዚህ እንሰሳት አዘውትረው የሕገ ወጥ አዳኞች ዒላማ መሆናቸው የቀጠለው። የአውራሪስ ቀንድ ተፈጭቶ የሚገኘው ዱቄት በእስያ ፣ በተለይ በቻይና እና በቪየትናም ላዕላዕ መደብ አባላት ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ ነው። ዱቄቱ ከተለያዩ ንጥረነገሮች ጋር ሲደባለቅ ለልዩ ልዩ የበሽታ ዓይነቶች መፈወሻ እና በዕድሜ ጠና ላሉ ሰዎች ለወሲብ መቀስቀሻ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው የሚነገረው። ሌሎች ደግሞ ዝና እና ክብር ለማግኘት ሲሉ የቀንዱ ባለቤት መሆን ይፈልጋሉ፣ ሌሎችም ለጌጣጌጥ ንግዱ ይጠቀሙበታል። አንድ ኪሎ የአውራሪስ ቀንድ በስውሩ ገበያ የሚሸጠው ለአንድ ኪሎ ወርቅ ወይም ለአንድ ኪሎ ሕገ ወጡ አደንዛዥ ዕፅ ኮኬይን ከሚከፈለው ገንዘብ ይበልጣል። እስከ 100,000 የአሜሪካ ዶላር ይሸጣል።

USA Künstliches Rhinohorn (Bildergalerie)
ምስል DW/G. Hofmann

የዱር እንሰሳት ጥበቃ መስሪያ ቤቶች እና ተሟጋቾች ከብዙ ጊዜ ወዲህ አራዊቱን ከሕገ ወጥ አዳኞች ለመከላከል እና አዳኞቹን ለመያዝ ያስችላል ያሉትን ዘዴ ከማፈላለግ ቦዝነው አያውቁም። በዚሁ ጥረት መሠረትም በደቡብ አፍሪቃ የፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ተመራማሪዎች በዘመናዩ የ«ዲ ኤን ኤ» ምርመራ ቴክኒክ መጠቀም ጀምረዋል። ይህንኑ ሥራ እንዴት እንደሚያካሂዱ ዶክተር ሲንዲ ሀፐር በቤተ ሙከራቸው ላነጋገራቸው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ያን ፊሊፕ ሽሉተር እንዳስረዱት፣ ሕገ ወጥ አዳኞች የአውራሪሱን ቀንድ ለመቁረጥ የሚጠቀሙበትን ቢላ፣ ዶማ እና ባህላዊው ቆንጨራ በመሰብሰብ የአውራሪስ ደም እንዳለበት ከመረመሩ በኋላ የዘረመል አሻራ ለመለየት ይሞክራሉ።

ሲንዲ ሀፐር ከአምስት ዓመታት በፊት በእንግሊዝኛ አህፅሮቱ «RhODIS» በመባል የሚታወቀውን የአውራሪስ ዘረመል ባንክ በማዘጋጀት በደቡብ አፍሪቃ እና በሌሎች አምስት አፍሪቃውያት ሃገራት ያሉትን አውራሪሶችን የመመዝገብ ሥራ የጀመረው የፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ዘረመል ላቦራቶሪ ወይም ቤተ ሙከራ ኃላፊ ናቸው።

« የአውራሪሶቹን የዘረመል ዝርዝር ታሪክ መዝግበናል። ይህ ዓይነት ምዝገባ ሲደረግ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚሁ ሥራችን አማካኝነት የአንድ አውራሪስ ቀንድ እና የተገደለበትን ቦታ ማስተያየት እንችላለን። ይህም ወንጀለኞቹን ለመያዝ የሚጠቅም ጠንካራ ማስረጃ ነው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድ የተሸጠ ቀንድ የነበረበትን ባዶ ጆንያ አገኘን። ከጥቂት አቧራ በስተቀር ምንም የሚታይ ማስረጃ አልነበረውም። ግን ለኛ የተገደለውን አውራሪስ ዝርዝር ታሪክ ለማውጣት ለመለየት በቂ ነበር። በዚሁ ምርመራችን ወቅት በክሩገር ብሔራዊ ፓርክ የነበረ በሕገ ወጥ መንገድ የተገደለ አውራሪስ ቀንድ መሆኑን ለማጣራት ችለናል። »

USA Künstliches Rhinohorn (Bildergalerie)
ምስል DW/G. Hofmann

እስካሁን 18,000 አውራሪሶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ሀርፐር እና ቡድናቸው ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ወንጀለኞችና በሕግ እንዲቀጡ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸዋል። የእነ ዶክተር ሀርፐር ጥረት አውራሪሶቹ ከተገደሉ በኋላ ገዳዮቹን ለመያዝ እና ሌሎች ሕገ ወጥ አዳኞች እና ነጋዴዎችን በዚህ ተግባራቸው እንዳይገፉበት የሚረዳ ነው። እንደ ዶክተር ዘላለም አስተሳሰብ፣ ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ የደቡብ አፍሪቃ ተመራማሪዎች የጀመሩት የዘመናዩ «ዲ ኤን ኤ» ምርመራ ቴክኒክ የጀመሩት ምዝገባ ውጤታማነት ያን ያህል አይደለም።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሜሪካውያኑ ኬሚስት እና የባዮሎጂ ተመራማሪው ማቲዩ ማርኩስ እና ጆርጆ ቦናቺ ቀንዱን በቤተ ሙከራ ማምረት የመጥፋት ስጋት የተደቀነባቸውን አውራሪሶቹ ሳይገደሉ በፊት ኅልውናቸውን ለመጠበቅ ያስችላል በሚል ቀንዱን ማምረት ከጀመሩ ሰንበት ብሏል። ይሁንና፣ የአውራሪሱን ቀንድ በቤተ ሙከራዉ ውስጥ ማምረቱም ካለአስተሳሰብ ለውጥ ብቻውን የተፈለገውን ጥቅም እንደማያስገኝ ነው ዶክተር ዘላለም ያስታወቁት።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ