1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ ዲሞክራሲ በራቃት አልጀሪያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2006

አልጀሪያን እጎአ ከ1998 አንስቶ ለ16 ዓመታት በሦስት የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው አንቀጥቅጠው ገዝተዋል፤ ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ። ካለፈው ዓመት አስንስቶ በነርቭ ዕክል በሽታ የሚሰቃዩት የ77 ዓመቱ አዛውንት ስልጣን ዛሬም አልበቃኝም፥ ለአራተኛ ጊዜ መጥቻለሁ ብለዋል። የፊታችን ሐሙስ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/1BiOg
ምስል DW/ El Kebir Nour El Hayet
ፖሊሶች አልጄሪያዊ ተቃዋሚን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ
ፖሊሶች አልጄሪያዊ ተቃዋሚን በቁጥጥር ስር ሲያውሉምስል Reuters

ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ ለፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ በዋናነት ሁለት የመከራከሪያ ነጥቦችን ይዘው ነው ብቅ ያሉት። የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብትና የደኅንነት ጉዳይ። በማርቡርግ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ራሺድ ኦዋይሳ።

«በተደጋጋሚ የሚደመጠው ዋና የመከራከሪያ ነጥብ የደኅንነት ጉዳይ ነው። ይህን ደግሞ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ በሚገባ ተጠቅመውበታል። እራሳቸውን በሀገሪቱ ሠላም ማስፈን ያስቻሉ ሰው ተብለው እንዲቆጠሩ ማድረጉ ተሳክቶላቸዋል። በእርግጥ የእሳቸው ቀዳሚ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዛርዋል ነበሩ ያን ማሳካት ችለው የነበሩት። ቡተፍሊካ ግን ይህ ርዕሠ-ጉዳይ የራሳቸው ሆኖ እንዲታይ ማድረግ ችለዋል።»

በአልጄሪያ ከመጋረጃው ጀርባ እንዲያ የስልጣን ሽኩቻው በተጧጧፈበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንቱ የማይነቃነቅ ስልጣን የተቆናጠጡ ይመስላል። በእርግጥም አልጀሪያ ውስጥ ከመጋረጃው ጀርባ የጦር ኃይሉና ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባሩ በአንድ ወገን፤ በሌላ ወገን ደግሞ የሐገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ማብቂያ የለሽ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ እንደተዘፈቁ ይነገራል። እንደ ፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ትንተና ከሆነ ዘንድሮ ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ውስጥ ውስጡን በልዩነት የሚጠዛጠዙትን ጦሩንና የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ያቀራርባሉ በሚል ነው። ሆኖም ቡተፍሊካ በስልጣን ዘመናቸው ሁሉ ወደየትኛውም የኃይል ሚዛን ላለማድላት ሲያደቡ መኖራቸው ይነገራል።

«ጥቅም ፈላጊ ሰው ናቸው። ሥልጣን ባይኖራቸው መኖር አይችሉም። በእዛው መጠን ደግሞ ዙሪያቸውን የተሰባሰቡት ሰዎች የጋራ ጥቅም አደጋ እንዳይደርስበት በሚል በምርጫው እንዲሳተፉ ግፊት ሳይደርግባቸውም አይቀርም። ሀገሪቷ ነፃ ከወጣች ጀምሮ አይታ የማታውቀው ሙሰኛ መንግሥት ነው ያለው። ቡተፍሊካ ሀገሪቷ በመንግሥት አስተዳደር እራሷን ችላ እንዳትቆም አድርገው ነው የሚያልፉት።»

አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ በስልጣን ዘመናቸው እንዲያ ተደላድለው ለመክረም በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ባለመካከለኛ ገቢ ሕዝብ በጥቅም ደልለዋል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ ራሺድ ኦዋይሳ። ሞሐመድ ሲፋዊ የተባለው ጋዜጠኛ በበኩሉ «የአልጄሪያ የፃነት ምሥጢር ታሪክ» በሚል ለኅትመት ባበቃው መጽሐፉ በአልጄሪያ ደሀው ሕዝብ ዝምታ የመምረጡን ምሥጢር በሦስት ይከፋፍለዋል።

ሲጀመር ይላል ጋዜጠኛው፤ ሕዝቡ እጎአ ከ1992 እስከ 2002 ድረስ ለአስር ዓመታት ተዘፍቆ ወደነበረበት የእርስ በእርስ ግጭት ማምራት አይፈልግም። ሲቀጥል ከነዳጅ ሽያጭ የሚገኘውን ሀብት ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ቁጥር መንግሥት ያለምንም ዕቅድ ተቃውሞውን ለማብረድ ይጠቀምበታል። ሲሰልስ በአልጀሪያ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ተቃዋሚ የለም። ያሉትንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ አንድም በጥቅም ገዝተዋቸዋል አለያም ደብዛቸውን አጥፍተዋቸዋል ሲል ያብራራል ጋዜጠኛው።


የአልጀሪያ ወጣቶች በኑሮ ውድነት ማጉረምረም ሲጀምሩ ደግሞ ከሀገሪቱ ብሔራዊ ሀብት እየቆነጠሩ ወለድ አልባ ብድር በመስጠት ክህሎትም ተክነዋል አዛውንቱ ፕሬዚዳንት። እንዲያም ሆኖ ግን ለአራተኛ ጊዜ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ተቃውሞ አስነስቷል። «ባራካት!» የተባለ ቡድን በመዲናዋ አልጀርስ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የተቃውሞ ፅሁፎችን የያዘ በራሪ ወረቀት እየበተነ ይገኛል። «የተማፀንኩዎት ለአራተኛ ጊዜ ለመወዳደር ብቅ እንዲሉ አይደለም። ይልቁንስ የፖለቲካ ጭንብልዎን ወደያ ይሉ ዘንድ እጠይቅዎታለሁ» ይላል የጽሁፉ መልዕክት።
ከሁለት ዓመታት በፊት ቡተፍሊካ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር። «እኔና የእኔ ዘመነኞች የሚገባንን አድርገናል። አሁን በፖለቲካ ባቡሩ ላይ የሚሳፈሩት ወጣቶች ናቸው።» በተግባር ባያውሉትም እሳቸው ያንን ብለው ነበር፤ ወጣቱስ? የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ራሺድ ኦዋይሳ ።

«አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ወጣቶቹ በሚሰጣቸው ገንዘብ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የአብዛኞቹ መልስ ጀልባ እገዛበታለሁ የሚል ነበር።»

እንደ ራሺድ ኦዋይሳ ከሆነ አብዛኞቹ የአልጄሪያ ወጣቶች በፖለቲካው ባቡር ላይ የመሳፈር ፍላጎት የላቸውም። ይልቁንስ ከባሕር ጠረፋቸው ወደያ ተዘርግታ ወደምታብረቀርቀው አውሮጳ በገዙት ጀልባ አንድ ቀን ፈትለክ ማለት ነው ህልማቸው። ፕሬዚዳንታቸው ግን ለአራተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ከመሆን የሚያግታቸው ኃይል እንደሌለ በመተማመን ዳግም ለምርጫ ብቅ ብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቡተፍሊካ ለ4ኛ ጊዜ መወዳደራቸውን በመቃወም
ቡተፍሊካ ለ4ኛ ጊዜ መወዳደራቸውን በመቃወምምስል picture-alliance/dpa

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ