1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚሊዮን ዶላር በዩቲውብ

ዓርብ፣ የካቲት 3 2009

ከማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መካከል አንዱ በሆነው ዩቲውብ በአንድ ጀምበር ባለ ፀጋ የሆኑ ጥቂቶች አይደሉም። ለአብነት ያኽል ስዊድናዊው ፒውዲፓይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 ዓመት በዩቲውብ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ቀዳሚው ነው። በዩቲውብ የሚጫኑ ቪዲዮዎች በእርግጥም ብዙ ተመልካቾችን ባስገኙ ቊጥር በርካታ ገንዘብ ያስገኛሉ።

https://p.dw.com/p/2XISU
Symbolbild YouTube Bezahlmodell Einführung
ምስል Reuters/L. Nicholson

በዓለማችን በዩቲውብ (YouTube) በርካታ ገቢ እና ተከታዮችን በማፍራት ቊጥር አንድ ታዋቂ የሆነው  ስዊድናዊው ፒውዲፓይ ሥራዎቹን 53 ሚሊዮን አድናቂዎቹ በመደበኛነት ይከታተሉለታል። ፎርብስ የኢኮኖሚ እና ቢዝነስ መጽሄት መረጃ እንሚጠቁመው ስዊድናዊው በጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከዩቲውብ በማግኘት የሚስተካከለው እንደሌለ ይጠቁማል። 

እንደ ፒውዲፓይ ባይሆንም ኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎች ሥራዎቻቸው በዩቲውብ ሲታዩላቸው ገቢ ያገኛሉ። የድሬ ቲዩብ መሥራች እና ባለቤት ቢኒያም ነገሡ በደንብ ከተያዘ እና ቊጥጥር ከተደረገበት የፈጠራ ሰዎች በዩቲውብ ለሥራዎቻቸው ደህና ገቢ ማግኘት ይችላሉ ይላል። «አንድ ሙዚቀኛ ክሊፕ ሠርቶ በዩቲውብ ሲለቅ መቶ በመቶ ከሦስት መቶ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ገቢ ያገኛል።»

PewDiePie
በዩቲውብ 15 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛው ተከፋይ ስዊድናዊው ፒውዲፓይምስል Roslan Rahman/AFP/Getty Images

ቢንያም አንድ የቪዲዮ ሥራ በሦስት ወር ውስጥ አንድ ወይንም ሁለት ሚሊዮን እይታ ካለው ከአንድ መቶ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ የሚያገኝበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። ይኽ ገቢ የተመልካች ቊጥር እስካልተቋረጠ ድረስ መጠኑ ከፍ ዝቅ ይበል እንጂ እንደማይቋረጥም ይጠቅሳል። የዚያን ያኽል ክፍያ ለባለሞያ እንደፈጸሙም ገልጧል።

ዩቲውብ ማንኛውም ሰው በቀላል ሊጠቀምበት የሚችል የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ነው። በዩቲውብ ለመጠቀም በዋናነት የሚያስፈልገው ካሜራ እና ኢንተርኔት ነው። በተለይ ዘመናዊ ስልክ ያላቸው ሰዎች ቀለል ያሉ ሆኖም ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎችን ዩቲውብ ላይ በመጫን ገቢ ማግኘት ይችላሉ። መጀመሪያ ግን ኢንተርኔት ውስጥ ተገብቶ የዩቲውብ አድራሻ በስም ማስመዝገብ ይገባል። ከዚያም የሚጫኑት ቪዲዮዎች ወይንም በተንቀሳቃሽ ምስል የታጀቡ የድምጽ መልእክቶች በርካታ ተመልካች ባገኙ ቊጥር የጫነው ግለሰብ ገቢ ማግኘት ይችላል።

በእርግጥ ኢንተርኔት ውስጥ የሚሞሉ መስፈርቶች እንዳሉ ኾነው ማለት ነው። ታዲያ በቀላሉ ገቢን ለማግኘት በመመኘት ወይንም በሌላ ምክንያት የፈጠራ ሥራዎች በዩቲውብ ሲባክኑ መመልከት የተለመደ ነው። ደራሲ መአዛ ወርቁ እጅግ ከፍተኛ ልፋት እና ጥረት ያደረገችበት የፈጠራ ሥራዋ ያለፈቃድዋ ኢንተርኔት ላይ የተመለከተችው በአጋጣሚ ነበር።  

«ማን እንደሆነ የማይታወቅ የሆነ የአፍሪቃ የሚመስል ስም ያለው፤ ግን ጭራሽ ሰምቼው የማላቀው አንድ ሰው ጉግል ላይ አማርኛውን እና እንግሊዝኛውን የቴአትሬን ጽሑፈ-ተውኔት ጎን ለጎን አውጥቶታል። እና በተለይ አማርኛው ጽሑፍ ማንም ሰው እጅ ላይ በተለይ ኢንተርኔት ላይ ሊወጣ ይችላል ብዬ ባልጠበቅኹት ኹኔታ አየሁት። እና በጣም ገረመኝ። እና ምን አይነት የድፍረት ትጋት ቢኖረውነው ይኼ ሰው እንደዚህ አድርጎ ያስቀመጠው?»

Los Angeles YouTube Space LA Bezahlmodell Einführung
ምስል Reuters/L. Nicholson

መአዛ ከድርሰቷ በተጨማሪ ቴአትሯ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ ከመድረክ ላይ ተቀርጾ ዩቲውብ ላይ ያለፈቃዷ መውጣቱን ታውቃለች ግን ምንም ያደረገችው ነገር የለም። 

መአዛ ዩጋንዳ ካምፓ ላይ ያሳየችው ቴአትር በሷ ፈቃድ ወደ ቡሩንዲ እና ሩዋንዳ ለፌስቲቫል ተወስዶ መድረክ ላይ ሲቀርብ በቦታው አልነበረችም። «የሩዋንዳው የመድረክ ሥራ ሲቀርብ እኔ በቦታው አልነበርኩም። ነገር ግን ቆይቼ ዩቲውብ ላይ [ስመለከት] ሙሉው ቴአትር ከመድረክ ተቀርጾ ዩቲውብ ላይ ተጭኖ አየሁት። እና በጣም ገረመኝ።»

የድሬ ቲውብ ባለቤት ቢንያም ምንም እንኳን አላግባብ የሰዎችን ሥራ የሚጠቀሙ ሰዎች ቢኖሩም የፈጠራ ሰዎች ሥራዎቻቸው ኢንተርኔት ላይ ሲወጡ በአሁኑ ሰአት ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግሯል። 

«ምንም ሰው ከየትኛው ዓለም ላይ ሆኖ ቢጭነው እኛ ዩቲውብ ላይ የጫነውን ቪዲዮ ሌላ ሰው ቢጭነው በቀላሉ የምንቆጣጠርበትን መንገድ ዩቲውብ አመቻችቶልናል።»

የዩናይትድ ስቴትሱ የስለላ ተቋም (CIA) የኢንተርኔት መረጃ 100 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ የሞባይል ተጠቃሚዎች 42 ሚሊዮን እንደኾነ ይጠቁማል። ምን ያኽሉ ዘመናዊ ስልክ እንዳለው እና ዩቲውብ እንደሚጠቀም አይታወቅም።

ዩቲውብ ገና ከአመሰራረቱ አንስቶ ይዞት የተነሳው ግቡ ተጠቃሚዎች የሚሠሯቸውን ቪዲዮዎች በስፋት ሌሎች እንዲመለከቱት ማዳረስ ነው። በዩቲውብ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ የተጫነው ቪዲዮ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2005 ዓመት ሲሆን የ18 ሰከንድ ርዝማኔ አለው። «እኔ በመካነ አራዊት ውስጥ» የሚል ርእስ የተሰጠው ይኽ አጭር ቪዲዮ በአጥር ውስጥ ተከልለው ቅጠል ከሚበሉ ዝኾኖች ፊት ለፊት ሆኖ የሚናገር ወጣት የሚታይበት ቪዲዮ ነው። ይኽን አጭር ቪዲዮ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል። 

በየደቂቃው በዓለማችን 300 ሰአት ርዝማኔ ያላቸው የተለያዩ ቪዲዮዎች ዩቲውብ ላይ ይጫናሉ። በየቀኑም 5 ቢሊዮን ቪዲዮዎች ዩቲውብ ላይ ይታያሉ። በአማካይ ዋነኛ የዩቲውብ ተመልካቾች እድሜያቸው ከ18 እስከ 49 የሚደርሱ ሰዎች ናቸው። 

ዩቲውብ ሥራዎቻቸው የተሰረቁባቸው ወይንም ያለአግባብ ጥቅም ላይ የዋሉባቸውን ሰዎች የሚረዳበት መንገድ አለው። ዩቲውብ ገጽ ውስጥ «የፈጠራ መብት አቤቱታ ካለዎት ያመልክቱ» የሚል ቅሬታ ማቅረበያ ቦታ አመቻችቷል። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማጫወቻውን ይጫኑ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ