1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሩዋንዳ 

ሰኞ፣ የካቲት 27 2009

በሩዋንዳ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ማሸጋገር በሀገሪቱ ከሚፈፀሙ ከባድ ወንጀሎች አንዱ ነው። ይህ ወንጀልም ከቀድሞው አሁን እየጨመረ መሄዱ ነው የሚነገረው። የሩዋንዳ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ድንበሯን ክፍት ያደረገው መርህዋ ሀገሪቱ ከኬንያ እና ከጎረቤት ኮንጎ የሚመጡ ሕገ-ወጥ የሰው አሻጋሪዎች ዒላማ እንድትሆን አድርጓታል።

https://p.dw.com/p/2Yj4Q
Symbolbild Human Trafficking
ምስል AFP/Getty Images

Human trafficking in Rwanda* - MP3-Stereo

ለብዙ ሩዋንዳውያን ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ እረፍት የሚያገኙበት ቦታ ነው። ለጀምስ ሙሬንዚ ግን ከዚያ በተቃራኒው ነው የሆነበት። ከቤተ ክርስቲያኑ ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኝ ቦታ የብሩንዲ ዜግነት ያላቸው የቤተ ክርስቲያንዋ ቄሶች የምድር ገነት እንዳለ ቃል ገብተውለት አምኗቸው ያሉትን አድርጎ ነበር። ሙሬንዚ የብሩንዲ ደላላዎች እየተጠጉ ሥራ እና ሌሎች ጥቅሞች እንደሚያገኙ ቃል ገብተውላቸው ተታለው የኮንጎ ዜግነት ላላቸው ሰው አሻጋሪዎች አሳልፈው ከተሰጡ 28 ሩዋንዳውያን አንዱ ነው። ሆኖም ሙሩንዚን የሩዋንዳ የፀጥታ ኃይሎች ታድገውት ከከፋው ችግር ሊተርፍ ችሏል። እርሱ እንደሚለው ሰዎችን ለዚህ ችግር የሚዳርገው ሥራ አጥነት ነው። 

«ለፀሎት ቤተ ክርስቲያን በተገኘሁበት ወቅት ከብሩንዲ የመጡ ቄሶች ወደ እኔ መጥተው አማላይ ሃሳባቸውን አካፈሉኝ ። እኛ ከወሰድናችሁ ቤት እንሰጣችኋለን ፣ ጥሩ ሥራ ፣ ጥሩ ደሞዝ እና ነፃ የጤና ዋስትና ታገኛላችሁ አሉን ።ዒላማ ያደረጉት ገንዘብ የሚያስፈልጋቸውን ችግር ላይ የወደቁትን ሥራ ያጡ ወይም ሌላ ቤተሰባዊ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ነው ። ይህ አይነቱ ሥራ የሚካሄደውም ቄስ የሚባሉትን ሰዎች በቀጠሩ ኮንጎ በሚኖሩ ሰዎች ቡድን ነው። እኛም የኮንጎ ስደተኞች ተብለን እንድንሄድ ነበር የታሰበው ።እናም እኔ የሰው አሻጋሪዎች ሰለባ ልሆን እችል ነበር።»

የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣ ዘገባ በብሩንዲ አለመረጋጋት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ወደ ሩዋንዳ ከሚሰደዱት ውስጥ አንዳንዶቹ ህጻናትን ጨምሮ ለወሲብ ንግድ እና ገንዘብ ለማያገኙበት የቤት ሥራ ይዳረጋሉ። ሀገሪቱ ሥራ ታገኛላችሁ የሚል ቃል እየገቡ የብሩንዲ እና የኮንጎ ዜጎችን በቀላሉ የሚያጠምዱ ሰው አሻጋሪዎች መተላለፊያ ሆናለች ። የነዚህ ሰለባ ከሆኑት አንዱ ብሩንዲያዊው አይሳክ ንዮጌና ነው ። ወደ ቃታር ለመሄድ መንገድ ጀምሮ ወታደሮች መልሰውታል ። መጀመሪያ ለመሄድ ያሰበው ግን ቃታር አልነበረም ። 

Griechenland Demonstration gegen Menschenhandel in Athen
ምስል Louisa Gouliamaki/AFP/Getty Images

«ብሩንዲ እያለሁ ሥራ አልነበረኝም ። ኡጋንዳ ከፍተና ትምህርቱን የሚከታተል ጓደኛ ነበረኝ ። ለበዓል ሲመጣ አግኝቼው እርሱ ያለበት ሀገር ቀጥረው ሊያሰሩኝ የሚችሉ ሰዎች እንዳሉ ጠየቅኩት ። ሥራ ሊሰጠው የሚችል ጓደኛ እንደሌለው ነገር ግን ቃታር ስራ የማግኘት እድል እንዳለ ነገረኝ ።»

የሩዋንዳ አቃቤ ህግ ዦን ቦሶኮ ሙታንጋና እንደሚሉት ሰዎችን በህገ ወጥ መንገደ የሚሸጋገሩበት ወንጀል በርግጥ ለሩዋንዳ ከፍተኛ ችግር ነው ።እርሳቸው እንደሚሉት መንግሥት እስካሁን አንዳንዶቹን ሰው አሻጋሪዎች ለፍርድ ማቅረብ ችሏል ።ይሁንና ችግሩ ከዓመት ወደ አመት እየተባባሰ በመሄዱ መንግሥት ይበልጥ ራሱን ማዘጋጀት አለበት ይላሉ። 

«ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀሎች ተፈታታኝ ናቸው ። ምክንያቱም ወንጀሉ በተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን  ነው የሚፈፀመው ። ያም ሆኖ አንዳንዶቹን ለፍርድ ማቅረብ ችለናል። በጎርጎሮሳዊው 2012 ፣ 12 የክስ ዶሴዎች ነበሩ የደረሱን ። ዓመቱ በጨመረ ቁጥር ግን ወንጀሉ እየጨመረ ነው የሄደው ። በ2014 10 ደረሱ ፣ ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ደግሞ 51 ሆኗል። እነዚህ ቁጥሮች እየጨመሩ ነው ። በሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ምን እንደሚሆን ደግሞ አናውቅም ።»

ሩዋንዳ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት በጎርጎሮሳዊው 2003 አጽድቃለች ። ይሁን እስከ 2012 ድረስ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ የሚያሻግሩ ወንጀለኞችን የሚቀጣው ህግ የሩዋንዳ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አካል አልነበረም ።

 ናስራ ቢሹምባ/ኂሩት መለሰ 

አዜብ ታደሰ