1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት የሚያባብሱ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል

ማክሰኞ፣ መስከረም 16 2010

የኢትዮጵያ መንግስት  በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ መልዕክቶች ላይ ተደጋጋሚ ስጋቱን ሲገልጽ ይስተዋላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልል መንግስታት መገናኛ ዘዴ፣ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች እና ኃላፊዎቻቸው ጭምር የሚሰራጩ መረጃዎችም እንደሚያሳስቡት በተለያየ መልኩ ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2kkPr
Mauritius Internet cafe Facebook neben der alten Kirche in Gondar Äthiopien
ምስል Imago/ZUMA Press

በመገናኛ ዘዴዎች ግጭት የሚያባብሱ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል

የዛሬ ዓመት ግድም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት አጽንኦት የሰጡት አንድ ጉዳይ ነበር - የማህበራዊ መገናኛ ዘዴን።

“ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በዲጂታል መድረክ የመረጃ ልውውጥን እንደማሻሻሉ እና የብዙሃንን ተሳትፎ እንደማጎልበቱ የሚያመጣቸው አሉታዊ ተጽእኖዎችም በቀላሉ ችላ የሚባሉ አይደሉም፡፡ የተሳሳተ መረጃ በማህበራዊ መገናኝ ብዙሃን እንዴት በአጭሩ እንደሚሰራጭ እና በርካታ ሰዎችን በተለይም የወደፊት ተረካቢዎቻችን ወጣቶችን እንደሚያሳስቱ አይተናል፡፡ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በእርግጥም አጫጭዋኺዎችን እና ሌሎች ጽንፈኞችን የህዝቡን እውነተኛ ብሶት አላግባብ እንዲጠቀሙበት አስችሏቸዋል፡፡ ያለምንም ተአቅቦ የጥላቻ እና የአክራሪነት መልዕክቶቻቸውን አሰራጭተዋል፡፡”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ከተናገሩ በኋላ በሀገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ መንግስት እርምጃዎች መውሰድ ጀመረ፡፡ ተቃውሞውን ለመግታት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከልም የማህበራዊ መገናኛዎችን ለይቶ መዝጋት ባሰ ሲልም ኢንተርኔትን ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱ አሰራር ተቃውሞዎች በሚበረቱባቸው ጊዜያት እንደቀጠሉ አሉ፡፡

Äthiopien Debre Zeit (Bishoftu) - Smartphone Nutzung
ምስል DW/T. Waldyes

የዛሬ ዓመት የኢትዮጵያን መንግስት አሳስቦት የነበረው መናኸሪያቸውን ከሀገር ውጭ ያደረጉ የፖለቲካ ቡድኖች፣ አራማጆች እና የመብት ተሟጋቾች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች እና የሚያደርጓቸው ቅሰቀሳዎች ነበሩ፡፡ ይኸው ስጋቱ ከዓመት በኋላ እንዳለ ቢሆንም ከገዢው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች የሚሰነዘሩ መልዕክቶች፣ ትችቶች እና መግለጫዎች እረፍት ይነሱት ይዘዋል፡፡

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በቅርቡ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዎች ዘንድ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በነበረው የቃላት ጦርነት ላይ የፌደራል መንግስት  በግልጽ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡  ጠብ አጫሪ ያላቸውን መልዕክቶች በሚያስተላልፉት ላይም እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫም ይህንኑ አንጸባርቀዋል፡፡

“ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ የሙያ ስነ ምግባሩን በመከተል ለዜጎቻችን መረጃ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ የሚበረታታ ስራ የሚሰሩ ወይም ደግሞ ግጭቶች እንዲቆሙ ዜጎቻችን ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በዲሞክራሲ ግንባታ፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያደርጉ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተዋናዮች አሉ፡፡ በተጻጻሪው ግን በሀገር ውስጥ የሚደረገው ማንኛውም መልካም ነገር የማያስደስታቸው፣ በህዝቦች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት፣ ሰላም የማያስደስታቸው አካላት፣ ሌት ተቀን ተግተው የሚሰሩ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ ለአንዱ የወገነ ወይም ደግሞ ለአንዱ የሚወግኑ እየመሰሉ ነገር ግን ስርዓቱ ያልቆመለትን ዓላማ የሚያራምዱ ግለሰቦች ደግሞ አሉ፡፡ 

ይህንን መንግስት ብትኩረት እየተከታተለ ከምንጫቸው፣ አንደኛ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እየመከራቸው፣ ካልሆነ ግን ይሄ ግጭት እንዲባባስ ለየትኛውም አመራር ይሁን መለከት እየነፉ፣ ለየትኛውም ግለሰብ ይሁን ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሳብ እንፈልጋለን፡፡ ይሄ ባልሆነበት ግን መንግስት በየአቅጣጫው ለእነዚህ ችግሮች መንስኤ የሆኑትን እያጠና፣ በየደረጃው አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይቀጥላል” ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ 

መንግስት ይህን መሰሉን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ማዘወተሩን የተመለከቱ መንግስት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለመቆጣጠር እየተንደረደረ እንደሆነ ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡ እነዚህን የመገናኛ አውታሮች ለመቆጣጠር አዋጅ ማርቀቁ ሲነገር ተደምጧል፡፡ በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ልማት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ታምራት ደጀኔ ግን መንግስት የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ብቻ ነጥሎ ህግ እያዘጋጀ እንዳልሆነ ያስተባብላሉ፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል እና እንዴት መመራት እንዳለባቸው የሚጠቁም ክፍል በመስሪያ ቤታቸው እየተዘጋጀ ባለው የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ፖሊሲ ላይ መካተቱን ያስረዳሉ፡፡

Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

“ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ለበጎ ነገር የሚጠቀሙበት በርካታ ኩባንያዎች ያሉ ቢሆንም ለማሻሻጫ፣ መረጃ ለመስጠት፣ ለመለዋወጥ በርካታ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም በዚያው ልክ ደግሞ ያው ሽብር የሚስፋፋበት፣ የዚህ የጥላቻ ንግግር የሚባለው ነገር አንዱን በሌላው ላይ የማነሳሳት፣ ሀሰተኛ [መረጃዎችን] የማሰራጨት ሁኔታዎች ስላሉ፣ ይሄ ጉዳይ በተወሰኑ አካባቢዎችመ ትርምስ እና ግጭት እየፈጠረ ስለሆነ ይሄ መስተካከል አለበት ማለት ነው፡፡ በዚያ ደረጃ ማህበራዊ ሚዲያውን እንዴት የበለጠ እንጠቀምበታለን በሚል ደረጃ የሚሰራ ይሆናል፡፡”

በዝግጅት ላይ ያለው የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ፖሊሲ እንደተጠናቀቀ ለተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ የሚናገሩት አቶ ታምራት መቼ የሚለውን ግን አሁን መመለስ እንደማይችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ዳግም አፈወርቅ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ “ያልተጣራ እና ያልተዛባ የሰዎችን አስተያየት ለማግኘት” ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ብቸኛ አማራጮች ናቸው ይላሉ፡፡ “ተጠቃሚው ገደብ ሳይጣልበት አስተያየት የሚያቀርብበት መድረክ በመሆኑም ለመቆጣጠር እየተደረገ ነው የሚባለው ጥረት ትልቅ ተጽእኖ ይፈጥራል” ባይ ናቸው፡፡

“የመንግስት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ሰዎችም ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ አደጋ ማድረስ የሚያስችል አቅም አለው ስለዚህ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ብለው ያምናሉ፡፡ ግን በእኔ አረዳድ እና አመለካከት ራሱ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑን የመጥፎነት አደጋ ወይም አቅም የምታጠፋው ክፍት አድርገኸው ለክርክር በመተው ነው፡፡ ሰዎች እዚያው አስተያየቶቻቸውን ሲቀያይሩ እዚያው የምትገለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ቁጥጥር ሊደረግበት ከታሰበም ትልቅ አደጋ ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል መምህሩ፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ