1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መካከለኛዉ ምሥራቅ እና የአሜሪካ መርሕ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2010

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉሳኔ ቁጥር 181 (II) ተብሎ በሚጠራዉ ዉሳኔ መሠረት ፍልስጤም ይባል የበረዉ ግዛት ለአይሁድ እና ለአረብ እሁለት ይገመሳል።ሁለቱ ወገኞች ሁለት መንግሥት ያቆማሉ።ጥንታዊቱ ከተማ እየሩሳሌም ግን በዓለም አቀፍ ልዩ አስተዳደር ትተዳደራለች።

https://p.dw.com/p/2pAYi
Jerusalem Entscheidung Proteste weltweit
ምስል Reuters/O. Orsal

መካከለኛዉ ምሥራቅ እና የአሜሪካ መርሕ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ወሰኑ።ሮብ።«እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንኗን በይፋ እዉቅና የምሰጥበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ወስኛለሁ።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር አፀደቁ።ትናንት።«ፓሪስ የፈረንሳይ ርዕሠ-ከተማ ነዉ።እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ ነዉ።»

ከኒዮርክ እስከ ብራስልስ፤ ከአንካራ እስከ ጃካርታ የዓለም መሪዎች፤ ፖለቲከኛ እና ዲፕሎማቶች ተቃወሙ።የብዙ ሐገራት ሕዝብ በየአደባባዩ ተንጫጫ፤ ፍልስጤም ለዓመታት እንደኖረበት ይገደል፤ ይቆስል፤ በጢስ ጠለስ-ይጠበስ-ይታፈን ያዘ። ስድስተኛ ቀኑ። ወይም ሰባኛ ዓመቱ።

 

ዩናይትድ ስቴትስ የመሠረተችዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከዚያ ዘመን ድረስ እጅግ ያወዛጋበዉን ረቂቅ ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን እስከ ብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ክሌመንት አትሌ የነበሩ የሁለቱ ሐገራት ፖለቲከኞች እና ዲፕሎማቶች ሐሳቡን አንቀበልም ያሉትን አስፈራርተዉም፤ አባብለዉም፤ ተስፋ ሰጥተዉም አፀደቁ።ሕዳርም አበቃ።1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉሳኔ ቁጥር 181 (II) ተብሎ በሚጠራዉ ዉሳኔ መሠረት ፍልስጤም ይባል የበረዉ ግዛት ለአይሁድ እና ለአረብ እሁለት ይገመሳል።ሁለቱ ወገኞች ሁለት መንግሥት ያቆማሉ።ጥንታዊቱ ከተማ እየሩሳሌም ግን በዓለም አቀፍ ልዩ አስተዳደር ትተዳደራለች።

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆርጅ ማርሻል እና ሌሎች ዲፕሎማቶች በዉሳኔዉ መፅደቅ ተደሰቱ እንጂ በርግጥ አልተከፉም።ዉሳኔዉ በፀደቀ በመንፈቁ አይሁድ «የእስራኤል አይሁድ መንግስት» ያሉትን መንግስት ሲያቁሙ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ተሽቀዳድመዉ እዉቅና ለመስጠት ማሰባቸዉ ግን ለነ ማርሻል ፤አሳሳቢ፤ አስጊም ነበር።

Israel | Palästina Jerusalem - Felsendom
ምስል picture alliance/dpa/R.Holschneider

                               

«በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ነን።ሥለዚሕ በዓለም አቀፍ ችግሮች ላይ በስሜት ተመርተን መወሰን የለብንም።»

የማርሻል ሥጋት ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎቹ ቀድማ ለእስራኤል መንግስት እዉቅና ከሰጠች መካከለኛዉ ምሥራቅ ከለየለት ጦርነት ይሞጀራል የሚል ነበር።ጦርነቱ እራስዋ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያላገገመዉን ዓለም ይጎዳል ነበር።

ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ቱርማን ግን ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉም ሆነ ለሌሎች ባለሙያዎቻቸዉ ምክር፤ ዝክር ማስጠንቀቂያ ደንታ አልነበራቸዉም።የጃፓንን ከተሞች በአዉቶሚክ ቦምብ ለማንጨርጨር ያላመነቱት የቀድሞዉ ወታደር እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ ወታደርነታቸዉ፤ በሰከነ ልቡናቸዉ ሳይሆን በስሜታቸዉ ተመርተዉ ወሰኑ።

                                 

«ባለሙያ ተብዬዎች ሁሉ፤ ከተደረገ መላዉ የቅርብ ምሥራቅ ከጦርነት ይዘፈቃል።ጦርነቱ ዩናይትድ ስቴትስንም ይነካል ብለዉ ነግረዉኛል።ሒትለር አይሁድን በግራም በቀኝም ይገድል ነበር።አይቼዋለሁ።እንዲያዉም ይሕ ቀን እንዲመጣ ሳልም ነበር።አይሁድ የሚኖሩበት ሥፍራ ሊያገኙ ይገባል።»

ትሩማን ወሰኑ።ለእስራኤል መንግስትነት ግንቦት 14፤ 1948 በድብቅ፤ ጥቂት ቆይተዉ በይፋ እዉቅና ሰጡ።ማርሻል የፈሩት፤ የቱርማን አማካሪዎች ያስጠነቀቁት ጦርነት አልቀረም።1948 ጦርነት፤ 1956 ጦርነት፤ 1967 ጦርነት።1973 ጦርነት።ዛሬም ቀጥሏል።

በሁሉም ጦርነቶች ዩናይትድ ስቴትስ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እስራኤልን ደግፋ ተዋግታለች።የ1967ቱ ጠንከር ያለ፤ በዩናይትድ ስቴትስ የተመሠረተዉ፤ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራዉ፤ በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፈዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዉሳኔን የቀለበሰ ነበር።

Libanon Proteste gegen US-Entscheidung zu Jerusalem
ምስል picture-alliance/AA/M. A. Akman

በዚያ ዘመን የእስራኤል የስለላ ድርጅት የሞሳድ ኃላፊ የነበሩት ሚር አሚት ኋላ እንደተረኩት ሰኔ መጀመሪያ 1967 እራሳቸዉን ደብቀዉ በሐሰት ፓስፖርት ወደ ዋሽግተን በረሩ።ጊዜ የለም።በቀጥታ የአሜሪካዉን መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ማክናማራን አገኙ።

«ዉጊያ መግጠም አለብን አልኳቸዉ» አሉ አሚት በ2002 ላንድ ወዳጃቸዉ።

 «ማክናማራ ሁለት ጥያቄዎችን ብቻ ነበር የጠየቁኝ» አከሉ።

«ስንት ቀን ይፈጃል» ጠየቁ የአሜሪካዉ ሚንስትር።

«አንድ ሳምንት» መለሱ የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ኃላፊ።

«ምን ያሕል ሰዉ ይጎዳል።» ሁለተኛ ጥያቄ።

በነፃነቱ ጦርነት ከደረሰዉ ያነሰ ነዉ።በ1948 የተደረገዉን ጦርነት እስራኤሎች የነፃነት ጦርነት ነዉ የሚሉት።በዚያ ጦርነት ስድስት ሺሕ ሰዉ መገደሉን የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ኃላፊ ለአሜሪካዉ መከላከያ ሚንስትር አስታወሷቸዉ።«በግልፅ ተረድቼሐለሁ» መለሱ ማክናማራ።

ሰኔ 5፤ በዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ፤ ዲፕሎማሲ፤ የጦር መሳሪያ እና የጦር አማካሪዎች የምትደገፈዉ እስራኤል የግብፅን፤ የዮርዳኖስን፤ የሶሪያን፤ ወታደራዊ ይዞታዎች በምርጥ ጄቶች ታወድም ገባች።የሞሳድ ኃላፊ እንዳሉት በስደስተኛ ቀኑ ጦርነቱ አበቃ።ድል አድራጊዋ እስራኤል በርካታ የአረቦችን ግዛት ተቆጣጠረች።አንዷ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዋሽግተኖች ግፊት በዓለም አቀፍ አስተዳዳሪዎች እንድትተዳደር የወሰነላት ቅድስት ከተማ ናት።

ከክርስቶት ልደት በፊት ከ586 ጀምሮ አሲሪያዎች፤ ባቢሎኖች፤ግሪኮች፤ሮሞች፤አረቦች፤ ፋርሶች፤ቱርኮች፤አዉሮጶች እያፈረሱ የገነቧት፤ እየገነቡ ያወደሟት ቅድስት ከተማ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በኋላ አይሁድ እጅ ገባች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔም ተጣሰ።ዘንድሮ አርባ ዓመቱ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቀደም የአርባ ዓመቱን እዉነት ነዉ የተቀበልኩት አሉ።

«በስተመጨረሻዉ ዛሬ እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ የመሆንዋን እዉነት ተቀበልን።ይሕ እዉነቱን ከመቀበል ያነሰ ወይም የበዛ አይደለም።መደረግ የሚገባዉ ትክክለኛዉ ነገርም ነዉ።ከዚሕ በፊት መደረግ የነበረበት ነዉ።»

 

ለትራምፕ እዉነቱ እየሩሳሌምን የእስራኤል ከተቆጣጠረቻት መቆየትዋ ነዉ። ሐሰት ሲደጋገም እዉነት ይሆናል እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር እስራኤል በአሜሪካኖች ዙሪያ መለስ ድጋፍ እየሩሳሌምን ስትቆጣጠር በአሜሪካኖች ግፊት የፀደቀዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ ጥሳ የመሆኑ እዉነት ባልተካደ ነበር።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉ ዓለም እራሱ ያፀደቀዉን ዉሳኔ ማስከበር አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉም እዉነት ነዉ።

 

ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ለቤንያሚን ኔታንያሁ ደግሞ እዉነቱ ከትራምፕም፤ ከትክክለኛዉ ሐቅም የተለየ ነዉ።«ታሪካችንን አክብሩ»ነዉ ያሉት በቀደም።

                                   

«ለሰወስት ሺሕ ዓመታት የእስራኤል ርዕሠ ከተማ ነበረች።ለሰባ ዓመት የአይሁድ መንግስት ርዕሰ ከተማም ናት።ታሪካችሁንና ምርጫችሁን እናከብራለን።እንደወዳጅ እናንተም የኛን እንደምታከብሩ እናዉቃለን።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምን ዉሳኔ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ፤ እስከ አዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግግኙነት ኃላፊ ፌደሪካ ሞግሔሪኒ ያሉ የዓለም ዲፕሎማቶች ተቃዉመዉታል።ከሬሴፕ ጠይብ ኤርዶሐን እስከ ኤማኑኤል ማክሮን፤ ከቭላድሚር ፑቲን እስከ ሺቺፒንግ ያሉ የዓለም መሪዎች አዉግዘዉታል።ቅሬታ፤ ተቃዉሞ፤ ዉግዘታቸዉ ከፖለቲካ- ዲፕሎማሲያዊ ፍጆታ፤ አለያም የየሕዝባቸዉን ስሜት ከማቀዝቀዝ ማለፉ ግን ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

USA Trump eröffnet Bürgerrechtsmuseum in Jackson
ምስል Reuters/K. Lamarque

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆን ሮበርት ቦልተን በ1994 ባደረጉት ንግግር «የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የለም» ብለዉ ነበር።ያለዉ አልፎ አልፎ በዓለም ላይ በቀረችዉ ብቸኛ ኃያል ሐገር በዩናይትድ ስቴትስ ሊመራ የሚችል ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ነዉ።» ሰዉዬዉ በዚሕ አላበቁም።ኒዮርክ የሚገኘዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፅሕፈት ቤት 38 ፎቆች አሉት።አስሩ ፎቆች ዛሬ ቢደረሰመሱ ምንም ልዩነት አያመጣም።» እያሉ ቀጠሉ።

ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የመሯቸዉ ቦልተንና ብጤዎቻቸዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሕግ፤የዓለም ሕዝብን ተቃዉሞ ጥሰዉ ኢራቅን ሲወሩ ግዙፉ ድርጅት አለመኖሩን አስመስክረዋል።የተቀሩት የድርጅቱ አባል ሐገራት ምንም አለማድረጋቸዉ ቦልተን እንዳሉት ዓለም የአሜሪካ ካሜሪካም  የዋይት ሐዉስ መሆንዋን ጠቋሚ ነዉ።

ትራምፕም ዓለም የዋይት ሐዉስ መሆንዋን ዳግም ከማረጋገጥ ያለፈ ያሉ እና ያደረጉት የለም።እርግጥ ነዉ የአልጀዚራዉ የፖለቲካ ተንታኝ ማርዋን ቢሻራ እንደሚሉት የትራምፕ ዉሳኔ ከጦርነት አዋጅ የሚቆጠር ይሆን ይሆናል።

                           

«ይሕ በፍልስጤም ሕዝብ እና በመብታቸዉ ላይ፤ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፤ ለዓለም አቀፉ ሕግ ባለዉ ተገዢነት ላይ የታወጀ ጦርነት ነዉ።ከአዉሮጳ እና ከአረብ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶችም የምንሰማዉ ይሕንኑ ነዉ።ባጠቃላይ ሲታይ እዉነቱ፤ ፍልስጤም በኃይል እንደተያዘች ትቀጥላለች።ምስራቃዊ እየሩሳሌምም በኃይል እንደተያዘች ትቀጥላለች።ግን የደንበኞቻቸዉን ቃላት፤ አሰልቺ አገላለፆች፤ አሳሳች መረጃዎች እና ታሪክን  የሚያዛቡ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አሉ።»

Belgien Brüssel Netanjahu trifft Mogherini
ምስል Reuters/F. Lenoir

 

ታዛቢዎች እንደሚሉት የትራምፕን ዉሳኔ እንቃወማለን የሚሉ መንግስታት እና ድርጅቶች እንገዛለታለን የሚሉትን ወይም ቃዛፊን ለማስገደል፤ ሙጋቤን፤በሽርና አሰድን፤ ወይም ሌሎች ደካሞችን ለማስወገድ  የሚመዝቱን ዓለም አቀፍ ሕግ ካላስከበሩ ተቃዉሞ ዉግዘታቸዉ ጥቅምን ከማስከበር ወይም ከሚጮኸዉ ሕዝብ ጋር ከመጮሕ ያለፈ የሚተክረዉ የለም።

ብሔረተኛ የሚባሉት የአረብ መንግስታት ተራ በተራ ፈርሰዋል።የተቀሩት ከየመን እስከ ሶሪያ እርስ በርስ እየተዋጉ ነዉ።ከሳዑዲ አረቢያ እስከ ቀጠር እየተሻኮቱ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ቢሻራ እንደሚሉት ጦርነት መጫሩ  ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ፍልስጤም ግን አንድ-አራት እያለ መገደል፤ መታሰር፤ መጋዙ ይቀጥላል። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ