1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፍትሄ የታጣለት የስደተኞች እልቂት

ረቡዕ፣ የካቲት 11 2007

በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ በጉዞ ላይ ህይወታቸው የሚያልፍ ስደተኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት በመጠኑ ቀንሶ ነበር ።

https://p.dw.com/p/1EdPi
Italien Rettungsschiffe Flüchtlinge
ምስል picture alliance/AP Photo

ሆኖም ባለፈው ሳምንት ቁጥራቸው ከ300 በላይ የተገመተ ስደተኞች የሜዲቴራንያን ባህር ሲሳይ ሆነዋል ። የቀጠለው የባህር ስደተኞች እልቂትና መላው የዛሬው ትኩረት ነው ።

ከሰሜን አፍሪቃ ተነስተው በሜዲቴራንያን ባህር አድርገው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር አሁንም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ።ሙከራቸው ሰምሮ በህይወት የአውሮፓን ምድር የሚረግጡት ግን ሁሉም አይደሉም ። አብዛኛዎቹ በሚሳፈሩባቸው ጀልባዎች አቅም ማነስ በመጥፎ የአየር ንብረትና በሌሎችም ሰው ሰራሽ ችግሮች መንገድ ላይ ወሐ በልቷቸው ይቀራሉ ።እርግጥ ነው ከአንድ ዓመት ከ4 ወር በፊት ኤርትራውያን የሚያመዝኑባቸው ከ366 በላይ አፍሪቃውያን ስደተኞች በኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ የሚደርስላቸው አጥተው ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ኢጣልያ ያሰማራችው የባህር ጠባቂ በርካታ ስደተኞችን በመታደጉ ብዙ ስደተኞችን ማትረፍ ተችሎ ነበር ። ማሬ ኖስትሩም የተባለው ይኽው የኢጣልያ የፍለጋና መድን ተልዕኮ ከአንድ ዓመት በኋላ ሥራውን በማቆሙ ግን የቀድሞው ችግር ተመልሷል።ባለፈው ሳምንት በሜዴትራንያን ባህር ላይ ያለቁት ስደተኞች የዚህ አብነት ናቸው ።

«እሁድ ነበር ከሊቢያ የተነሱት ።ያለ ምግብና ውሐ 30 የፈረስ ጉልበት ባላት ጀልባ ላይ ሆነው ቢያንስ አንድ ቀን ሙሉ ሀይለኛ ማዕበል በሚያናውፀው ባህር ላይ ነበሩ ። ወዲያውኑ በውሐ በተሞሉ ሁለት ጀልባዎች ላይ እንደነበሩ ነግረውናል ። ከመካከላቸው 203 ሰዎች ሞተዋል ።በእድሜ ትንሹ የ12 ዓመት ልጅ ነበር ።»

Verstorbene Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል Reuters/Vista via Reuters TV

በኢጣልያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሻርሎታ ሳሚ በህይወት ከተረፉት ስደተኞች የሰሙትን ነበር የተናገሩት ። ከማሊ ና ከሴኔጋል ከመጡት ከነዚሁ ስደተኞች መካከል 9ኙ የተሳፈሩባትን የጎማ ጀልባ የሙጥኝ ብለው በህይወት ለመትረፍ በቅተዋል ። በዚያው ሳምንት በ4 ትናንሽ ጀልባዎች ከሊቢያ ተነስተው ወደ ኢጣልያ ይጓዙ ከነበሩት አፍሪቃውያን ስደተኞች ወደ 300 የሚሆኑት ደብዛቸው ጠፍቷል ። እነዚህ የደረሱበት ያልታወቀ ስደተኞች ሲሆኑ በዚያው ሰሞን ከሊቢያ ወደ ኢጣልያ ሲጓዙ ከነበሩ ስደተኞች 27 ቱ ቅዝቃዜውን መቋቋም አቅቷቸው ህይወታቸው አልፏል ።ሟቾቹ በአነስተኛና ጀልባ ከሊቢያ ከተነሱት 105 ስደተኞች መካከል ነበሩ ። የድረሱልኝ ጥሪ ቀርቦለት የታደጋቸው የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ቃል አቀባይ ፊሊፖ ማሬኒ እንዳሉት ኃይለኛውን ማዕበል መቋቋሙ የባህር በር ጠባቂው ቡድንም ፈተና ነበር ።

« ከሊቢያ የባህር ዳርቻ በጥቂት ማይሎች ርቀት ላይ ለሚገኙት 105 ስደተኞች ርዳታ ለመስጠት ከላምፔዱዛ የተንቀሳቀሱት ጀልባዎች አዳጋቹን ሁኔታ፣ ብሎም ስምንት ፣ ዘጠኝ ሜትር ከፍታ የነበረው ማዕበል እና ጠንካራ ንፋስ መቋቋም ነበረባቸው ። የርዳታ ሰጪው ቡድን አባላት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ስደተኞቹን ሁሉ ወደነርሱ ጀልባ አሸጋግሮ ነበር። »

የኢጣልያ የባህር ጠባቂዎች 160 ኪሎሜትር ተጉዘው የጀልባ ስደተኞቹ ጋ ሲደርሱ ከመካከላቸው 7ቱ ኃይለኛውን ቅዝቃዜ መቋቋም አቅቷቸው ህይወታቸው አልፎ ነበር ።እነዚህኑ ስደተኞች የታደገው የኢጣልያ የባህር ጠባቂ ወደ ኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ ሲወስዳቸው ረዥም ጊዜ በመፍጀቱ 20ው መንገድ ላይ በቅዝቃዜ ሞተዋል ። በወቅቱ ስደተኞችን ለመታደግ አነስተኛ ጀልባ ሳይሆን ተለቅ ያለ መርከብ ተልኮ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ የ 20ዎቹን ህይወት ማትረፍ ይቻል እንደነበር ነው የላምፔዱዛ ከንቲባ ግዩሲ ኒኮሊኒን የተናገሩት ።

Italien Flüchtlingsdrama vor Lampedusa
ምስል picture alliance/ROPI

«አውሮፓ ብቻችንን የተወን ያህል ነው የሚሰማን ። በሜዲቴራንያን ባህር ስደተኖችን የመታደጉን ተግባር ለማጠናከር መንግሥት ለአዲስ ሰብዓዊ ተልዕኮ መነሳት አለበት ።ለነዚህ በህይወት ተረፈው በኋላ በቅዝቃዜ ለሞቱት ሰዎች ማሬ ኖስትሩም ደርሶላቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ በህይወት በተገኙ ነበር ማሬ ኖስትሮም ሁሌም ከላምፔዱዛ በስተደቡብ ራቅ ብሎ ይሰማራ ነበር ።

ለዚህ አሳዛኝ አደጋ ምክንያት የተደረገው ማሬ ኖስትሩም የተባለው የኢጣልያ የፍለጋና የመድን ተልዕኮ ሥራውን ማቋረጡ ነው ። ኢጣልያ ወጪ በዛብኝ ስትል ባለፈው ጥቅምት ማሬ ኖስትሩም ሥራውን እንዲያቆም አድርጋለች ። ኢጣልያ እንደምትለው ማሬ ኖስትሮም በአንድ ዓመት ብቻ 114 ሚሊዮን ዩሮ ፈጅቷል ትላለች ። አሁን በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ቅኝት የሚያደርገው ፍሮንቴክስ በተባለው የአውሮፓ ህብረት ድንበር ጠባቂ ድርጅት ስር ያለው ትሪቶን ነው ።የትሪቶን ቁጥጥር ደግሞ በህብረቱ አባል ሃገራት ድንበር ላይ ብቻ የተገደበ ነው ። ትሪቶን በኢጣልያዋ ሲሲሊና በማልታ ባሰማራቸው ሁለት ትላልቅ ጀልባዎች ብቻ ነው ጥበቃውን የሚያካሂደው ።በርካታ ስደተኞች የሚጎርፉባት የላምፔዱዛ ከተማ ከንቲባ ግዩሲ ኒኮሊኒ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ አደጋ ላይ የሚወድቁ የባህር ላይ ስደተኞችን መታደጉ በኢጣልያ ላይ ብቻ ላይ የተጣለ ሆኗል ።

Verstorbene Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Buccarello

«ከማሬ ኖስትሩም በኋላ ሌላ ተልዕኮ የለም ። ትሪቶን ሰብዓዊ ተልዕኮ አይደለም ።ትሪንቶን ፍሮንቴክስ ነው ። ተግባሩም ድንበር ጥበቃ ነው ። እናም ስደተኞቹን የታደገው ፍሮንቴክስ ወይም ትሪንቶን አይደለም ። ጭንቅ ላይ የነበሩት ስደተኞች ጥሪ በቀጥታ የደረሰው ለኛ የባህር ጠባቂ ነው ። »

አሠራሩ በዚህ ከቀጠለ ወደፊት የሜዴትራንያን ባህር ሲሳይ የሚሆኑት ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ እንደማይቀር ከወዲሁ ማሳሰቢያ እየቀረበ ነው ። አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች ስደተኞች ብዙም በማይጠበቁበት በአሁኑ የአውሮፓ ክረምት ይህን ያህል አደጋ ከደረሰ የዓየር ንብረቱ ሲሻሻል ደግሞ የከፋ ችግር መከተሉ ስለማይቀር ከወዲሁ ይታሰብብበት እያሉ ነው ። የUNHCR ዋ ሻርሎታ ሳሚ ይህን ማሳሰቢያ ከሚቀርቡት አንዷ ናቸው ።

«ሁኔታዎችን ካልተሻሻሉ አቅማችንን ካላሳደግን አዳዲስ አሳዛኝ ሁኔታዎች መከሰታቸው አይቀርም ። ልብ በሉ አሁን ክረምት ነው ። በበጋ ግን ስደተኞችን የጫኑ 15 ፣ 20 ጀልባዎች ናቸው በአንዴ የሚመጡት ።ይህን ነው የኢጣልያ ባህር ኃይል በጎርጎሮሳዊው 2014 የተወጣው ።»

Symbolbild Flüchtlinge Mittelmeer Bootsflüchtlinge Migranten
ምስል picture-alliance/dpa

በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም የኢጣልያ ባህር ኃይል በአነስተኛ ጀልባ ከሰሜን አፍሪቃ ወደ ኢጣልያ ይጓዙ የነበሩ ከ170ሺህ በላይ ስደተኞች ታድጓል ። እነዚህ ቀንቷቸው ኢጣልያ ቢደርሱም በዓመቱ 3200 ስደተኞች በጉዞ ላይ ህይወታቸው አልፏል ። ይህ ማብቂያ ያጣው የባህር ላይ አደጋ እንዲገታ የአውሮፓ ህብረት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግለት ከሚያሳስቡት አንዷ ዶክተር አልጋነሽ ፍስሃ ናቸው ። ስደተኞችን የሚረዳው ጋንዲ የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ሃላፊ ዶክተር አልጋነሽ አዲስ አሠራር ይቀየስ ነው የሚሉት ።

« የአውሮፓ ማህበረሰብ አቋሙን እንደገና መፈተሽ ይኖርባታል ። ስደተኞችን መታደግ ያልቻሉትን ማሬ ኖስትሮምን ወይም ፍሮንቴክስን ትተው ሌላ አዲስ አሠራር መቀየስ አለባቸው ።»

በርሳቸው አስተያየት ማሬ ኖስትሮም እንደገና ሥራ መጀመሩ ችግሩን በዘላቂነት አያስወግድም ። ድርጅታቸው ሊቢያ ውስጥ ስደተኞችን የሚረዳው ዶክተር አልጋነሽ እንደሚሉት ከዚያ ይልቅ የስደተኞቹ መነሻ በሆነችው በሊቢያ ለችግሩ መፍትሄ ቢፈለግ ይሻላል ይላሉ ።

«የተሻለው መንገድ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች መተላለፊያ መስመር መክፈት ነው ። ያ ማለት አፍሪቃ ውስጥ 2 ሃገራት መርጦ ስደተኞች እዚያ ሆነው እንዲያመለክቱ ማድረግ ነው ። ይህን ተግባር የሚያከናውኑ ኤምባሲዎች ወይም ድርጅቶች ስደተኞቹን እያነጋገሩ ተገን የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ይመርጣሉ ። ይህ ሲሆን የሰዎችን ህይወት እናድናለን፤ ደላላዎችንም እናስቆማለን ። በኔ አመለካከት ሌላ ማሬ ኖስትሮምን ማሰማራቱ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ። »

Symbolbild Flüchtlinge Sizilien Bootsflüchtlinge
ምስል Reuters

ከዚህ ሌላ በዶክተር አልጋነሽ እምነት አውሮፓ በሯን ለስደተኞች ክፍት ማድረግ አለባት ።የመጀመሪያዋ የስደተኞች መድረሻ የሆነችው ኢጣልያም ህጓን ማስተካከል ይገባታል ።

«አውሮፓ የስደተኞች ሃገር መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል ። እነዚህ ሃገራት የሚቀበሉት ስደተኞች መጠን ብዙ አይደለም ችግሩ ከነርሱ በኩል ዝግጁነት አለመኖሩ ነው ። ለምሳሌ ኢጣልያ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ አይደለችም ። ስደተኞችን መቀበል የሚያስችል መዋቅርም የላትም ። ለስደተኞች ምንም ዓይነት እርዳታ አትሰጥም ። የኢጣልያ ስደተኞች አቀባበል ህግ መለወጥ አለበት ህጉ ዘረኛና የሚያዳላ ነው ። ለዚህም ነው ከስደተኞቹ 99 በመቶ የሚሆኑት ኢጣልያን ፣ ወደ ጀርመን ስዊትዘርላንድ ፈረንሳይ ኖርዌይና ስዊድን መሸጋገሪያ የሚያደርጓት »

ከጎርጎሮሳውያኑ 2015 መጀመሪያ አንስቶ በሜዲትራንያን ባህር በኩል 3700 ስደተኞች ኢጣልያ ገብተዋል ።ይህ አሃዝ ደግሞ ከአምናው ጋር ሲነፃጸር ከፍተኛ ነው ። ባለፈው እሁድ ደግሞ የኢጣልያ ድንበር ጠባቂ ባካሄደው መጠነ ሰፊ ዘመቻ በሊቢያና በኢጣልያ መካከል በሚገኘው የባህር ክልል ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩ ከ2000 በላይ ስደተኖችን ታድጓል ።ይህ የኢጣልያ የባህር ላይ የነፍስ አድን ዘመቻ በዘላቂነት መቀጠሉ ለጊዜው ግልጽ አይደለም ። ሆኖም ለአሁኑም ቢሆን ቢያንስ 2ሺህ ስደተኞችን ማዳኑ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ