1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቆም ያለበት ልማድ የሴት ልጅ ግርዛት

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2009

በመላዉ ዓለም የሴትን ልጅ የመዋለጃ አካል የመተልተል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ በሚፈፀምባቸዉ ሃገራት 200 ሚሊየን የሚሆኑ ሴቶች የዚህ ሰለባ መሆናቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በየዓመቱም 3 ሚሊየን ሴት ልጆች ለዚህ የተጋለጡ መሆናቸዉም ተገልጿል። ድርጊቱ አፍሪቃ ዉስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለይ በ27 ሃገራት በስፋት ይፈጸማል።

https://p.dw.com/p/2X7jC
Sierra Leone Mädchen vor der Beschneidung
ምስል picture-alliance/robertharding/L. Taylor

M M T/ AMh Umwelt & Gesundheit 07.02.2017 (FGM a must abandon tradition) - MP3-Stereo

 

 በየመን፣ በኢራቅ ኩርዶችና ኢንዴኔዢያም የተለመደ ነዉ። ተጨባች መረጃዎች አልወጡም እንጂ በሌሎች የእስያ እና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሃገራትም ሊፈጸም እንደሚችል ጥርጣሬ አለ። በምዕራብ አፍሪቃ የቤኒን፣ የኒዠር እና የቡፍኪና ፋሶ ቀዳማይ እመቤቶች በየሀገራቸዉን ድርጊቱ እንዲቆም ለማድረግ ታጥቀዉ መነሳታቸዉን ትናንት አመልክተዋል።  የተመድ እንደሚለዉ ዕድሜያቸዉ ከ15 እስከ 49 ከሚደርሱ ሴቶች 70 በመቶዉ ድርጊቱ ተፈፅሞባቸዋል። ኢትዮጵያ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2004 ዓ,ም ጀምሮ በይፋ የሴት ልጅ ግርዛት እንዳይፈፀም አግዳለች። ተግባሩ ግን አሁንም ዉስጥ ዉስጡን መፈጸም መቀጠሉ ነዉ የሚነገረዉ።

ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በሴቶች ላይ የሚያስከትለዉን አሉታዊ ተፅዕኖ በማገናዘብ እንዲቆም ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በህክምና ሙያ የተሰማሩ አንዳንዶች በድብቅ ሴት ልጆችን መግረዝ መገጠላቸዉ ሊገኝ የሚችለዉ አዎንታዊ ዉጤትን እያደናቀፈ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ምሁራን ይፋ አድርገዋል። ሴት ልጅ የመግረዙ ልማድ እንዲቀር ትምህርት እና ቅስቀሳ ከተጀመረ፤ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት አልፈዋል። በአንዳንድ አካባቢ በዚህ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎችን በማስተማር ከድርጊቱ እንዲታቀቡ ለማድረግ ተሳክቷል። እንደ አፋር ያሉት ድርጊቱ በከፋ መልኩ ይፈጸምባቸዉ የነበሩ አካባቢዎች ደግሞ ጠንከር ያለ ሕግ አዉጥተዉ ለመቆጣጠር እየጣሩ ነዉ። አሁንም ግን ድርጊቱ በከተማም ሆነ በገጠር በስዉር መቀጠሉ ነዉ የሚሰማዉ።

Elfenbeinküste Mädchen bei Information Aufklärung gegen weibliche Genitalverstümmelung Female Genital Mutilation / Cutting (FGM / C) der UNICEF
ምስል picture-alliance/dpa/Unicef/Asselin

በአካላዊ ጤናም ሆነ ስነልቦናዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ተደጋግሞ የተገለጸዉ ሴት ልጅን መግረዝ እንዲቀር የሚደረገዉ ቅስቀሳ እና ጥረት በየአካባቢያችሁ ምን ያህል ዉጤት አምጥቷል ትላላችሁ በሚል ከዶቼ ቬለን የፌስቡክ ገጽ ተከታዮች አሰተያየት ለማሰባሰብ ሞክረን ነበር።  ይህን ርዕሰ ጉዳይ ከ19 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተመልክተዉታል፤ የተወያዩበትም ጥቂት አይደሉም። ከዉይይቱ የተረዳነዉም ይህ ጉዳይ ዛሬም ደጋፊና ነቃፊዎችን በጎራ ለይቶ ማነጋገር መቀጠሉን ነዉ። በአንዳንድ አካባቢዎች የተካሄደዉ የማስተማር ሥራ ዉጤት ማሳየት መጀመሩ ይነገራል። ለምሳሌም ድርጊቱ በከፋ ሁኔታ እንደሚፈፀምባቸዉ ከሚነገርላቸዉ አካባቢዎች አፋር አንዱ ነዉ። ዛሬ የአፋር ልጃገረዶች ከዚህ ሙሉ ለሙሉ ተርፈዋል ባይባልም እየቀነሰ መሄዱ ግን እየታየ መሆኑን የአካባቢዎ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በአፋር ክልል በወጣዉ ሕግ መሠረት ሲገርዝ የተገኘም ሆነ የተረጋገጠበት እስከ 6 ዓመት እስራት፤ ሴት ልጃቸዉን ያስገረዙ ወላጆች ደግሞ እስከ ስድስት ወር እስራት ሊያስቀጣቸዉ ይችላል። በአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ድርጊቱ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ በይፋ ከተደነገገ ዓመታት አልፈዋል። ሕግና ደንቡን በማጽደቁም ሆነ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቆም የሚንቀሳቀሱ መርሃግብሮችን በመዘርጋቱ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ችግር ያለ አይመስልም። በየደረጃዉ የሚገኙ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም ያንን በአግባቡ ያረጋግጣሉ። ደንብና ሕጉ ግን ድርጊቱን ከመፈጸም ያገደዉ እንደማይመስል ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት። ሙሉዉን ቅንብር ከድምጽ ዘገባዉ ኢድምጡ!

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ