1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማማ ትኩስ እንጀራ- የመቶ አመት እቅድ

ረቡዕ፣ መጋቢት 28 2008

ማማ ትኩስ እንጀራ እንዲህ እንደ ዛሬ ስሙ ከመግነኑ በፊት ደንበኞቹ የአዲስ አበባ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች ነበሩ። የድርጅቱ ምርቶች ዛሬ ድንበር ተሻግረው ናይጄሪያ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመንን በመሳሰሉ አገሮች ለሚገኙ የእንጀራ እና የኢትዮጵያ ባልትና ፈላጊዎች መድረስ ችለዋል።

https://p.dw.com/p/1IQI8
Enjera Äthiopien
ምስል Mama Fresh

ማማ ትኩስ እንጀራ- የመቶ አመት እቅድ

አቶ ሐይሉ ተሰማ ከ13 ዓመታት በፊት ማማ ትኩስ እንጀራን ከመመስረታቸው በፊት በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው አገልግለዋል። አቶ ሐይሉ እንጀራ ጋግሮ የመሸጥ ስራን አንድ ብለው ሲጀምሩ የመነሻ ካፒታላቸው 100,000 ብር የሰራተኞቻቸውም ብዛት አምስት ብቻ ነበር።

በ100,000 ብር የተጀመረው ማማ ትኩስ እንጀራ የመንቀሳቀሻ የገንዘብ አቅሙን ወደ 17 ሚሊዮን ብር አድርሷል። የሰራተኞቹ ብዛትም ከ105 በላይ ደርሷል። ከእንጀራ ተሻግሮ ዶሮ ወጥ ፤ ቆጮ ፤ ሽሮ ፤ በርበሬ ፤ ሚጥሚጣን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ግብዓቶቹን ለደንበኞቹ ያቀርባል። ከጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እነዚህን ምርቶቹን ወደ ውጭ አገራት መላኩን አቶ ሐይሉ ተሰማ ይናገራሉ።

በአቶ ሐይሉ እና በቤተሰቦቻቸው የሚመራው ማማ ትኩስ እንጀራ ዘመናዊ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል። እነ አቶ ሐይሉ ስራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማስፋፊያ እቅድ መሰረት ከመንግስት የተለያዩ ድጋፎች እንደተደረጉላቸው ተናግረዋል። የማምረቻ ቦታ እና የብድር አቅርቦት እንድናገኝ ከመንግስት ድጋፍ ተደርጎልናል የሚሉት አቶ ሐይሉ ፖሊሲው ለሌሎች መሰል ሥራ ጀማሪዎች መልካም እድል ነው የሚል እምነት አላቸው።

Enjera Äthiopien
ምስል Mama Fresh

የኢትዮጵያ መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶች የመስሪያ ቦታ፤የብድር አቅርቦት እና ስልጠና ማመቻቸት ከጀመረ አስር ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። በአንድ ወቅት በተለይ በሥራ አጥ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የነበረው ፖሊሲ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሁነኛ ሚና ሊጫወት ይችላል ተብሎለትም ነበር። የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም ገና ጀማሪ ለሆነው እና በግዙፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያልወደቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማማ ፍረሽን ለመሳሰሉ ድርጅቶች በሒደት ለማደግ እድል እንደሚሰጥ ያምናሉ።

በጥቃቅን አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የልማት ፖሊሲ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ማማ ትኩስ እንጀራን የመሰሉ እጅግ በጣም ጥቂቶች ስኬታማ መሆን ችለዋል።የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ዓመት በዚሁ ዘርፍ ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች ስራ መፍጠሩን አስታውቆ ነበር። ለዚሁ ዘርፍ 15 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የዓለም ባንክ በበመጋቢት 2015 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ በርጃታ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የገበያ እድል ይሰጣል የሚሉት አቶ ጌታቸውም ተግዳሮቶቻቸው በርካታ እንደሆኑ ይስማማሉ።

Enjera Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele Tekele

አቶ ሐይሉ ተሰማ በኢትዮጵያ የገበያ ፍላጎትን አጥንተው በአነስተኛ የገንዘብ አቅም ሥራ ከሚጀምሩ ድርጅቶች በተጋነነ የገንዘብ መጠን ለሚመሰረቱ ድርጅቶች ትኩረት እንደሚሰጥ ይተቻሉ። በ119 አገሮች ከ68 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ማክዶናልድ ኩባንያን በዓርዓያነት የሚጠቅሱት አቶ ሐይሉ ለማማ ትኩስ እንጀራ የመቶ አመታት እቅድ መሰነቃቸውን ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም አነስተኛ እና ጥቃቅን የልማት ተቋማት በምርት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚኖራቸው እድገት በተመለከተ ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አለመኖራቸውን ይናገራሉ። የማማ ትኩስ እንጀራ እድገት ከውጭ ንግድ ስርዓቱ ጋር በመቆራኘቱ መሆኑን የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው ተመሳሳይ ድጋፍ ለሌሎች ተቋማትም አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

ማማ ትኩስ እንጀራ ኩባንያ በዓመት ከ15 እስከ 20 በመቶ እድገት አሳይቷል የሚሉት አቶ ሐይሉ ተሰማ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣው የጤፍ ተፈላጊነት ከፍተኛ ጥቅም እንደሰጣቸው ተናግረዋል። አቶ ሐይሉ ከደንበኞቻቸው መካከል ከ10-15 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ