1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙዚቀኛ ግርማ በየነ እና አካሌ ዉቤ ባንድ

እሑድ፣ ሰኔ 11 2009

በዘመኑ «ሴት አላምንም» «እንከን የሌለብሽ» «እኔ ነኝ ባይ ማነሽ? » እንዲሁም «ይበቃኛል(ፍቅር እንደ ክራር)» የተሰኙ ሙዚቃዎቹ ተጠቃሽ ናቸዉ።  በ 30ኛዉ የኢቶፒክስ የሙዚቃ መድብል ዉስጥ የሚገኙት የግርማ በየነ ሙዚቃዎች አብዛኞቹ የተቀናበሩት በሙዚቃ አዋቂዉ ድምጻዊ በግርማ በየነ በራሱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2elwF
Girma Bèyènè und Akalé Wubé
ምስል Akalé Wubé

,

በ 60 ዎቹና 70 ዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ የነበሩ ታዋቂ ድምጻዉያን የተጫወቱዋቸዉን ሙዚቃዎች «ኢቶፒክስ» በሚል ስያሜ በተከታታይ ከወጣዉ የአልበም ስብስብ ከ 30ኛዉ አልብም የተወሰደ በአንጋፋዉ ሙዚቀኛ ግርማ በየነ በአዲስ ተሻሽሎ በቅርቡ ለአድማጮች ጆሮ የደረሰዉን ሙዚቃ ነዉ። ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈዉ ኅዳር ፓሪስ ላይ የተመረቀዉና ባለፈዉ ሳምንት በድሪደዋ እና አዲስ አበባ ላይ በአራት ዝግጅት የተመረቀዉ 30ኛዉ የኢቶፒክስ የሙዚቃ አልብም፤ የሙዚቃዉ ተራ ቁጥር ብቻ ሳይሆን አንጋፋዉን ሙዚቀኛ ግርማ በየነን ከሚወደዉና ከ30 ዓመት በላይ ከተለየዉ መድረኩ ያገናኘዉም ነዉ። የፈረንሳዩን የሙዚቃ ቡድን አካሌ ዉቤን እና አንጋፋዉን ሙዚቀኛ ግርማ በየነን  በእንግድነት ይዘናል።     

Girma Beyene
ምስል Pierre Guillaud

በ 1950 ዎቹ አጋማሽ በመደመጡና በዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀዉ፤ አንጋፋዉ ድምጻዊ እዉቅ የፒያኖ ተጫዋች፤ ሙዚቃ አቀናባሪና ቀማሪና ግርማ በየነ፤ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ከተለዩት ከሙዚቃ መድረክ በኢቶፒክስ ሠላሳኛ የሙዚቃ አልብም ከ 14 ሙዚቃ ጋራ ብቅ ብለዋል።

በዘመኑ «ሴት አላምንም»   «እንከን የሌለብሽ»  «እኔ ነኝ ባይ ማነሽ? » እንዲሁም «ይበቃኛል(ፍቅር እንደ ክራር)» የተሰኙ ሙዚቃዎቹ ተጠቃሽ ናቸዉ።  በ 30ኛዉ የኢቶፒክስ የሙዚቃ መድብል ዉስጥ የሚገኙት የግርማ በየነ ሙዚቃዎች አብዛኞቹ የተቀናበሩት በሙዚቃ አዋቂዉ ድምጻዊ በግርማ በየነ በራሱ ነዉ።  በ2009 ዓ.ም ሰኔ ወር የመጀመርያ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተደረገዉ የሙዚቃ ዓልብም ምርቃት ላይ ሙዚቀኛ ግርማ በየነን በስልክ አግኝተነዉ ነበር።

Girma Beyene
ምስል Pierre Guillaud

ግርማ በየነ ዛሬ እርጅና ጫን ብሎታል። ዛሬ ዳግም  ለሙዚቃ አፍቃሪዉ ዘመን ተሻጋሪዉን ሙዚቃዉን በጆሮ ማንቆርቆሩን ጀምሮአል።  የግርማን ሙዚቃ የሃገሩ ልጆች ቋንቋዉን እና ባህሉን የሚያዉቁት ብቻ ሳይሆኑ ወዝወዝ እና ቆዘም የሚሉበት አዉሮጳዉያን በተለይ ደግሞ ፈረንሳዮቹ ናቸዉ። ጀርመን ገና አልመጣሁም ጋብዙኝ እያለ ነዉ። ግን ሌሎች አዉሮጳ ሃገራት ለመሄድ መረሃግብሩን ቀርፆ የቀኑን መዳረስ እየጠበቀ ነዉ።

ከሙዚቀኛ ግርማ በየነ ጋር በአዲስ አበባና ድሬደዋ ላይ የሙዚቃ ድግሱን ያሳየዉ ሙሉ የፈረንሳይ የሙዚቃ ባንድ መጠርያዉም « አካሌ ዉቤ » ይባላል አካሌ ዉቤ የኢትዮጵያን የጥንት የጠዋቱን ሙዚቃ የአንጋፋዎቹ ሙዚቀኞች በባትሪ  እያደነ መጫወት ከጀመረ አስር ዓመት ግድም ሆኖታል። ግርማ በየነንም ርግፍ አድርጎ ከተወዉ ሙዚቃ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ነበር የመለሱት ከዝያም ይኸዉ ዛሬ የሙዚቃ አልበሙ ለምርቃት በቃ። የሙዚቃ ባንዱ የቤዝ ጊታር ተጫዋች ኦሊቨር ዴ ገብርኤለ እንደሚለዉ የምርቃቱ ሥነ-ስርዓት በድሬደዋና አዲስ አበባ ላይ ነበር።

CD Cover Girma Bèyènè und Akalé Wubé
ምስል Akalé Wubé

«አዲስ አበባ ከደረስን በኋላ አራት ኮንሰርቶችን ተጫዉተናል። የመጀመርያዉን የሙዚቃ ድግስ የነበረዉ ፈድቃ አሳየን በመለጠቅ ብሔራዊ ትያትር አሳየን፤ ከዝያ አፍሪቃ ጃዝ መንድር ከዝያ እንደገና ብሔራዊ ትያትር ነበር ያቀረብነዉ። ባለፈዉ ቅዳሜ በዚሁ በብሔራዊ ትያትር በነበረዉ የሙዚቃ ድግስ ላይ የተገኘዉ ሰዉ እጅግ ብዙ ነበር። የሙዚቃዉን ድግስ ለማየት የመጣዉ ሰዉ ሁሉ ሙዚቃኛ ግርማ በየነን ለማየት በጣም ጉጉት እንዳደረበት ይታይ ነበር። ከሕዝብ ይህን ያህል ፍቅርና ጉጉትን ማየቱ  ለሙዚቀኛ ግርማ በየነም ሆነ ለኛ ለሙዚቃ ባንዱ እጅግ ያባባን ነገር ሆኖ ነዉ ያገኘነዉ። እና ባንዱ መድረኩ ላይ ከቀረበ በኋላ ግርማ በየነ ከመድረክ በስተጀርባ በኩል ወደ መድረኩ ሲገባ በአዳራሹ ያለዉ ሕዝብ ሁሉ ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲያጨበጭብ እና በደስታ ሲጮህ ሲያይ በጣም ባብቶ አይተነዋል። ዓይኑ ላይ ሁሉ እንባ አቅርሮ ይታይ ነበር። በአዳራሹ የነበረዉ ታዳሚ ግርማ ሲያዜም አብሮ ያዜም ነበር። በጣም የሚያስገርም ዓይነት ሁኔታ ነበር የሚታየዉ።»

ይህ የፈረንሳይ የሙዚቃ ጓድ የቤድኑን ስያሜ «አካሌ ዉቤ» ብሎ መስጠቱ  እንዴ ሳያሰኝ አልቀረም ። በባንዱ አንድም አበሻ አንድም ጥቁር የለም ሁሉምl ነች ፈረንሳዊያን ናቸዉ። በኢትዮጵያ ፍቅር ከተነደፉ በኋላ ባህላዊ ምግቧን ከዝያም ቡናን የቡናቁርስዋን እንደሚወዱ ኦሊቨር ከሸገር የግርማ በየነን ሙዚቃ ለማስመረቅ ካለበት ከሸገር በስልክ አዉግቶናል። እንደዉም አካሌ ዉቤ ማለት ምን ማለት እንደሆን ሊያስረዳኝ ገባ። እንዴት ስያሜዉንም እንዳገኘ ተርኮአል። ግን በመጀመርያ የአካሌ ዉቤ ትርጉም ነዉ የተናገረዉ።

Girma Beyene
ምስል Pierre Guillaud

« የአካሌ ዉቤ የሙዚቃ ባንድ ከተመሰረተ አስር ዓመቱን የያዘ ይመስለኛል። አካሌ ዉቤ ማለት፤ የነፍስ ዉበት ፤ ወይም ዉብ የሆነች ሴትም ማለት ይሆናል። እነደ አግባቡ የተለያየ ትርጉምን ሊይዝ ይችላል። ቅኔያዊ ስያሜ ነዉ። ይህን ስም ያገኘነዉና፤ ለሙዚቃ ባንዱ መጠርያ እንዲሆን ያደረግነዉ፤ ከታዋቂዉ የሳክፎን ተጫዋች ጌታቸዉ መኩርያ የሙዚቃ አልብም አንድ መጠርያን ወስደን ነዉ። ስሙን የሰጠነዉ እንዲህ ነበር። ከአስር ከዘጠኝ ዓመት በፊት ይሆናል በፓሪስ የሚገኝ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቤት ሄድን። የጌታቸዉ መኩርያን የሙዚቃ ሴዴን ይዘን ነበር።  በሲዴዉ ላይ አንዱ ሙዚቃ አካሌ ዉቤ ይል ነበር። ዝም ብለን መረጥንና ለባንዱ ስያሜ ሰጠን። ድምጹ ስናነበዉ ደስ ስላለን ነዉ። ግን ትርጉሙ ምን እንደሆን አናዉቅም ነበር። አጠራሩ ደስ ስላለን ብቻ ነበር የወሰድነዉ። ከዝያ በኋላ ቆይተን ትርጉሙን ካወቅን በኋላ ለኛ ባንድ ተስማሚ መሆኑን ሁሉ ተረዳን። ባንዳችን በዚህ ይጠራል ብለን ወሰንን ይህ ነዉ እንግዲህ ታሪኩ»

ኦሊቨር ልማድ ሆኖበት ነዉ። ስለአካሌ ዉቤ ትርጉም ሊያስረዳ የዳዳዉ፤ ምክንያቱ ቡድኑ የሙዚቃ ድግሱን ሲያያቀርብ መጀመርያ የሚያደርገዉ ስለ «አካሌ ዉቤ» ትርጉም  ምን ማለት እንደሆነ ከየት እንዳገኘዉ ስለ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለጠቅ ሲልም ታሪክዋን ሁሉ እንደናገርና በተለይ ስለ ወርቅማ ስለሚባሉት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመናት፤  ስለ የኢትዮጵያ አንጋፋዎቹ ሙዚቀኞች አዉርቶ እንደማይጠግብ ተናግሮአል። 

Girma Bèyènè und Akalé Wubé
ምስል Akalé Wubé/Bernard Nicolau-Bergeret

« ላለፉት ሁለት ዓመታት ከድምጻዊ ግርማ ጋር መስራት ላይ ነን። ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ፓሪስ እንዲመጣ ለመጀመርያ ጊዜ ጋበዝነዉ። ሙዚቀኛ ግርማን አግኝተን ወደዚህ እንዲመጣ ለማድረግ ት የቻልነዉ በበርካታ ሰዎች ርዳታ ነዉ። ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ፤ የኢቶፒክስ ሴዲ አልብም አሳታሚ ፈረንሳዊዉ ፍራንሲስ ፋልሴቶ፤ ግርማን እንድንገናኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከተጫዉቱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸዉ። ከዝያም ፓሪስ ዉስጥ የሙዚቃ ትርኢትን አሳይተን ከፍተኛ አድናቆትን ነዉ ያተረፍነዉ። ብዙ ሰዎች የመጡት ምናልባት ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ የማያዉቁ የነበሩ ናቸዉ። ስለ ግርማ በየነ ታሪክ ብቻ ሰምተዉ እንደዉ ለማየት ብቻ መጥተዉ ኢትዮጵያን ተዋዉቀዉ ሙዚቃዉን አድንቀዉ ነዉ የተመለሱት። ለኛ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ዉጤትና ድል ነበር። የሚገርመዉ ግርማ በየነ ከ30 ዓመት በላይ ከሙዚቃዉ ዓለም ከተለየ በኋላ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ፓሪስ ላይ ከኛ ጋር በመሆን ወደ መድረኩ ዳግም የገባዉ። በጣም ብዙ ሕዝብ ነበር፤ ሁሉ ሰዉ በጉጉት ነበር ያየዉ።»

እዉቅ የፒያኖ ተጫዋቹ ፤ የሙዚቃ አቀናባሪና ቀማሪ አንጋፋዉ ድምጻዊ ግርማ በየነ ስለ  ድምጻዊ ግርማ በኢትዮጵያ ታሪክ ወርቃማዉ ዘመን በመባል የሚታወቀዉን ጊዜ እንዲህ ያስታዉሳል።

ሙዚቀኛ ግርማ በየነ አድማጭ እንደወደደዉ ከሙዚቃዉ መድረክ እንደወረደ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ጠፍቶ መክረሙ ለምን ይሆን የብዙዎች ጥያቄ ነዉ። እኛም ጠየቅነዉ ግን የግል ጉዳይ መሰለኝ መመለስ አልፈለገም።

አንዳንድ ዘገባዎች ሙዚቀኛ ግርማ በየነ በጣም ያዘነበት ሃዘን ደርሶበት እንደነበር ይጠቁማሉ። አሁን ወደ አካሌ ዉቤ ልመልሳችሁ» እንደዉ ምን አይነት ባትሪ ቢይዙ ነዉ አንጋፋዉን ሙዚቀኛ ግርማ በየነን ፈልገዉ ያገኙት ኦሊቨር ከሁለት አበት በፊት ይላል።

Girma Bèyènè und Akalé Wubé
ምስል Akalé Wubé

« በመጀመርያዉ የሙዚቃ ትዕይንት ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማግኘታችንን  ካየን በኋላ ከግርማ በየነ ጋር የሙዚቃ አልብምን ለማሳተም ወሰን። ከዚያ ነዉ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ፓሪስ ጋብዘነዉ፤ አብረን የሰራነዉን ሙዚቃ ቀረፅን። ሙዚቃዉን ስንሰራ የተለያዩ አዲስ ፈጠራዎችን ሞከረናል። ብዙ ነገሮችን ለማካተት ሞክረናል። ከዝያም የቀዳነዉን ለኢቶፒክስ የሙዚቃ አልብም ዳይሪክር ለፍራንሲስ ፋልሴቶ ሰጠን። ፍራንሲስም ሙዚቃዉ 30ኛዉ የኢቶፒክስ አልብም ስብስብ  ሆኖ መዉጣት አለበት ብሎ ወሰነ። ከዝያም አልብሙ ታተመ ና፤ ግርማን በጎርጎረሳዊዉ 2017 ዓመት መጀመርያ ኅዳር ወር ወደ ፓሪስ ለሦስተኛ ጊዜ ጋብዘን የሙዚቃ አልበሙን በከፍተኛ የሙዚቃ ድግስ አስመረቅን።  አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ የሙዚቃ አልበሙን ዳግም አሳትመን አዲስ አበባ ላይ ለመመረቅ ተገኘን ማለት ነዉ» 

ወጣቱ የሙዚቃ መሳርያ ባለሞያዉ ግሩም መዝሙር የአንጋፋዉ ሙዚቀኛ የግርማ በየነ አድናቂ ነዉ፤ የግርማ ሙዚቃ z።መን ተሻጋሪነቱን በዝርዝር አስረድቶአል። ሙዚቀኛ ግርማ በየነ አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ 7 ዓመት እንደሆነዉ ተናግሮአል። ከኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያዉያን ሙዚቀኞች ታጅቦም ያዜማል። ስለ ሙዚቀኛ ግርማ በየነ እና ስለፈረንሳዩ «አካሌ ዉቤ የሙዚቃ ባንድ፤ በድምጽ የተዘጋጀዉን ሙሉ ቅንብር፤ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ