1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፈንቀለ መንግሥት በማሊ

ሐሙስ፣ መጋቢት 13 2004

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ማሊ ዓማፅያን የጦር ኃይል መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬን ከሥልጣን ማውረዳቸውን አስታወቁ። በዚሁ ወቅትም በርካታ ሚንስትሮች ማሰራቸውና የሀገሪቱን ቴሌቪዥን ድርጅትም መቆጣጠራቸው ተሰምቶዋል።

https://p.dw.com/p/14PKM
ምስል Reuters

የጦር ኃይሉ ይህን ርምጃ የወሰደው ኃላፊነቱን በሚገባ ያልተወጣው የፕሬዚደንት ቱሬ መንግሥት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ከፊል የተነሳውን የቱዋሬግ ዓመፅ ማብቃት ባለመቻሉ መሆኑን ዴሞክራሲንና መንግሥትን ለመመሥረት ዓማፅያኑ ያቋቋሙት የጦር ኃይል ኮሚቴ ዛሬ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ገልጾዋል።

ፕሬዚደንት ቱሬ የጦር ኃይሉን መፈንቅለ መንግሥት ማምለጣቸውና በአንድ የጦር ሠፈር ውስጥ በታማኝ ዘቦቻቸው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን አንዳንድ ምንጮች እየጠቆሙ ነወ። ዴሞክራሲንና መንግሥትን ለመመሥረት ዓማፅያኑ ያቋቋሙት የጦር ኃይል ኮሚቴ ቃል አቀባይ መቶ አለቃ አማዱ ኮናሬ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ባደረጉት ንግግር፡ የሀገሪቱ አንድነትና የግዛት ሉዓላዊነት እንደገና እስኪረጋገጥ ድረስ ሕገ መንግሥቱ መታገዱን አስታውቀዋል።
« የሬፓብሊኳ ጦር ኃይል የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት በተጣለበት ተልዕኮው መሠረት፡ ብቃት የጎደለውን መንግሥት እና ፕሬዚደንቱን ከሥልጣን በማውረድ ኃላፊነቱን ለመረከብ ወስኖዋል። በዚህም የተነሳ እአአ ከመጋቢት ሀያ ሁለት፡ 2012 ዓም ጀምሮ ቀጣዮቹን ርምጃዎች ወስዶዋል። አዲስ ደንብ እስኪወጣ ድረስ ሕገ መንግሥቱ ታግዶዋል፤ የመንግሥቱ ተቋማትም ፈርሰዋል። በሀገሪቱ ካሉ ኃይላት ጋ ምክክር ከተደረገም በኋላ አንድ ሁሉን የሚያጠቃልል የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይቋቋማል። የጦር ኃይሉ ብሔራዊው ኮሚቴ ዓላማ ሥልጣኑን ራሱ ለመያዝ ሳይሆን፡ በሀገሪቱ የግዛት ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነው ስጋት እንደተወገደ ሥልጣኑን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሚመረጥ ፕሬዚደንት ማስረከብ ነው። »
የማሊ መንግሥት የቱዋሬግ ዓማፅያን በሰሜን የሀገሪቱ ከፊል ባለው በረሀማ አካባቢ ከመንግሥቱ ጦር ኃይላት ጋ የሚያካሂዱትን ዓመፅ ለመደምሰስ የሚያስችለው በቂ የጦር መሣሪያ ለጦር ኃይሉ አላቀረበም በሚል ነው ዓማፅያኑ ወታደሮች ወቀሳ ያሰሙት። በዚሁ አካባቢ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል ካለፈው ከጥር መጀመሪያ አንስቶ የተኩስ ልውውጥ እና የአየር ጥቃት ቀጥሏል ። በተለይ ውጊያው የቀድሞ የሊቢያን መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊን ይደግፉ የነበሩ ከባድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ተዋጊዎች ወደ ማሊ ከተመለሱ ወዲህ ተባብሶ፡ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ያካባቢው ነዋሪዎችን ለሽሽት ዳርጓል። ይህም በማሊ መንግሥት ላይ ብርቱ ወቀሳ እንዲሰነዘር ምክንያት ሆኖዋል።
የፕሬዚደንት ቱሬ ፓርቲ አባል የሆኑት ያያ ሳንጋሬ የቱዋሬግ ዓመፅን በተመለከተ የተሰራ ስህተት ሊኖር እንደሚችል ቢገልጹም፡ የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥቱ ማካሄዱን በጥብቅ ነቅፈዋል።
« እንደ አንድ ዴሞክራት መፈንቅለ መንግሥቱን አወግዛለሁ። ምክንያቱም ዛሬ፡ በተለይ ቀጣዩ ምርጫ ሊደረግ አርባ ቀኖች በቀረበት ባሁኑ ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ በማሊ ሁኔታዎችን አያሻሽልም። እርግጥ፡ መስተዳድሩ ለውዝግቡ ትኩረት ሰጥቶ ተገቢውን መልስ አልሰጠ ይሆናል። ግን፡ ይህ ወጣቶቹን የጦር መኮንኖች ገና ዴሞክራሲያዊዊውን ሂደት በመገንባት ላይ በምትገኝ ሀገር ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያካሂዱ ምክንያት መሆን አልነበረበትም። »
ትናንት ሌሊት ከባድ ተኩስ ከተካሄደበት የመፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሁኔታዎች ከቁጥጥር እንዳይወጡ ለመቆጣጠር የጦር ኃይሉ ብሔራዊ ኮሚቴ የሰዓት እላፊ አውጆ፡ ዜጎች እንዲረጋጉ ሻምበል አማዱ ሳያ ሀኖጎ አሳስበዋል።
« የማሊ ሕዝብ ተረጋግቶ እንዲጠብቅ እጠይቃለሁ። ሁከቱን የሚያባብስ ርምጃን፡ ዝርፊያን ሁሉ እናወግዛለን። ሁሉም ዜጋ የሀገሩን ፀጥታ እንዲያስከብር እንጠይቃለን። የሀገሪቱን እና የሕዝቧን ፀጥታ ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ርምጃ ሁሉ እንወስዳለን። »
የአፍሪቃ ህብረት፡ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ በምህጻሩ ኤኮዋስ እና የሙሥሊም ትብብር ድርጅትም ርምጃውን በማውገዝ ሀገሪቱ ወደዴሞክራሲያዊው ሂደት እንድትመለስ ጠይቀዋል። የተመድ ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙን ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።
ያሁኑ ድርጊት ባካባቢው መረጋገት ከሰፈነባቸው ጥቂት ምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ አንድዋ በሆነችው ማሊ መጥፎ እውነታ ከመፍጠሩ ጎነ ለዴሞክራሲያዊ ሂደት ክሽፈት መሆኑን የፖለቲካ ታዛቢዎች አስረድተዋል ። እአአ በ1991 ሥልጣን በመፈንቅለ መንግሥት ቢይዙም ሥልጣን ከሲቭል በማስረከባቸው ተሞግሰው ነበር። በ 2002 እና 2007 በዴሞክራሲያዊ ዘዴ የተመረጡት ቱሬ ሁለት የሥልጣን ዘመናቸውን አብቅተው ከአንድ ወር በኋላ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ነበር የተገለጸው።

አርያም ተክሌ

Renegade Malian soldiers appear on television at the ORTM television studio in Bamako in this March 22, 2012 still image taken from video. Renegade Malian soldiers went on state television on Thursday to declare they had seized power in protest at the government's failure to quell a nomad-led rebellion in the north. REUTERS/Mali TV via Reuters TV (MALI - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. MALI OUT. NO COMMERCIAL OR EDITORIAL SALES IN MALI
ምስል Reuters
Civilians cheer as mutinous soldiers drive past, in front of a backdrop of burning tires, in Bamako, Mali Wednesday March 21, 2012. Gunshots could still be heard in the Malian capital late Wednesday, hours after angry troops started a mutiny at a military base near the presidential palace. Soldiers stormed the offices of the state broadcaster, yanking both TV and radio off the air.(Foto:Harouna Traore/AP/dapd)
ምስል AP
Mali President Amadou Toumani Toure inspects a Guard of Honor during a ceremonial reception at the Presidential Palace in New Delhi, India, Wednesday, Jan. 11, 2012. (AP Photo/Pankaj Nangia)
ምስል AP

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ