1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማይክሮሶፍት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 28 2008

በኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያ የሆነው ማይክሮሶፍት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት የመማር እና ማስተማር ሂደት እንዲያግዝ በሚል ከትምህርት ሚንሥቴር ጋር ስምምነት ማድረጉን ገልጧል። እንደ ማይክሮሶፍት ማብራሪያ ከሆነ ስምምነቱ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በዲጅታሉ ዓለም ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።

https://p.dw.com/p/1IPtA
Betriebssystem Windows 10 Microsoft
ምስል picture-alliance/dpa/P. Steffen

ማይክሮሶፍት በኢትዮጵያ

ስምምነቱ ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ክኅሎት እንዲዳብር፤ የፈጠራ አስተሳሰብ እንዲጎለብት፤ ብሎም በሀገር ውስጥ ያሉ አስተማሪዎች አቅም እንዲገነባ መንገድ ይከፍታ ተብሏል። በእርግጥ ማይክሮሶፍት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ገበያው ለመግባት ከመፈለጉ ባሻገር የፈጠራ ሰዎች እና ተመራማሪዎች በራሳቸው እንዲቆሙ ለማስቻል ምን ያኽል ጥረት ያደርጋል?

ማይክሮሶፍት ከትምህርት ሚንሥቴር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሶፍትዌር አበልፃጊ ተማሪዎች የሚለማመዱባቸው የማይክሮሶፍት ምርቶችን እንዲሁም የኦፊስ 365 የትምህርት ማገዣ መሣሪያዎችን ያበረክታል። አቶ ዘላለም አሠፋ፤ የኢትዮጵያ የምርምር እና የትምህርት መረብ ዳይሬክተር ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞም ቢሆን የማይክሮሶፍት ምርቶች ገበያው ላይ ስለሚገኙ ስምምነቱ ዕውቀትን ገብይቶ ምርቱን በደንብ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

ማይክሮሶፍት፦ ዋነኛ ግቡ «የሕይወት ዘመን ሙሉ የትምህርት ፍላጎትን የሚያጭር በጥልቀት አሳታፊ ልምድን መፍጠር» እንደሆነ ይገልጣል። ማይክሮሶፍት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ያደረገው ስምምነት ለተማሪዎች ምን የሚያግዘው ነገር አለ? ኢትዮጵያ ውስጥ ጀማሪ የንግድ ሰዎችን የሚረዳው አይስ አዲስ የተሰኘው የአዲስ ግኝት ማዕከል መስራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ለማ። የማይክሮሶፍት እና የትምህርት ሚንስቴር ስምምነት ተማሪዎች ሶፍትዌሮችን በቀላሉ እንዲያገኙ እና እንዲለማመዱ ይረዳል ሲሉ ጠቅሰዋል።

«ለሕይወት አስፈላጊ ክኅሎቶች ብልፃጌን ማነቃቃት ብሎም አስተማሪዎች የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት መኮትኮት እና መስመር ማስያዛቸው ላይ ማገዝም» የማይክሮሶፍት ተጨማሪ ግብ እንደሆነ በድረ-ገጹ ሰፍሮ ይገኝል። ያም በመሆኑ ማይክሮሶፍት በስምምነቱ መሠረት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት አጋዥ ምርቶችን የለገሰው ሙሉ ለሙሉ በነፃ ነው።

በእርግጥ ማይክሮሶፍት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወሰኑ አገልግሎቶቹን በነፃ ሲያቀርብ ራሱም ወደፊት በስፋት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ አርቆ በመተለም ነው።

በስምምነቱ መሠረት ማይክሮሶፍት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሶፍትዌር አበልፃጊ ተማሪዎች የሚለማመዱባቸውን ምርቶቹን ለግሷል። ለአብነት ያህልም ስድስት ሺህ ያኽል የሶፍትዌር አበልጻጊዎች የሚለማመዱበት (DreamSpark) የተሰኘውን መድረክ በነፃ አበርክቷል።

ማይክሮሶፍት በነፃ ያቀረባቸው ሌሎቹ ምርቶች በኢንተርኔት የሶፍትዌር መለማመጃ መሣሪያዎች በእንግሊዝኛው (BizSpark) እና (Kodu Game)ይሰኛሉ። ቢዝስፓርክ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ሥራ ላይ ሆነው በመገናኘት ተጨማሪ ሥራ እንዲፈጥሩ የሚያስችል የኢንተርኔት መድረክ ነው። ኮዱ ጌም ደግሞ የተለያዩ የኢንተርኔት ጨዋታዎችን ለመሥራት እና ለማበልጸጊያነት ያገለግላል። ለአሠልጣኞች የምስክር ወረቀት፣ የምርት ፍቃድ፣ የማማከር እና የድጋፍ አገልግሎቶችንም ማይክሮሶፍት ይሰጣል። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለወጡ ተማሪዎች ማይክሮሶፍት ምን አስተዋፅዖ ያደርጋል?

የዕውቀት ሽግግሩ እንዲፋጠን ማይክሮሶፍት የሚያደርገው ትብብር የሚበረታታ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሶፍትዌር ማበልጸግ ክኅሎቱ ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ። እነዚህ ወጣቶች ያበለጸጓቸው ሶፍትዌሮች ወደ ገበያ እንዲገቡ ማይክሮሶፍት እና መሰል ዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

የማይክሮሶፍት ሠራተኛ የኩባንያውን አዲስ ምርት ኒውዮርክ ውስጥ ይፋ ሲያደርግ
የማይክሮሶፍት ሠራተኛ የኩባንያውን አዲስ ምርት ኒውዮርክ ውስጥ ይፋ ሲያደርግምስል Getty Images/A. Burton
የማይክሮሶፍት መሥራች ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ ስለ ድሪምስፓርክ መጀመር ሲናገሩ
የማይክሮሶፍት መሥራች ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ ስለ ድሪምስፓርክ መጀመር ሲናገሩምስል AP

አዜብ ታደሰ