1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማንዴላና ትውልድ ቦታቸው ኮኑ፣

ዓርብ፣ ሰኔ 28 2005

በዓለም ዙሪያ እጅግ የታወቁትና የተከበሩት የደቡብ አፍሪቃ ፀረ አፓርታይድ ስመ ጥር ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ፣ ሀኪም ቤት ውስጥ ፣ በሞት-ሽረት ላይ እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ የተወለዱባት መንደር፣ ኩኑ፣ ኑዋሪዎች፣ በእርሳቸው ዝና ሳቢያ የኤኮኖሚ

https://p.dw.com/p/192vN
ምስል Reuters

ጠቀሜታ የሚያገኙበትን አጋጣሚ አሁንም ገና በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ከምሥራቅ ኬፕ ወጣ ብላ ወደምትገኘው መንደር ጎራ ያለው ሉድገር ሻዶምስኪ፣ የአካባቢውን ተወላጆችና ጎብኝዎች አነጋግሮ ዘገባ ልኳል፣

«አሁን የተሣካለት የንግድ ሰው ለመሆን የበቃሁት በነጻነቱ ትግል ውጤት ነው። የዶክተር ማንዴላ መስዋእትነት ለእኛ ለጥቁሮቹ የአገሪቱ ነባር ተወላጆች፣ በሮች የከፈተልን ሲሆን ፣ ዛሬ የዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን ፍሬ በመመገብ ላይ ነን። እዚህ የመጣሁት የተወለዱበትን ቦታ ለማየትና ከህይወቴ ጋር ለማገናዘብ ሲሆን ፣ የጥቁሮች ታሪክ እዚህ ላይ በትርዒት መልክ እንዲቀርብ ማድረግ ይቻላል ብዬም አምናለሁ።»

Nelson Mandelas Heimatregion Qunu
ምስል DW/L.Schadomsky

ሉታንዶ ምዚዚ የተባሉት ደቡብ አፍሪቃዊ ናቸው ይህን ያሉት። እ ጎ አ በ 1994 ለውጥ ከተከሠተ በኋላ፤ የንግድ ሰው ምዚዚ፣ ከአክሲዮን ገበያ ጋር ግንኙነት ያለው የንግድ ድርጅት በማቋቋም ፤ በአሁኑ ጊዜ ለ 50 ሰዎች የሥራ ዕድል ሰጥተዋል።

ሉታንዶ ምዚዚ፣ መንግሥት በነደፈው ፤ ጥቁሮችን ለኤኮናሚ ሥልጣን ማብቃት(“Black Economic Empowerment”)በተሰኘው መርኀ- ግብር የተጠቀሙ ናቸው።

የመርኀ-ግብሩ ዓላማ ፣ አድልዎ ሲፈጸምባቸው የኖሩት ነባሮቹ ጥቁሮች፣ በኤኮኖሚ እንዲጠናከሩ ማድረግ ነው። በአሁኑ ጊዜ ፤ ነጭ ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን አድልዎ ተፈጸመብን እንደሚሉም ይነገራል። የኩኑ መንደር ወጣት ኑዋሪዎች፤ ብሩኅ የኤኮኖሚ ዕድል ለማግኘት በህልም ዓለም ብቻ ነው እስካሁን የሚገኙት።

ኢሞንቲ ምዲንጋኔ፤ ሲፌሎ ማቢና አሳንዳ እንቖሻ የተባሉ 3 የአልኮል ሱሰኞች ጠረናቸው ከሩቁ ይታወቃል ። ዓይናቸው በሃሺሽ ጭምር ቀላልቷል። ከቀትር በኋላ ነው ፣ የማንዴላ ቤተ-መዘክር አቅራቢያ ወደሚገኝ ኪዎስክ ሲጋራ ሊገዙ ብቅ ያሉት። አንዳንድ ነጠላ ሲጋራ ካልሆነ «ፓኬቱን» ለመግዛት የገንዘብ አቅማቸው አይፈቅድም። ኪዮስኩ ዙሪያ ያለው አዲስ መኖሪያ ሠፈር በድኽነት ሳቢያ ጎስቋላ ነው። ቆሻሻ በየቦታው ተጥሎ ይታያል። በጡብ የተሠሩት ጎጆዎች ባስቸኳይ እድሳት ያሻቸዋል።

ኢሞንቲ እምዲንጋኔ

«ወጣቶቹ፣ ሁሉም እዚህ ጎዳና ላይ ነው የሚቀመጡት። እኔም አልተሳካም እንጂ ሥራ በመፈለግ ላይ ነኝ። እንዲሁ ነው የምንገላወደው! እዚህ የሚንቀሳቀስ ምንም ነገር የለም»።

Nelson Mandelas Heimatregion Qunu
ምስል DW/L.Schadomsky

ሲፌሎ ማቢ፤

«እዚህ የምንሠራው ምንም ነገር የለም። ከእጅ ወደአፍ ነው ኑሮአችን። ስለሆነም፤ ማንዴላ እንደገና ጤንነታቸው ቢመለስ ጥሩ ነው፣ ምንጊዜም እኛ ወጣቶች እንድንሠቃይ አይፈልጉምና! ስለሆነም እንደገና ጤንነታቸው እንዲመለስ ለእግዚአብሔር ጸሎቴን አቀርባለሁ።እርሳቸው የና ሙሴ ናቸው። የአሁኑ ፕሬዚዳንታችን ለእኛ ሥራ አይሰጡም። ለራሳቸው ጠ/ግዛት ሰዎች ነው የሚያደሉት። እነርሱ የተደላደለ ኑሮ አላቸው። እኛ በዚህ በኩኑ የምንገኝ ሰዎች ግን ፤ ምንም የለንም።»

የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙት ማንዴላ፤ በልጅነት በደስታ ማደጋቸውን ነው በህይወት ታሪካቸው መጽሐፍ ላይ ያሠፈሩት። በእርሳቸው የልጅነት ወቅት ያማረ የነበረው ኮረብቶች ያሉበት ምሥራቅ ኬፕ ፤ የዛሬዎቹ ወጣቶች ብሩኅ ሁኔታ የሚያዩበት አልሆነም።

ከኬፕታውን ፣ የማንዴላን ቤተ መዘክር ለመመልከት የተጓዙት ሊዛ ኮፕላንድና 3ቱ ልጆቻቸው የሚያስታርቅ ቃል ነው የሰነዘሩት።

Nelson Mandelas Heimatregion Qunu
የማንዴላ የትልዉድ ቦታ እርሻምስል DW/L.Schadomsky

የ 6 ዓመቷ ልጅ፤ ኦሊቪያ ቤተመዘክሩን ተዘዋውራ ካየች በኋላ፣ አንድ ነገር ስለመማሯ እንዲህ ነበረ ያለች።

«እዚህ ኖራል ያደጉት፤ ከብቶችንም ይጠብቁ ነበር። »

እናቷ ደግሞ እንዲህ አሉ።

« ልጆቼ፣ ማንዴላ የተወለዱበትን ቦታ ሳይሞቱ መጎብኘታቸውን ወደፊት ለራሳቸው ልጆች፤ እንዲተርኩላቸው ፤ ይህን ዕድል መስጠት ፈለግሁ። ልብ ይበሉ! አሁን የደቡብ አፍሪቃን ይዞታ በቃላት መግለጽ አስቸጋሪ ነው። እርግጥ ነው በየቦታው ሥራ አጦች ተበራክተዋል። ገና ብዙ ሥራ ማከናወን ያሻል። ቀጣዩ ትውልድ ኀላፊነትን እስኪሸከም ትዕግሥት ሊኖረን ይገባል። አሁን ከጥቁሮቹም ከነጮቹም የአመራሩን ሥልጣን እንደያዙ የሚገኙት በዕድሜ የገፉ ሰዎች ናቸው። »

በዚህ አጽናኝ ቃላት በኩኑ የሚገኘው የማንዴላ ቤተመዘክር ጉብኝት ተጠናቋል። ማንዴላ የሽምግልና ዘመናቸውን ከሚያሳልፉባት ኩኑ አንስቶ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጩኸት የበዛበት አውራ ጎዳና አገናኝ መንገድ ለመዘርጋት ይመስላል ሥራ ሲቀላጠፍ ይታያል። በመቶ የሚቆጠሩ የውጭ ሃገራት እንግዶችን ለመቀበል ታስቦ ይሆን?!ግምት ነው! ስለዚህ ጉዳይ በአሁኑ ሰዓት፣ማንም ሰው መናገር አይሻም።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ