1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማወዛገብ የቀጠለው የስደተኞቹ ጉዳይ እና ሜርክል

ሐሙስ፣ የካቲት 10 2008

የአውሮጳ ህብረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ አሁንም እንደተከፋፈለ ይገኛል። የህብረቱ አባል ሀገራት ከወራት አንስቶ እያከራከረ ባለው ወደ አህጉሩ በብዛት የገቡትን ስደተኞች በመከፋፈሉ ጉዳይ ሰበብ በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ሊያስወግዱ ይችሉ ይሆን?

https://p.dw.com/p/1HxXH
Berlin Regierungserklärung Angela Merkel im Bundestag
ምስል Getty Images/AFP/A. Berry

[No title]

አወዛጋቢው ጥያቄ መፍትሔ የማግኘት ያለማግኘት ዕድሉ ዛሬ በብራስልስ፣ ቤልጅየም በተጀመረው የህብረቱ አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት ጉባዔ ይለያል ተብሎ ይጠበቃል። ለችግሩ ህብረቱ ከተባበረ መፍትሔ ሊያገኝለት እንደሚችል የጀርመን መራሒተ መንግሥት ቢያስታውቁም፣ ብዙዎቹ አቻዎቻቸው ይህን አስተሳሰባቸውን አልተጋሩትም።


ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት 2016 ከገባ ወዲህ ዛሬ በብራስልስ የመጀመሪያው የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት ጉባዔ ሊከፈት ጥቂት ሲቀረው የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለሀገራቸው ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታኽ ባቀረቡት የመንግሥታቸው መግለጫ ወደ አህጉሩ በገቡት እጅግ ብዙ ስደተኞች ሰበብ ህብረቱ በታሪኩ ላገጠመው ለዚሁ ፈታኝ ውዝግብ መፍትሔ በመሻቱ ረገድ አግባቢ ሀሳብ ላይ እንደሚደርሱ ተስፋቸውን ገልጸዋል። አባል ሀገራትም በዚሁ ግዙፍ ችግር የተነሳ በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ለማስወገድ ተባብረው እንዲሰሩም ጀርመናዊትዋ መራሒተ መንግሥት ጥሪ አሰምተዋል።
« የጋራ ዓላማችን ፣ የኛን ርዳታ የሚፈልጉትን ሰዎች ወደፊትም መርዳት እንድንችል፣ የስደተኞችን ቁጥር በጉልህ ለመቀነስ ነው። አካራካሪ የሆነው ይህን ዓላማችንን ተግባራዊ የምናደርግበት ዘዴ ነው። እና የጀርመን መንግሥት ሶስት የመፍትሔ ሀሳቦችን አስቀምጦዋል። የመጀመሪያው፣ የስደትን መንሥዔ መታገል ነው። ሁለተኛው፣ ስደተኞች የሚመጡበትን በግሪክ እና በቱርክ መካከል ያለውን የአውሮጳ ህብረት የውጭ ድንበር ፣ ቢያንስ የሸንገን ሀገራት ድንበርን መከላከል ነው፣ ሶስተኛ፣ ስደተኞቹ ወደ አህጉሩ የሚመጡበትን ሕጋዊ መንገድ ማስተካከል ይሰኛል። »
ሜርክል ያቀረቡዋቸውን እነዚህን ሀሳቦች በተግባር መተርጎሙ አዳጋች መሆኑን አላጡትም፣ ያም ቢሆን ግን፣ ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ይህን እውን ማድረጉ አያከብደም፣ ለዚህም፣ እንደ መራሒተ መንግሥቷ አስተያየት፣ አውሮጳውያኑ መንግሥታት የትኛውን መንገድ መከተል እንደሚፈልጉ መወሰን አለባቸው።
« የአውሮጳ ህብረት በወቅቱ ለሚታዩ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ሳይቀር መልስ የማግኘት አቅም እንዳለውም ማስመስከር አለብን። »
በተለይ፣ ከመተባበር ይልቅ ድንበሮቻቸውን ለማጠር ከሚፈልጉት ጥቂት የማይባሉ የህብረቱ ሀገራት ይህን ትብብር በብራስልሱ ጉባዔ ማግኘታቸውን ታዛቢዎች ተጠራጥረውታል።
ይሁንና፣ የህብረቱ በተለይ ምሥራቅ አውሮጳውያኑ አባል ሀገራት ለስደተኞቹ ውዝግብ ከግሪክ ጋር የሚያዋስነውን የቡልጋርያ እና መቄዶንያ ድንበር እንዲዘጋ ያሰሙት ሀሳብ ቸው መፍትሔ እንደማይሆን አስጠንቅቀዋል።
« እንደ አውሮጳ ህብረት የባህር ድንበሮቻችንም መቆጣጠር መማር አለብን። የባህሩን ድንበር መቆጠጠሩ ከየብሱ የበለጠ አዳጋች ነው። ይህን ማድረግ የማይችል እና የየብሱን ድንበር ብቻ የሚያጥር፣ ከዚያም፣ ከአጥሩ በስተኋላ ስለሚገኙት ስደተኞች ደንታ የለኝም የሚል አህጉር፣ በኔ ፅኑ እምነት መሰረት፣ ትክክለኛው አውሮጳዊ መልስ እየሰጠ አይደለም። »
የስደተኞችን ቁጥር በመቀነሱ ረገድ የአውሮጳ ህብረት ከቱርክ ጋር የጀመረው ትብብር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በዚሁ መሰረት፣ ቱርክ የስደተኞችን ጉዞ የድንበሯን ቁጥጥር በማጠናከር እንድትከላክል፣ በምላሹም በሀገሯ የሚገኙትን 2,5 ሚልዮን የሶርያ የስደተኞችን ሁኔታ ለማሻሻል ሶስት ሚልያርድ ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
እንግዲህ፣ 28ቱ አባል ሀገራት፣ ህብረቱ በስደተኞች ሰበብ ለገጠመው ውዝግብ፣ ሜርክል እንደጠየቁት፣ ተባብረው መፍትሔ ማግኘት መቻል አለመቻላቸው በቀጣዮቹ ሰዓታት በብራስልስ በሚካሄደው ምክክር የሚታይ ይሆናል።

Griechenland Frontex Küstenwache bei Lesbos
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Palacios
Mazedonien baut zweiten Zaun an der Grenze zu Griechenland
ምስል picture-alliance/dpa/G. Licovski


አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ