1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙስና በኢትዮጵያ

እሑድ፣ ጥር 29 2008

ሙስናም ቀስ በቀስ ሥር እየሠደደ፤ ፈጣኑን የምጣኔ ሐብት ዕድገት እየገዘገዘ፤ የመንግሥትን ገቢ እያመናመነ፤ የሐገሪቱን ሐብት እያራቆተ፤ አልፎ ተርፎም የግለሰቦችን ክብር እየናደ፤ ነባሩን ባሕልና ወግ እያናጋም ነዉ።

https://p.dw.com/p/1HqWu

ሙስና በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሐብት ዕድገት ከሚያስመዘግቡ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ መሆንዋ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነዉ።የፖለቲካዉ ነፃነት፤ የሠብአዊ መብት ይዞታ፤ የፍትሕ እና የመልካም አስተዳደር ሥርፀት ግን የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከምጣኔ ሐብቱ ዕድገት በተቃራኒዉ ቁል ቁል እየተንደረደረ ነዉ።

ሙስናም ቀስ በቀስ ሥር እየሠደደ፤ ፈጣኑን የምጣኔ ሐብት ዕድገት እየገዘገዘ፤ የመንግሥትን ገቢ እያመናመነ፤ የሐገሪቱን ሐብት እያራቆተ፤ አልፎ ተርፎም የግለሰቦችን ክብር እየናደ፤ ነባሩን ባሕልና ወግ እያናጋም ነዉ።የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ተቋማት በተለያዩ ዓመታት ባወጧቸዉ ዘገቦች ኢትዮጵያ ዉስጥ ሙስና እየተንሠራፋ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንትግሪቲ (GFI) የተሰኘዉ ተቋም የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ባወጣዉ ዘገባዉ ደግሞ ከግሮጎሪያኑ 2000 እስከ 2012 በነበሩት ዓመታት ብቻ ወደ አስራ-ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የተጭበረበረ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ወጥቷል።

Symbolbild Transparency International Korruption
ምስል picture-alliance/dpa/P. Steffen

ሥለ ሙስና የሚያጠናዉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘዉ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ ባወጣዉ መዘርዝር ኢትዮጵያ በጎርጎሪያኑ 2015 ሙስና አለቅጥ ከተንሠራፋባቸዉ ሐገራት አንዷ መሆንዋን መስክሯል።ተቋሙ ለኢትዮጵያ የሠጠዉ ነጥብ ከመቶ ሠላሳ-ሰወስት ሲሆን፤ ከ168 ሐገራት ደግሞ ኢትዮጵያ 103ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለኝ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1993 ጀምሮ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተሠኘዉ መስሪያ ቤት አማካይነት ሙስናን እየተዋጋ፤ ሙሠኞችን ለፍርድ እያቀረበ መሆኑን በየአጋጣሚዉ ማስታወቁ አልቀረም።ይሁንና ትራንስ ፓራንሲይ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሙስናን የሚከታተሉ የተለያ ተቋማትና አጥኚዎች እንደሚሉት እራሱ ሙስናን እዋጋለሁ የሚለዉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ የጦር ጄኔራሎች፤የፖሊስ መኮንኖችና የቢሮ ባለሙያዎች ሳይቀሩ በኮንትሮባንድ ንግድ፤ በመሬት ሽያጭ፤ በጉቦ፤ እና በምልጃ የተዘፈቁ ናቸዉ።

ሰሞንኑ አዲስ አበባ ዉስጥ በተደረገ የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃ የንግድ ሥብሰባ እንደተገለፀዉ ደግሞ የአሜሪካ ኩባንዮች ኢትዮጵያ ይሁን በመላዉ አፍሪቃ በሚፈለገዉ መጠን የማይወርቱት ሙስና ሥለሚያሰጋቸዉ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሷ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድም መዋዕለ ንዋይ የማፍሰሱን ዕድል የሚዋጉ ሹማምንት ወይም ባለሥልጣናት በየመንግሥታቱ ዉስጥ አሉ» ብለዋል። ሌሎች ተመሳሳይ ዘገቦቹ ወይም እዉነቶችም አሉ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ ይጫኑ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ