1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል የፖለቲካ ልዩነቶች እንዲከበሩ ጥሪ አቀረቡ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 22 2010

የጀርመን መራሔተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በፖለቲካ ተዋስኦ የሚሳተፉ የሀገራቸው ዜጎች አንደኛው ለሌላው አጋርነት እና ክብር እንዲያሳይ ጠየቁ፡፡ መራሒተ-መንግሥቷ የአውሮፓ ትብብር የቀጣይ ዓመታት “ወሳኝ ጥያቄ ነው” ሲሉ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ተናግረዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2qAGq
Deutschland | Neujahrsansprache BK Angela Merkel 2018
ምስል picture-alliance/dpa/H. Hanschke

መራሔተ መንግስቷ ነገ የሚብተውን የጎርጎሮሳዊውን 2018 ዓ.ም. አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በጀርመን ውስጥ የሚታየውን ክፍፍል አጽንዖት ሰጥተውታል፡፡ ሜርክል “በሀገራችን እንደዚህ አይነት ልዩነት የተንጸባረቀባቸው አመለካከቶች ለረጅም ጊዜ አልነበሩም ሲሉም አክለዋል፡፡ የተወሰኑት እንደውም በማህበረሰቡ ውስጥ ስላለው መከፋፈል ይናገራሉ” ሲሉ በጀርመናውያን ዘንድ ስጋት የፈጠረውን ህብረት የማጣት ችግር እንደሚረዱ ተናግረዋል፡፡ 

“ስኬታማነት እና በራስ መተማመን ነገር ግን ፍርሃት እና ጥርጣሬ፡፡ እነዚህ ሁለቱም በሀገራችን ያሉ እውነታዎች ናቸው፡፡ ለእኔ ሁለቱም ማትጊያዎች ናቸው”
ሜርክል ጀርመናውያን አንዳቸው ለሌላኛው “ትኩረት እንዲሰጡ”፣ እርስ በእርስ “ይደማመጡ እና ይግባቡ ዘንድ” ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ የ63 ዓመቷ ሜርክል በመስከረም ወር በጀርመን ከተካሄደው የምክር ቤት ምርጫ በኋላ መንግስት መመስረት ያልቻለችውን ሀገራቸውን በጊዜያዊነት መምራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህንኑ የሀገሪቱን አንገብጋቢ ጉዳይ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ያነሱት ሜርክል በተቻለ ፍጥነት መንግስት ለመመስረት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ጀርመን ለቀጣይ 10 እና 15 ዓመታት የሚኖሯትን ግቦችም አስቀምጠዋል

የእርሳቸው ስራ በጀርመን ፖለቲካዊ መረጋጋት ማምጣት መሆኑን የጠቆሙት መራሔተ መንግስቷ የሀገራቸውን የወደፊት ዕጣ ከአውሮፓ ጋር አቆራኝተው የአህጉሪቱን አካሄድ አብራርተዋል፡፡ 
“በዚህ ሁሉ ውስጥ የጀርመን መጻኢ እጣ-ፈንታ ከአውሮፓ የወደፊት ሁኔታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ሃያ ሰባቱ የአውሮፓ አባል ሀገራት በህብረት እንደ አንድ ማህብረሰብ እንዲቆሙ ሊደረግ የሚገባበት ነው፡፡ ይህ ለመጪዎቹ ዓመታት ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ጥያቄው እኛ አውሮፓውያን በዓለም አቀፉም ሆነ የዲጅታሉ ዓለም በአጋርነት እና የራስ መተማመን ለዕሴቶቻችን ታማኝ ሆነን ማንጻባረቅ እንችላለን ወይ? የሚለው ነው፡፡ በኢኮኖሚ ስኬታማ እና ፍትሃዊ ለሆነች አውሮፓ ለመስራት፤ ድንበራችንን እና የዜጎቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነን ወይ? የሚለው ነው”  
አውሮፓ ለመጪው ጊዜ ምቹ እንደትሆን ለማድረግ ሀገራቸው ከፈረንሳይ ጋር ተባብራ እንደምትሰራም ቃል ገብተዋል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ