1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙስና፤ ግብርና ግብር ሠብሳቢዎች በአፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2007

በአንዳድ የአፍሪቃ ሐገራት ሙስና የሐኪሞችን ሙያዊ ሐላፊነት፤ ቃለ መሐላ፤ ሕሊናዊ ግዴታን ጭምር አሳጥቷል።አፍሪቃዊ ከእንቅልፉ ሲነሳ ይላል ዓለም አቀፉ አጥኚ ድርጅት «ባለችኝ ገንዘብ ለቤተሰቤ ምግብ ልግዛባት ወይስ ሕክምና ለማግኘት ጉቦ ልክፈላት» እያለ ይቆዝማል።

https://p.dw.com/p/1FWen
ምስል picture alliance/dpa

[No title]

የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ) 13 የአፍሪቃ ሐገራት የተመረጡ 27 ግብር ሠብሳቢና የገንዘብ ባለሙያዎችን ለተጨማሪ ትምሕርትና ሥልጠና ወደ በርሊን-ጀርመን ጋብዟል።ትምሕርትና ሥልጠናዉ በተለይ በግብር አሰባሰብ፤ በገንዘብ አያያዝ፤ የግብር ከፋይና አስከፋዮች መብትና ግዴታን በማስከበር ያተኮረ ነዉ።ትምሕርቱ አፍሪቃ ዉስጥ የተንሠራፋዉን ሙስና በተለይ በግብር አከፋፈል ላይ ያለዉን ጉድለት ለማሻሻል ያለመ ነዉ ተብሏል።ይሁንና ሙስናን ለመዋጋት ግልፅና ፍትሐዊ መርሕ ከሌላቸዉ ከአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት የተመለመሉት ሥልጣኞች ወደየሐገራቸዉ ሲመለሱ የሠለጠኑበትን ሙያ በትክክል ገቢር ማድረግ መቻላቸዉ አጠያያቂ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

በኢትዮጵያዉያን ወጣት የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ዘንድ አንድ ሰሞን የሚዘወተር ቀልድ-አዘል እዉነት ነበረ።እነዚያ መስሪያ ቤቶች የተመደበ ወይም የተቀጠረ ባልጀራቸዉን አንዳዶች «ሎተሪ ወጣለት» ሌሎች «ኩዌት ደረሰዉ።» ይሉታል።ዛሬም ቀልዱ እንጂ እዉነቱ ብዙ አልተቀየረም።ወጣቱ ለፖለቲካዉ በማደር፤ በዘመድ-ወዳጅ ፤በእጅ-እግር ተጉዞ፤ በፆም በፀሎት፤ በድል-አጋጣሚም ብሎ ከነዚያ መስሪያ ቤቶች አንዳቸዉ ጋ ከተቀጠረ ድሕነትን «ባጭር ጊዜ ተሰናበተ።»

ድሕነትን የመሰናበቻዉ መሠረት ልዩ ችሎታ፤ እዉቀት፤ ጥረት-ድካም ግን አይደለም።ሙስና እንጂ።ይሕ ነዉ-ድቀቱ።ከመስሪያ ቤቶቹ ታዋቂዎቹ -ሁለትም-አንድም ናቸዉ።«ጉምሩክ» እና የሐገር ዉስጥ ገቢ።ሁለቱም ብዙ ጊዜ አንድ ሚንስቴር (የገንዘብ) የሚያስተዳድራቸዉ የአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ናቸዉ።

ማላዊ ከኢትዮጵያ የተሻለች አይደለችም።ፍራንክ ካሊዚንጂ የማላዊ የሐገር ዉስጥ ገቢ ቋሚ ሠራተኛ ነዉ።ግብር ሠብሰቢ።ለተጨማሪ ትምሕርት በርሊን ከገቡት ሃያ-ሰባት አፍሪቃዉያን አንዱ ነዉ።

«አብዛኞቹ የሐገራችን ሠዎች የግብር ክፍያን መጥፎ አድርገዉ ነዉ የሚገነዘቡት።በዚሕም ምክንያት ያለን ድጋፍ በጣም ዝቅተኛ ነዉ።ሰዉ ግብርን የሚያየዉ መንግሥት ሕዝቡን የሚዘርፍበት ሥልት አድርገጎ ነዉ።ግብር መክፈል ጥቅሙ ለራሳቸዉ እንደሆነ አይቀበሉትም።»

Symbolbild Korruption Bestechung
ምስል Colourbox/Wolfgang Zwanzger

ታዲያ መማር መሠልጠን የነበረበት ማነዉ። ሥለግብር የማያዉቀዉ ወይስ ግብር አስከፋዩ።ለነገሩ ሥለ ግብር ጥቅም አያዉቅም የሚባለዉ ሕዝብ የሚል የሚያደርገዉ ብዙዎች እንደሚሉት በትክክል የሚደረግ፤ ኖሮበት የሚያዉቀዉን።

ሥለ ሙስና ምክንያት፤ ደረጃና ጉዳት የሚያጠናዉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ በአንዳድ የአፍሪቃ ሐገራት ሙስና የሐኪሞችን ሙያዊ ሐላፊነት፤ ቃለ መሐላ፤ ሕሊናዊ ግዴታን ጭምር አሳጥቷል።አፍሪቃዊ ከእንቅልፉ ሲነሳ ይላል ዓለም አቀፉ አጥኚ ድርጅት «ባለችኝ ገንዘብ ለቤተሰቤ ምግብ ልግዛባት ወይስ ሕክምና ለማግኘት ጉቦ ልክፈላት» እያለ ይቆዝማል።

የትኛዉ አፍሪቃዊ መንግሥት ነዉ-ከግብር የሚሰበስበዉን ገንዘብ ሕዝብን መርገጪያ መዋቅሮቹን ከማጠናከር፤ የሥለላና የፀጥታ ሠራተኞቹን ከመቀለብ አልፎ ለግብር ከፋዩ ሕዝብ፤ ፍላጎትና ጥቅም ያዋለዉ? ብዙዎች-ብዙ ጊዜ ጠይቀዉታል።ዛሬም ይጠየቃል።ደቡብ አፍሪቃዊቱ የገንዘብ ሚንስቴር ሠራተኛ ሎንዲቪ ኮዛ ከማላዊያዊዉ ባልደረባዋ የተሻለ መልስ አላት።

«እንደሚመስለኝ ሕዝቡ የሚከፍለዉ የግብር ገንዘብ የሚዉልበትን እንዲያዉቀዉ ማድረግ አለብን።በመንግሥት በኩል ገንዘቡ ለምን እንደሚዉል፤ የት እንደሚሄድ ለሕዝቡ ማሳወቅና ለተገቢዉ አገልግሎት መዋሉን ማረጋገጥ አለበት።»

ትልቁ መልስ የሚገኘዉ በርግጥ ከየመንግሥታቱ ትላልቅ ሹሞች ወይም ከአጠቃላይ መርሐቸዉ ነዉ።የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ድርጅት GIZ አፍሪቃዉያኑን ባለሙያዎች ለተጨማሪ ሥልጠና የጋበዘዉ ባለሙያዎችን ይበልጥ ማስተማር አስተሳሰብ እና አሠራርን ለመለወጥ ይረዳል ከሚል ነዉ።ሃያ ሰባቱ ወጣቶች የሚማሩበት ተቋም ባልደረባ ቤአተ ዮሒምሰን እንደሚያምኑት ተማሪዎቹ ከመደበኛዉ ትምሕርት ሌላ እርስበርስ ከሚያደርጉት ዉይይትም አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ብዙ ይማራሉ ነዉ ተስፋዉ።

Afrika Bauer Symbolbild German food partnership
ምስል Imago

«ብዙዎቹ፤ ለምሳሌ ሥለ ድንበር ተሻጋሪ ግብር ማለትም ሥለ ዓለም አቀፍ ግብር አከፋፈል፤ ወይም ኩባንዮች የገቢ ግብር እንዴት መክፈል እንዳለባቸዉ ምንም አያዉቁም። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት እዚሕ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ በጣም የሚጠቅማቸዉ በቡድን በሚሠሩና በሚያደርጓቸዉ (ዉይይቶች) እዚያዉ አፍሪቃ ዉስጥ ሥላለዉ አሠራር ልምድ የሚለዋወጡበት መረሐ-ግብር መኖሩ ነዉ።»

ተማሪዎቹ ወይም ሠልጣኞቹ ወደየ ሐገራቸዉ ሲመለሱ (ከተመለሱ) በሙስናዉ ባሕር ላለመዋጣቸዉ ማረጋገጫ አለመኖሩ ነዉ-ቀቢፀ ተስፋዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ