1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰለባዎቹ “ለሰላማዊ ትግል ህይወታቸውን ያጡ” ተብለዋል

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2009

የዛሬ 12 ዓመት ሰኔ አንድ የተገደሉ ሰዎችን ለመዘከር የተዘጋጀው የመታሰቢያ ስነ ስርዓት የተካሄደው አዲስ አበባ በሚገኘው የመኢአድ ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ሰዎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ ጥቁር ልብስ አድርገው ነበር፡፡

https://p.dw.com/p/2eMKe
Symbolbild Kerze Flamme
ምስል Colourbox

Ber. Addis Ababa (AEUP & Blue Party held remeberance day) - MP3-Stereo

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ የ1997ቱ ምርጫ ውጤት በቀሰቀሰው ግጭት የዛሬ 12 ዓመት ሰኔ አንድ የተገደሉ ሰዎችን ለመዘከር ዛሬ የሀዘን ስነ-ስርዓት አካሄደዋል፡፡ ስነ ስርዓቱ የተካሄደው አዲስ አበባ በሚገኘው የመኢአድ ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ለዶይቸ ቨለ ሲናገሩ “በ1997 ዓ.ም ሰኔ አንድ ቀን በኢህአዴግ ታጣቂዎች ሰለባ የሆኑ ንጹሃን ዜጎቻችን የመሰዋትዕነት ቀን ለማስታወስ ነው እዚህ የተሰበሰብነው” ብለዋል፡፡ ዶ/ር በዛብህ የ1997ቱ ምርጫ ውጤት በቀሰቀሰው ግጭት የተገደሉ ሰዎችን “ለሰላማዊ ትግል ሲሉ ህይወታቸውን ያጡ” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡ አብዛኞቹም ወጣቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

“እነዚህን ሰዎች ለምንድነው በየጊዜው የምታስታውሱት የሚል ጥያቄ ቢቀርብ” ምላሽ እንዳላቸው የመኢአድ ፕሬዝዳንት ይገልጻሉ፡፡  “እነዚህ ሰዎች በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ትግል እንዲዳብር ህይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁን እኛ እዚህ ቆመን ውይይት የምናደርገው እነርሱ ታግለው የዲሞክራሲን ጭላንጭል እንዲከፈት ለማድረግ ነው” ብለዋል፡፡ ዝግጅቱን የተከታተለው የአዲስ አበባው ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ በስነ-ስርዓቱ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ሰዎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ ጥቁር ልብስ አድርገው እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ሙሉ ዘገባውን የድምጽ መስፈንጠሪያውን ተጭነው ያድምጡ፡፡

 

ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ