1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መስቀል ክብረ በዓል- በዓለም የቅርስ መዝገብ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3 2006

የኢትዮጵያዉ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል /UNESCO/መዝገብ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦአል። የዚህ ክብረ በዓል በዓለም መዝገብ መፃፉ ለኢትዮጵያ የሚያመጣዉ ፋይዳ ምን ይሆን? ኢትዮጵያ እስከ ዛሪ ዘጠኝ ታሪካዊ ቅርሶችን በ UNESCO መዝገብ በማፃፍ ከአፍሪቃ ቀዳሚዋ ሀገር መሆንዋ ያዉቃሉ?

https://p.dw.com/p/1AXRh
Meskel Festival
ምስል DW/A. Hahn

ባለፈዉ ሰምወን አዘርባጃን መዲና ባኩ ላይ በተካሄደዉ ስምንተኛው የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል/UNESCO/ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያዉ የመስቀል በዓል አከባበር በዓለምቅርስነት ተመዝግቦአል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ታዳሽ ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ የመስቀል ባህላዊ ክብረ በዓል አስረኛውና የመጀመሪያው የማይዳሰስና የማይጨበጥ (ህሊናዊ) ባህላዊ ቅርስ በመሆን ነዉ የተመዘገበዉ። በዕለቱ ዝግጅታችን የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም አቀፉ የቅርስ መዝገብ እንዴት ሊመዘገብ እንደቻለ እና የዚህ ክብረ በዓል በዓለም መዝገብ መፃፉ ለኢትዮጵያ የሚያመጣዉን ፋይዳ ባለሞያዎችን አነጋግረን ዝርዝር ዘገባ ይዘናል፤

Feier von Äthiopische orthodox Kirsche in Deutschland
ምስል DW
Logo Unesco englisch
ምስል Unesco

የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል/ዩኔስኮ/ በቅርስነት የተመዘገበዉ ባህላዊዉ የመስቀል በዓል አከባበር፤ ባኩላይ በተደረገዉ ጉባኤ ላይ ከዓለም ሀገራት ከቀረቡ 31 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ መመረጡ ተነግሮአል። በተለያዩ ስነ-ፅሁፎቹ የሚታወቀዉ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ባህላዊዉ የመስቀል ክብረ በዓል በዓለማቀፉ የቅርስ መዝገብ በመፃፉ እጅግ ደስ ብሎኛል ሲል ገልጾልናል። በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ማለትም ህሊናዊ ቅርስ ለመጀመርያ ግዜ በዓለማቀፉ የቅርስ መዝገብ መስፈሩን የነገሩን በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፤ የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር፤ አቶ ደሳለኝ አበባዉ፤ የአንድ ሀገር ቅርስ በዋናነት በሁለት ይከፈላል፤ የሚዳሰስና የማይዳስ በማለት በዝርዝር አስረድተዋል።

ቅርስ ስንል የሚዳሰስ የሚታየዉን የቆየ ታሪክ ብቻ ስለምናስብ ነዉ እንጂ ከየትኛዉም በላይ ኢትዮጵያን የሚገልፃት፤ በተለያየ ብሄር በሄረሰቦችዋ ዘንድ የሚታየዉ ባህላዊ አከባበር የተለያየ ጥንታዊ ልምድ ነዉ፤ ነዉ ያለን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሄር ብሄርሰቦች ዘንድ የሚታየዉ ማንኛዉም ባህላዊ ክብረ በዓል እና ባህላዊ ክንዋኔ የኢትዮጵያን ታሪክ አንድነት እና እድገት ገላጭ ነዉ ሲል ተናግሮአል። በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፤ የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር፤ እንደ አቶ ደሳለኝ አበባዉ፤ መስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ ለኢትዮጵያ የመጀመርያዉ ቢሆንም፤ በተለያዩ ብሄረሰቦች የሚታየዉ የተለያየ ጥንታዊ ባህል በምዝገባ ላይ መሆኑን ሳይገልፁ አላለፉም። እስከ ዛሪም በዓለማቀፉ የቅርስ መዝገብ የኢትዮጵያ ዘጠኝ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪቃ ቀደምቱን ቦታ መያዝዋም ተነግሮአል። አቶ ደሳለኝ አበባዉ በመቀጠል እንደ መስቀል በዓል አከባበርን የመሰሉ ባህላዊ መለያዎች በቅርስነት እንዲያዙ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሚዲያዎች ባህሉን ለማህበረሰቡ በማስተዋወቁ ረገድ ትልቅ ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ገልፀዋል። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩል እንደመስቀል አይነቶቹን ኢትዮጵያዊ መለያ ክብረ በዓላት ቱፊቱን፤ ልምዱን ጠብቀዉ እዚህ ያደረሱትን አባቶች በማመስገንመጭዉ ትዉልድ ይህንኑ ባህል ሳይበርዝ ጠብቆ ለትዉልድ ማስተላለፍ አለበት ሲል ተናግሮአል። ቃለ ምልልሱን የሰጡንን እያመሰገንናለን፤ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ያድምጡ!

Meskel Festival
ምስል DW/A. Hahn

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ